
ከ 9 ሰአት በፊት
አገራቸው በወታደራዊ ዕዝ ስር እንድትሆን ያወጁት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ የዎል ላይ ክስ የመመሥረት ሂደት ፓርላማው ጀመረ ።
የደቡብ ኮሪያ ፓርላማ አባላት በአስቸኳይ የፕሬዝዳንቱን ድንጋጌ ከሻሩ በኋላ ፕሬዚዳንቱ ውሳኔያቸውን ለመቀልበስ ተገደው ነበር።
ፕሬዚዳንቱ ወታደራዊ ሕግን ለመደንገግ ካደረጉት ያልተሳካ ሙከራ ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ሕግ አውጪዎች ክስ ለመመሥረት ሂደት ጀምረዋል።
የደቡብ ኮሪያ ዋና ተቃዋሚ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ክሱን ካቀረበ በኋላ የፕሬዚዳንቱን ወታደራዊ ሕግ “የአመጽ ባህሪ” ሲል አውግዞታል።
ፓርላማው በፕሬዚዳንቱ ላይ ክስ ይመሥረት በሚለው ላይ ቅዳሜ፣ ኅዳር 28/2017 ዓ.ም. ውሳኔ ይሰጣል።
ደቡብ ኮሪያ በወታደራዊ ሕግ (ማርሻል ሎው) ስር እንድትሆን የታወጀው የፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ በፓርላማ አባላት ታግዷል።
ሕጉ መታገዱን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ አወዛጋቢ የተባለውን ሕግ ለማንሳት ተገደዋል።
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ዲሞክራሲ በሰፈነባት አገራቸው በወታደራዊ ሕግ (ማርሻል ሎው) ስር እንድትሆን በድንገት ማክሰኞ፣ ኅዳር 24/2017 ዓ.ም. ማወጃቸው አገሪቱን ያስደነገጠ ክስተት ሆኗል።
ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ የዎል አገሪቱ በአምስት አስርት ዓመታት አይታው የማታውቀውን ይህንን አስደንጋጭ ውሳኔ ለመወሰን ምክንያታቸው “ፀረ መንግሥት ኃይሎች” እና የሰሜን ኮሪያን ስጋት በመጥቀስ ነው።
ፕሬዚዳንቱ ከሰሜን ኮሪያ ኮሚኒስት ኃይሎች አገራቸውን ለመጠበቅ ወታደራዊ ሕጉ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናገሩ።
ነገር ግን ወታደራዊ ሕጉ በታወጀ ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፓርላማ አባላቱ ፕሬዚዳንቱን ተቃውመው በምክር ቤት ከተሰበሰቡ በኋላ አስቸኳይ ድምጽ በመስጠት ውሳኔውን አግደዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ሕግ እንዲያውጁ ምክንያት የሆናቸው እሳቸው እንዳሉት የውጭ ኃይሎች ስጋት ሳይሆን ውስጣዊ የፖለቲካ ችግሮች እንደሆኑ ግልጽ የሆነው ብዙም ሳይቆይ ነበር።
በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ኮሪያውያን ውሳኔውን በጽኑ ተቃውመው ወደ ፓርላማ አምርተው ነበር። አንዳንዶች የሕንጻውን አጥር ጥሰው በመግባት እንዲሁም በአጥሮች ላይ ተንጠላጥለው ወደ ፓርላማው ለመግባት ሲሞክሩ ታይተዋል። በተቃዋሚዎች እና በፖሊሶች መካከል ግጭት መፈጠሩ ተዘግቧል።
- የክሪስታል ፓላሱ አምበል የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ባንዲራ ላይ ‘እየሱስን እወደዋለሁ’ ብሎ መፃፉ አነጋጋሪ ሆነ4 ታህሳስ 2024
- ትራምፕ ኤፍቢአይን እንዲመሩ ያጯቸው አወዛጋቢው ዳይሬክተር መሥሪያ ቤቱን ይዘጉት ይሆን?4 ታህሳስ 2024
- በዘመናዊው ዓለም አምስት ተፈላጊ ሥራዎች እና ስኬታማ ለመሆን የሚያግዙ ክህሎቶች4 ታህሳስ 2024
ውሳኔያቸው በፓርላማ አባላት የታገደባቸው ፕሬዚዳንት ዩን የምክር ቤቱን ድምጽ ተቀብያለሁ እንዲሁም ሕጉን አንስቻለሁ ለማለት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ብቅ ብለዋል።
በአገሪቱ ወታደራዊ አገዛዝ በድንገት መጀመሩን ተቃውመው ከፓርላማ ውጭ ተሰባስበው የነበሩ ሰልፈኞች ሕጉ እንደገና በአጭር ጊዜ መቀልበሱን በማስመልከት ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን እንዲነሱ ተቃዋሚዎች እና የፓርላማ አባላት ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንቱ በአሁኑ ወቅት ከሥልጣናቸው ሊነሱ አልፎ ተርፎም ከፓርቲያቸው ሊባረሩ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ተነግሯል።
ወታደራዊ ሕግ (ማርሻል ሎው) የሲቪል ባለሥልጣናት ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደማይችሉ በሚቆጠርበት ጊዜ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲመሩ የሚደረግበት ጊዜያዊ አገዛዝ ነው።
አንዲት አገር በወታደራዊ ሕግ ስር በምትሆንበት ወቅት የሲቪል መብቶች መታደግ እንዲሁም ወታደራዊ ሕጉ ሊራዘም የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል።
በደቡብ ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ወታደራዊ ሕግ የታወጀው በአውሮፓውያኑ 1979 ሲሆን፣ ወቅቱም አገሪቱን ለበርካታ ዘመናት የገዙት አምባገነኑ ፖርከ ቹንግ ሂ በመፈንቅለ መንግሥት መገደላቸውን ተከትሎ ነው።