

በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሾሙት አዲሱ የመቀሌ ከንቲባ አቶ ብርሃነ ገብረ እየሱስ
ዜና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ሹመት ውዝግብ አስነሳ
ቀን: December 4, 2024
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ብርሃነ ገብረ ኢየሱስን አዲሱ የመቀሌ ከንቲባ አድርጎ በመሾም ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ሥራ ቢያስጀምርም፣ ሹመቱ በሁለቱ የሕውሓት ክንፎች መካከል ውዝግብ አስነሳ፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ጊዜያዊ አስተዳደሩ የከንቲባውን ሹመት ይፋ ያደረገው በፖሊስ የምክር ቤቱን ቁልፍ ሰብሮ በመግባት እንደሆነ ቢገልጹም፣ በሌላ በኩል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለተሿሚው በአመራሮችና በሠራተኞች አቀባበል እንደተደረገላቸው አስታውቋል።
ማክሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. አመሻሽ በመቀሌ ከተማ ምክር ቤት አስተባባሪ ቋሚ ኮሚቴ ማኅተም በወጣ የአቋም መግለጫ ደብዳቤ ደግሞ፣ ‹‹በ23/03/2017 ዓ.ም. በመቀሌ ምክር ቤት የተሾሙት ምክትል የከንቲባነት ሥራቸውን እየሠሩ እያለ የፖሊስ ኃይሎች የሕዝቡንና የምክር ቤቱን ሉዓላዊነት በመጣስ ወደ ጽሕፈት ቤቱ በመግባትና አገልግሎት እንዳይሰጥ ሲያግዱ፣ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ሕጋዊ ያልሆነ ከንቲባ እንዲገባና በአዳራሽ መግለጫ እንዲሰጥ አድርገዋል። የመቀሌ ከተማ ፖሊስ በሕጋዊ መንገድ የተሾመው እንዳይገባ በማድረግና ጽሕፈት ቤቱን በማሸግ እስካሁን ሕዝብ አገልግሎት እንዳያገኝ አድርጓል። ሕዝቡንም ወደ አላስፈላጊ መጨናነቅና መረበሽ እንዲገባ አድርጎታል፤›› ብሏል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የከንቲባውን ሹመት ለሕዝብ የገለጸው በሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው የፓርቲው ክንፍ ተቀባይነት የቸረው የከተማው ምክር ቤት፣ 34ኛ መደበኛ ጉባዔውን ከመስከረም 28 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም በማካሄድ፣ ረዳዒ በርሄ (ዶ/ር)ን ምክትል ከንቲባ አድርጎ መሾሙን ይፋ ካደረገ ከሁለት ወራት በኋላ ነው።
የረዳዒ በርሄ (ዶ/ር) ሹመት ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ምክር ቤቱ ባካሄደው አራተኛ ዘመን ስምንተኛ አስቸኳይ ጉባዔ ላይ ይፋ ሲደረግ፣ ሹመቱ የክልሉን ሕገ መንግሥት የተከተለና ተቀባይነት ያለው ነው ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።
በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው የፓርቲው ክንፍ በወቅቱ ይፋ ባደረገው መረጃ የከተማው ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ራህማ አብዱልቃድር መሐመድ ለምክር ቤቱ አባላት ረዳዒ (ዶ/ር) በምክትል ከንቲባነት የተሾሙት በ34ኛው መደበኛ ጉባዔ መሆኑን፣ ምክር ቤቱ በሰጣቸው ሹመት መሠረት ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት የላቸውም ሲሉ መናገራቸውን ገልጾ ነበር።
ይህንን ተከትሎም ኅዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም. የዚሁ ሕወሓት ክንፍ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹ብዙ ሰዎች ስለምክር ቤቶች የሚመለከተው የፌዴራል ሕገ መንግሥት ብቻ ነው ብለው ያስባሉ። ክልሎችም የራሳቸው ሕገ መንግሥት አላቸው። የትግራይ ሕገ መንግሥት የዞን ምክር ቤቶች ራሳቸውን የቻሉ አስተዳደሮች መሆናቸውን በግልጽ ይደነግጋል፤›› ብለዋል።
‹‹የትግራይ ሕገ መንግሥት ከአንቀጽ 71 እስከ 96 ስለጣቢያና ስለወረዳ ምክር ቤቶችን ይደነግጋል። ለክልሉ የተሰጡ ግልጽ ሥልጣኖች አሉ። የወረዳው የበላይ ሥልጣን የምክር ቤቱ ነው። ምክንያቱም ሥልጣን የሕዝብ ነው፣ የሚሠራውም በውክልና ነው። ሌሎች የካቢኔ አባላት በምክር ቤቱ ይሾማሉ፣ ከደረጃ ዝቅ ተደርገው ይወሰዳሉ ወይም ይባረራሉ። የወረዳውን አስተዳዳሪ ጨምሮ እነሱ ለምክር ቤቱ ተጠሪ ናቸው፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
ይሁንና የሌላው የሕወሓት ክንፍ መሪ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በሁለቱም ቡድኖች የሚያደረጉትን ሹመቶች በሚመለከት ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚሰጣቸውን ሹመቶች ወደ ጎን በመግፋት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በሚመሩት ሕወሓት የሚሾሙ ሰዎች ተቀባይነት እንደሌላቸውና ይህ አካሄድ ከዚህ በኋላ አይቀጥልም ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እሑድ ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በመቀሌ ከተማ ከወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በአጠቃላይ የክልሉን ሁኔታ በተመለከተ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹ቡድኑ›› ሲሉ የጠሩት በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራውን የሕወሓት ክንፍ፣ ‹‹የትግራይን ሕዝብ አጀንዳ ማዕከል አድርጎ ከመንቀሳቀስ ይልቅ የሥልጣን ሽኩቻና የሙስና ተግባር ውስጥ ተዘፍቋል፤›› ብለውታል።
አቶ ጌታቸው በማብራሪያቸው፣ ‹‹በሹመት ላይ ሌላ ሹመት መፈጸም፣ እንዲሁም የሐሳብ ልዩነት ያላቸውን ሰዎች የማፈን ድርጊት እንዳይቀጥል የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሰኞ ዕለት በይፋ ኃላፊነት መረከባቸው የተገለጸው የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ብርሃነ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹መንግሥት አፍርሶ የሚቋቋም አዲስ መንግሥት የለም፤›› ብለዋል።
አቶ ጌታቸውም ቀደም ብሎ ከወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይት የወጣቶችን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ማሰርና ማስፈራራት፣ እንዲሁም ሁሉንም ችግሮች የጊዜያዊ አስተዳደሩ ክፍተቶች እንደሆኑ አድርጎ ስም የማጥፋት ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል በማለት ወቀሳ አሰምተዋል፡፡
‹‹በዞንና በወረዳ መዋቅሮች የተመደቡና የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሹመቶች የሚቃወሙ አመራሮች በድሬዳዋ፣ በሐዋሳና በሌሎችም ከተሞች በሚዘጋጁ አበል የሚከፈልባቸው ስብሰባዎች፣ ‹‹ከመድረኩ አዘጋጆች ቀድመው ነው የሚገኙት፤›› ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ የሁሉም ወገኖች ትኩረት መሆን የሚገባው ተጠያቂነትን ማስፈንና የሕዝብን አጀንዳዎች ማራመድ ላይ ነበር ሲሉም አስረድተዋል፡፡
‹‹የትግራይ ትንታግ ትውልድ›› በሚል ተደራጀ ስለሚባለው ቡድንም የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹መሰል ቡድኖች የሚደራጁበት መንገድ ቢታወቅም፣ ትንታግም ሆነ ሌላ ወጣቱ ድምፁን የሚያሰማበት መንገድ ሊመቻች ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል በአቶ ጌታቸው የሚመራው ቡድን፣ ‹‹ወጣቶችን ለሁከትና ለብጥብጥ እያደራጀ ነው፤›› ማለታቸው ይታወሳል።