አንዲት ሴት እና አንድ ወጣት ስማርት መነፅር አድርገው

4 ታህሳስ 2024

የሥራው ዓለም በፍጥነት እየተቀየረ ነው። ዛሬ አስፈላጊ የሚባሉ በርካታ ሥራዎች በቅርቡ ሊጠፉ ይችላሉ።

ዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም በቅርቡ ባስጠናው ጥናት መሠረት ሁለት ጉዳዮች ነገሮችን እየለዋወጡ ነው ይላል። አንደኛው የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፈጠር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዓለም ወደ አረንጓዴ ምጣኔ ሀብት የምታደርገው ጉዞ ነው።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ቢግ ዳታ እና ክላውድ ኮምፒውቲንግ የተባሉት እየረቀቁ የመጡ ዘርፎች በሥራው ዓለም ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጡ እሙን ነው።

ምንም እንኳ አንዳንድ ሥራዎችን ከጥቅም ውጪ ቢያደርጉም፣ የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መምጣት መልካሙ ዜና አዳዲስ ሥራዎችን መፍጠራቸው ነው።

የዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም አጥኚዎች በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከዓለማችን ሥራዎች ቢያንስ ሩብ ያህሉ ይለወጣሉ ይላሉ።

ለዚህ ነው በጣም ፉክክር እየበዛበት በመጣው የሥራ ዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን አዳዲስ ክህሎቶችን መማር አስፈላጊ ነው እየተባለ ያለው።

አንድ ኢንጂነር ኤሌክትሪካል ማሺን ሲሰራ

ተፈላጊ ክህሎቶች

የቴክኒካዊ የሆኑ ክህሎቶች በአዲሱ የሥራ ዓለም ተፎካካሪ ለመሆን እና በልጦ ለመገኘት እጅግ አስፈላጊ ናቸው።

ይህ ማለት ሁሉም ሰው ኮምፒውተር የፕሮግራም መቀመሪያ ቋንቋ ማወቅ አለበት አሊያም በማሽን ለርኒንግ በሚባለው የረቀቀ ዘርፍ ልቆ መገኘት አለበት ማለት ግን አይደለም።

ነገር ግን ወደፊት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ማቲማቲክስ አሊያም ስቴም በተሰኘው መስክ ልቀው የተገኙ ሰዎች ተፈላጊ ይሆናሉ።

ልጄ በትምህር ቤት በየትኛው መስክ ልቆ መገኘት አለበት? ብላችሁ ከጠየቃችሁ መልሱ ማቲማቲክስ [የሒሳብ ትምህርት]፣ ኮምፒውተር ሳይንስ አሊያም የተፈጥሮ ሳይንስ ነው።

ቀጥሎ ደግሞ ‘አናሊቲካል ቲንኪንግ’ ወይም ነገሮችን የመተንተን ጥበብ አስፈላጊ ክህሎት ነው። ይህን ለማድረግ የማሰብ እና የማገናዘብ ችሎታ እንዲሁም ነገሮችን የማገናኘት እንዲሁም በስሜት እና በግላዊ ምርጫ ሳይገደቡ ውሳኔ ላይ መድረስ ግድ ይላል።

ይህን ክህሎት ለማዳበር ንቁ መሆን እና ሀሳብን ሰብስቦ በትኩረት ማሰላሰል ይጠይቃል።

አንዲት ታዳጊ ሮቦት ስትሰራ

የሞባይል ስልኮች፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ ጌሞች እና ማስታወቂያዎች ትኩረታችንን ለመሳብ በሚሯሯጡበት ዘመን ይህንን ክህሎት መካን ቀላል አይሆንም።

‘አናሊቲካል ቲንኪንግ’ የማወቅ ጉጉት እና ራስን ማበልጸግን ይሻል። በየጊዜው ትምህርታችንን ማሻሻል እና ግባችን ላይ ማተኮር ግድ ይለናል።

የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎታችንን በተቻለ መጠን ማሳደግ በቀላሉ የማይታይ አስፈላጊ ክህሎት ነው።

የፈጠራ ክህሎትም በጣም አስፈላጊ ነው። በሳይንስ፣ በኢንጂነሪንግ፣ በዲዛይን እና አርት (ጥበብ) ልቀው የሚገኙ ሰዎች ቴክኒካዊ ዕውቀታቸውን ከፈጠራ ክህሎታቸው ጋር ማጣመር የቻሉ ሰዎች ናቸው።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ዘመን ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት እና ርህራሄ ሁለት በቀላሉ የማይታዩ ክህሎቶች ናቸው።

ቴክኖሎጂ ምንም እየፈጠነ እያደገ ቢመጣ የሰው ልጅ ከሰው ልጅ ውጪ መኖር አይችልም። የቡድን ሥራ፣ የማዳመጥ ችሎታ፣ ታሪክ የመናገር አቅም፣ ድጋፍ እና ርህራሄ የበለጠ ቦታ ይኖራቸዋል።

በአውሮፓውያኑ 2020 ሊንክዲን በተሰኘው ለፕሮፌሽናሎች የተዘጋጀ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ የወጣ ዘገባ ‘ኮሚዩኒኬሽን’ ባለንበት ዓለም ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ክህሎት ሆኗል ይላል።

የሶፍትዌር ኢንጂነሮች

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች

በሚመጣው ዓለም ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በጣም አስፈላጊ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ማሽን ለርኒንግ እያደጉ ሲመጡ ደግሞ አዳዲስ ዕድሎች መፈጠራቸው ግድ ነው።

‘ፕሮምፕት ኢንጂነር’ የተባለው ሥራ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ኮሚዩኒኬሽንን አጣምሮ የያዘ ነው። ይህ ሥራ ወደፊት በጣም ተፈላጊነቱ እየጨመረ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር ተያይዞ ሌላ ተፈላጊ ሊሆን የሚችል ሥራ ደግሞ ሥነ-ምግባር (ኤቲክስ) ነው። ይህ ሥራ የሥነ-ምግባር እና የሴኪዩሪቲ ኢንጂነር ባለሙያ ለሆኑ ሰዎች የሚሆን ሲሆን፣ ለአጠቃቀም ቀላል የሆነ በሰዎች እና በማሽን መካከል የሚደረግ ግንኙነትን የሚመለከት ነው።

በአጠቃላይ ሰዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወዳጅ እንዲያዩት እንዲሁም እንዴት አብሮ መሥራት እንዳለባቸው ሊያውቁ እንደሚገባ ይመከራል።

ሌሎች ተፈላጊ የሚባሉ ሥራዎች ‘ቢግ ዳታ’ በተባለው መስክ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆኑ ኔትፍሊክስ እንደተሰኘው ዓይነት ግዙፍ ድረ-ገፆች ይህን የሚጠቀሙ ናቸው። የሳይበር ሴኪዩሪቲ ስፔሻሊስቶችም በፍፁም ሥራ አያጡም።

የፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ የቢዝነስ ተንታኞች እንዲሁም ‘የብሎክቼይን ሲስተም’ ባለሙያዎችም በእጅጉ ከሚፈለጉት ሙያተኞች መካከል ናቸው።

የኮንስትራክሽን ሠራተኞች በፀሐይ የሚሠራ መሣሪያ ሲገጥሙ

አረንጓዴ ሥራዎች

የመጪው ዘመን የዓለማችን እና የሕዝቧ ስጋት የሆነው የተፈጥሮ አካባቢ መጎዳት እና የአየር ጠባይ ለውጥ እንዲሁም ይህንን ተከትሎ እየተከሰተ እና እየተስፋፋ ያለው የተፈጥሮ አደጋ ነው። ስለዚህም ይህንን አደጋ ለመቀልበስ ተፈጥሮን መጠበቅ እና መንከባከብ ዋነኛ ጉዳይ ሆኗል።

ስለዚህም ከተፈጥሮ ጋር የተስማሙ አረጓዴ የሚባሉት ፈጠራዎች እና ሥራዎች በመጪው ዘመን ሀገራት እና ታላላቅ ተቋማት ከፍተኛ ትኩረስ በመስጠት ቢሊዮኖችን የሚያፈሱባቸው ዘርፎች ናቸው።

የአረንጓዴ ሥራዎች ተፈላጊነት እጅግ እየጨመረ መጥቷል ይላል ዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ባወጣው ዘገባ። በአውሮፓውያኑ 2030 በንፁህ ኢነርጂ እንዲሁም ‘ሎው ኢሚሺን’ በተሰኙት መስኮች 30 ሚሊዮን ሥራዎች እንደሚፈጠሩ ሪፖርቱ ይጠቁማል።

ለጊዜው አረንጓዴ ሥራዎችን እየፈጠሩ ያሉት ምዕራባዊያን አገራት ቢሆኑም እንደ ጃፓን እና ቻይና ያሉ አገራት ብቅ ብቅ እያሉ ነው።

የከተማ ግንባታ እና የሥነ-ሕንፃ ባለሙያዎች እንዲሁም ዲዛይነሮች እና ‘ስማርት’ [እጅግ የዘመኑ] ቤት የሚገነቡ ሰዎችም ተፈላጊነታቸው ይጨምራል።

ሁለት የሆስፒታል ሰራተኞች

የጤና ባለሙያዎች

የዓለማችን ሕዝብ እያረጀ ነው። በአማካይ የሰው ልጅ እዚህች ምድር ላይ የሚኖረው ዕድሜም እየጨመረ ይገኛል። ይህ ማለት ለሰው ልጆች እንክብካቤ መስጠት ተፈላጊ የሚሆን መስክ ነው ማለት ነው።

በሚቀጥሉት ዓመታት የጤና ባለሙያዎች ተፈላጊነታቸው የሚቀንስ አይሆንም። በተለይ ደግሞ በሕክምናው መስክ የሚሠሩ ለታካሚዎቻቸው መድኃኒት ብቻ ሳይሆን የሞራል ድጋፍ የሚሰጡም ተፈላጊ ይሆናሉ።

ነገር ግን ዶክተሮች እና የጤና ባለሙያዎች አዳዲስ የሕክምና መንገዶችን መማር ግድ ይላቸዋል። ሰው ሠራሽ አስተውሎት ይህን ለማገዝ እጅግ ይጠቅማል።

ሳይኮቴራፒስቶች እና በራስ ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚረዱ አማካሪዎች እና አሠልጣኞች አሊያም የመንፈሳዊ ዓለም መሪዎችም ተፈላጊነታቸው የሚቀንስ አይመስልም።

የእጅ ሙያ

በሚቀጥሉት ዓመታት እንደ ሜካኒክ፣ የጥገና ባለሙያ፣ የኤሌክትሪክ ሥራ ባለሙያዎች እና የሕንፃ ግንባታ ሠራተኞችን የመሳሰሉ የእጅ ሙያተኞች ተፈላጊ መሆናቸው የሚቀር አይደለም።

ጥቃቅን እና ቀጥተኛ የሚባሉ ችግሮችን ለመፍታት የሰው ልጅ አስፈላጊ መሆኑ አይቀሬ ነው። ነገር ግን የእጅ ሙያ ያላቸው ሰዎች ተፈላጊነታቸውን ለመጨመር በየጊዜው ክህሎታቸውን ማዳበር አለባቸው።

በግብርናው ዓለም ያሉ አዳዲስ ሥራዎችም ተፈላጊነታቸው ከፍ ይላል። የዓለማችን ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ሁሉም በልቶ ማደር አለበት። ነገር ግን ወደፊት ይህን ጥያቄ የሚመልሱት አርሶ አደሮች ሳይሆኑ ኢንጂነሮች ናቸው።

ግብርና በአርሶ አደሮች ሳይሆን በኢንጂነሮች የሚሠራ ይሆናል
የምስሉ መግለጫ,ግብርና በአርሶ አደሮች ሳይሆን በኢንጂነሮች የሚሠራ ይሆናል

ሊጠፉ የሚችሉ ሥራዎች

ዓለም እና ሕዝቧ በእጅጉ እየዘኑ ፍልጎታቸው እየረቀቀ ሲሄድ ተፈላጊ የመሆኑት ሙያዎች እና ዘርፎች ከመቀየራቸው ጋር ለዘመናት አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች ተሰማርተውባቸው የቆዩ አንዳንድ ሙያዎች ተፈላጊነታቸው ያበቃል።

አሁንም እንደሚታየው በበርካታ ዘርፎች ውስጥ የባለሙያዎች ወይም የተመደቡ ሠራተኞች በነበሩባቸው ቦታዎች ላይ ኮምፒውተሮች ወይም ማሽኖች ተተክተው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ለመሆኑ በዚህ ፈጣን ለውጥ ምክንያት ተፈላጊነታቸው ከመቀነስ አልፎ ከናካቴው ሊጠፉ የሚችሉት የሙያ ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?

ከዚህ በተቃራኒ በወደፊቱ ዓለም ተፈላጊነቱ አይደበዝዝም የሚባልለት መስክ ‘ታሪክ መናገር’ ነው።

ምንም እንኳ ሰው ሠራሽ አስተውሎት መስኩን ቢፈታተነውም ፀሐፊዎች፣ ገጣሚዎች፣ አዘጋጆች፣ ተዋንያን፣ ኮሜዲያን፣ አርቲስቶች እና ሙዚቀኞች ወደፊትም ተፈላጊ መሆናቸው አይቀርም።