ቴሌግራም

ከ 2 ሰአት በፊት

ተጠቃሚያቸው እያደገ ከሚገኙት የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መተግበሪያዎች መካከል አንዱ የሆነው ቴሌግራም ሲወቀስበት የነበረውን የተጠቃሚዎች ደኅንነት ጥበቃን በተመለከተ የአቋም ለውጥ አደረገ።

በዚህም ቴሌግራም ከዓለም አቀፍ ተቋም ጋር በመተባበር የሕጻናት የወሲብ ብዝበዛ ይዘቶች በገጹ ላይ እንዳይዘዋወሩ ለመገደብ ተስማምቷል።

ቴሌግራም ለሕጻናት ጥበቃ የሚያደርግ አሠራርን እንዲከተል ለዓመታት ጫና ሲደረግበት ቢቆይም፣ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ ነበር።

ቴሌግራም አብሮት ለመሥራት የተስማማው ‘ዘ ኢንተርኔት ዋች ፋውንዴሽን’ ወይም አይደብሊውኤፍ ተቋም የበይነ መረብ አገልግሎት ሰጪዎች ለሕጻናት ጥበቃ የሚገለገሉበት ነው።

የቴሌግራም መሥራች ፓቫል ዱሮቭ ፓሪስ ውስጥ ከታሰረ በኋላ ቴሌግራም ይዘቶች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ተስማምቷል።

ተቋሙ የቴሌግራም ውሳኔ “ለውጥ የሚያመጣ ነው” ብሏል። ሆኖም ግን ቴሌግራም አሁንም ረዥም ጉዞ እንደሚጠብቀው አክሏል።

የተቋሙ ተጠባባቂ ኃላፊ ዴሬክ ሬይሂል “አይደብሊውኤፍን በመቀላቀል ቴሌግራም በዓለም ቀዳሚ ቦታ ያላቸው የጥንቃቄ አካሄዶች በመከተል ይዘቶችን መገደብ ይችላል” ብሏል።

የቴሌግራም መሥራች ፓቫል ዱሮቭ
የምስሉ መግለጫ,የቴሌግራም መሥራች ፓቫል ዱሮቭ

‘በኪሳችን ያለው ጨለማ ማኅበራዊ ሚዲያ’

ቴሌግራምን ከ950 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይጠቀማሉ። ሌሎች ዓለም አቀፍ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ከሚከተሉት ፖሊሲ በተለየ የተጠቃሚዎችን የግል መረጃን የሚጠብቅ መተግበሪያ እንደሆነም በመግለጽ ራሱን ያስተዋውቃል።

ቢቢሲ እና ሌሎችም መገናኛ ብዙኃን የሠሩት ምርመራ እንደሚያሳየው ግን በቴሌግራም ላይ አደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ጨምሮ የሕጻናት ወሲባዊ ይዘት ያላችወ ይዘቶች ይዘዋወራሉ፤ የበይነ መረብ ምዝበራም ይፈፀማል።

ከዚህም የተነሳ አንድ ባለሙያ “በኪሳችን ያለው ጨለማ ማኅበራዊ ሚዲያ” ሲሉ ነው ቴሌግራምን የገለጹት።

ነሐሴ ላይ የቴሌግራም መሥራች በፓሪስ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ይታወሳል።

ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እና የሕጻናት ወሲባዊ ይዘት ያላችወ ይዘቶችን በተመለከተ ከሕግ አስከባሪዎች ጋር ትብብር ባለማድረግ ነበር መሥራቹ የተከሰሰው።

ተጨማሪ ምርመራ እስከሚደረግ ድረስ ከፈንሳይ እንዳይወጣም ውሳኔ ተላልፏል።

ቴሌግራም በበኩሉ መሥራቹ መታሰሩ ፍትሐዊ እንዳልሆነ ገልጿል። ተጠቃሚዎች በገጹ በሚያከናውኑት ነገር ተጠያቂ መሆን አንደሌለበትም አስታውቋል።

ቴሌግራም ከመሥራቹ መታሰር በኋላ የሚከተሉትን ለውጦች አድርጓል፦

የቴሌግራም መሥራች መተግበሪያው ላይ “አበረታች” ለውጦች ማድረጉም ተገልጿል።

ቴሌግራም አብሮት ለመሥራት የተስማማው ‘ዘ ኢንተርኔት ዋች ፋውንዴሽን’ የሕጻናት የወሲብ ብዝበዛ ይዘቶችን ማስጠፋት የሚችል ተቋም ነው።

ቴሌግራም እንደ ዋትስአፕ እና እንደ ሲግናል በተጠቃሚዎች መካከል ያለን የመረጃ ልውውጥ በምሥጢር የሚይዝ መተግበሪያ ነው።

መሥራቹ የተወለደው ሩሲያ ሲሆን ነዋሪነቱ ዱባይ ውስጥ ነው። የሩሲያ፣ የፈረንሳይ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንዲሁም የካረቢያን ደሴቶቹ ሴንት ኪትስ እና ኒቫስ ዜግነትም አለው።

ቴሌግራም በተለይም በሩሲያ፣ በዩክሬን እና በኢራን ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።