
ከ 1 ሰአት በፊት
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን የደኅንነት ስጋት አለብን ያሉ የአማራ ተወላጆች በመንግሥት ይሁንታ የታጠቅነውን ሕጋዊ የጦር መሳሪያ እንድንፈታ ተደረግን ሲሉ ተናገሩ።
በዞኑ ጊዳ አያና ወረዳ አንዶዲ ዲቾ ቀበሌ ሰኞ ኅዳር 23/2017 ዓ.ም. በአካባቢው የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት “ከበባ” በማድረግ ከ85 በላይ “ሕጋዊ” የግል የጦር መሳሪያዎችን እንደወሰዱ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተለያዩ ጊዜያት በነዋሪዎች ላይ በሚፈጽመው ጥቃት ምክንያት የደኅንነት ስጋት ያደረባቸው ነዋሪዎች መሳሪያቸውን እንዲፈቱ መደረጋቸው ለጥቃት ተጋላጭ ያደርገናል ብለዋል።
ሰኞ ከሌሊቱ 11፡00 እስከ ረፋድ 5፡00 ድረስ በዘለቀው መሳሪያ የማስፈታት እርምጃ 01 ቀበሌ በተባለ አካባቢ የመከላከያ ሠራዊት አባላት “በየቤቱ እየገቡ” የጦር መሳሪያዎችን መውሰዳቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ነዋሪ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመሆን በስም ዝርዝር መሠረት የነዋሪዎችን ቤት በመክበብ ግል መሳሪያቸውን መውሰዳቸውን “ዝርፊያ” ብለውታል።
የአካባቢው አስተዳዳሪ ግን በስፍራው ምንም ዓይነት ስጋት እንደሌለ እና ነዋሪው የተለመደውን መደበኛ ሕይወት እየመራ ነው በማለት ዝርዝር ሁኔታ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ከደርግ መንግሥት ጀምሮ የታጠቁትን መሳሪያ “እንደተነጠቁ” የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ “. . . ሌላው ታጠቂው [አጥቂዎች] ሳይጠፋ እንዴት አድርገን እንሰጣለን? ስንል ‘አይቻልም፤ አይቻልም’ አሉ። እንግዲህ የሕግ ሰው ናቸው ምን እናደርጋለን ብለን ሰጠን” ሲሉ ስለ ሁነቱ ተናግረዋል።
የፀጥታ አባላቱ ከነዋሪው ለቀረበላቸው ጥያቄ መሳሪያ እንዲያስፈቱ መታዘዛቸውን ብቻ በመግለጽ እንደሄዱ ይህም በደኅንነታቸው ላይ ስጋት እንደፈጠረባቸው ሌላ ነዋሪ ገልጸዋል።
“ምንድን ነው ችግሩ ስንል ‘ታዘናል’ አሉን። ለምን ይሄ ይደረጋል? [መሳሪያው ከተወሰደ] የእኛ የመኖር ተስፋ የለንም። እናንተ ነገ ትሄዳላችሁ፤ ለእኛ መጀመሪያ ቦታ ስጡን [ብለን ስንጠይቅ] ‘አልታዘዝንም’ አሉን” ሲሉ ነዋሪው ተናግረዋል።
“ትጥቅ ማውረድ ከሆነ ሁሉም ነው ማውረድ ያለበት እንጂ አንዱ ታጣቂ አንዱ ትጥቅ ፈቺ ለምን ይሆናል? እያቀራረባችሁን ሳይሆን እያራራቃችሁን ነው ብለን ስንጠይቅ ‘አይመለከታችሁም’ ይላሉ” ሲሉ ለስጋታቸው ዋስትና ማጣታቸውን ገልጸዋል።
“እንደዚህ አይነት መንግሥት አለ እንዴ?” ሲሉ የሚጠይቁት ነዋሪው፤ “እንዴት መኖር እንችላለን? ሲሉ ስጋታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የመሳሪያ ባለቤት እንዳልሆኑ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ የቤተሰቦቻቸው የጦር መሳሪያ መወሰዱን ጠቁመው “ወንድሞቼ ከተገፈፉ [መሳሪያቸው ከተወሰደ] የእኔ የመኖር ዋስትና አደጋ ላይ ነው” በማለት ከታጣቂዎች የሚሰነዘርን ጥቃት አሳሳቢነት ገልጸዋል።
- በአዲስ አበባ ከታህሳስ ጀምሮ የባንክ አካውንት ለመክፈት የ’ፋይዳ’ መታወቂያ ማቅረብ ግዴታ ሊሆን ነው2 ታህሳስ 2024
- በትግራይ ማኅሌት ተኽላይን አግቶ በመግደል ከተከሰሱት አንደኛው ሞት ተፈረደበት3 ታህሳስ 2024
- አቶ ታዬ ደንደአ በዋስ እንዲለቀቁ ተወሰነ2 ታህሳስ 2024
በአካባቢው ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ የአማራ ተወላጅ ነዋሪዎች “ተለይተው” መሳሪያ እንዲያስረክቡ መጠየቃቸውን ተከትሎ ውጥረት መፈጠሩን ተናግረዋል።
ለደኅንነታቸው በመስጋት መሳሪያቸውን አናስረክብም ያሉ ነዋሪዎችም ቤታቸውን ጥለው ጫካ መግባታቸውን ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።
በአካባቢው የተሰማራው መከላከያ ሠራዊት አዛዦች ቤተ ክርስቲያን ላይ ሕዝቡን “በምክክር ይሆናል” በሚል እንዲረጋጉ እና ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ መተማመኛ መስጠታቸውን ተከትሎ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሱን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
“‘ተስማምታችሁ፤ ታርቃችሁ በጋራ መኖር አለባችሁ ነው ያልነው እንጂ መሳሪያ አስገቡ፤ ትጥቅ ፍቱ ያለ አካል የለም’” በሚል ከመከላከያ ሠራዊት እንደተነገራቸው የገለጹ አንድ ነዋሪ “አርሶ አደር እንጂ ሽፍታ አይደለንም” ብለን ተመለስን ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“‘ሰላም ከሆነ አታወርዱም፤ ባለጌ ካለ ባለጌውን እንለቅማለን’ አሉን። ባለጌውን [ወንጀል የሚፈጽመውን] እኛ ሙልጭ አድርገን አጠፋን። የሚያዘውን አስያዝን፤ የማይያዘውን አባረርን” ሲሉ አካባቢው ከውጥረቱ በኋላ ተረጋግቶ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ሆኖም ባለፈው ሰኞ የመንግሥት ኃይሎች “አዘናግተው” መሳሪያ መንጠቃቸውን ተከትሎ ውጥረቱ እና ስጋቱ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።
“መከላከያ ሲወጣ ሸኔም ይመጣል. . . ። የተደራጀ ጥቃቱን መልሶ ይፈጽማል” ሲሉ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ጥቃቶችን ዋቢ አድርገው “ከባድ ስጋት” ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“ሕዝቡ እንዴት አድርገን አዝመራ እንሰብስብ? እንዴት እንሁን? እንዴት እናድርግ? በማለት መልሶ [ዳግም] ውጥረት ውስጥ ነው” በማለት ማኅበረሰቡ ያለበትን ሁኔታ ገልጸዋል።
በስጋት ምክንያት ቤታቸውን ለቀው የሸሹ ነዋሪዎች እንዳሉ የተናገሩ ሌላ ነዋሪ ደግሞ፤ “ከዛሬ ነገ ምን ይፈጠር ይሆን?” የሚለውን እያጤኑ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በአካባቢው የኖሩ ሌላ ነዋሪ ስጋቱን ሲገልጹ “የጊዜ ጉዳይ ነው” በማለት ደኅንነታቸው አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
የአካባቢ ሚሊሻ ሆነው ማገልግላቸውን የተናገሩ ሌላ ነዋሪ ያሉበትን ሁኔታ ሲገልጹ “በረት የገባ ከብት ማለት ነን” ሲሉ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ እና ሸኔ ከሚባሉት ታጣቂዎች ባለፈ ሌሎች ኃይሎችም እንደሚያሰጓቸው ተናግረዋል።
ቢቢሲ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች እና የመከላከያ ሠራዊት አዛዦችን ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳከም።
ሆኖም የአንዶዲ ዲቾ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ሂርኪሳ መኮንን የመሳሪያ ነጠቃውን ሳይጠቅሱ “ሕዝቡ በሰላም እየኖረ ነው” በማለት ማኅበረሰቡ ያደረበትን ስጋት አጣጥለዋል።
ትጥቅ ማስፈታትን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ የአካባቢ ሚሊሻዎች ብቻ መሳሪያ እንደሚታጠቁ እና ከዚህ ውጪ በክልሉ ውስጥ መሳሪያ ታጥቆ መገኘት እንደሚያስጠይቅ በመግለጽ መሳሪያ ማስፈታቱ ወገን ሳይለይ የሚፈጸም መሆኑን ለመገናኛ ብዙኃን መናገራቸው ይታወሳል።
የደኅንነት ስጋት አለባቸው በተባሉት በእነዚህ አካባቢዎች ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ የኦሮሞ ተወላጆች በሕጋዊ መንገድ የታጠቁት ጦር መሳርያ “ሸኔ እጅ ይገባል በሚል” ስጋት በመንግሥት መሰብሰቡን ይናገራሉ።
የአማራ ተወላጆች ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚፈጸም ጥቃት ከሚደርስባቸው ጉዳት እና ካለባቸው የፀጥታ ችግር ጋር በሚመሳሰል፣ የኦሮሞ ተወላጆች ድንበር ተሻግረው ጥቃት ይፈጽማሉ በሚባሉ የፋኖ ታጣቂዎች ምክንያት ግድያ እና መፈናቀል እንደደረሰባቸው ይናገራሉ።