

December 4, 2024
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ
የካፒታል ወይም የሊዝ ዕቃዎች ፋይናንስ ዘርፍ ተቋማት ካለፉት አምስት ዓመታት በሦስቱ ኪሳራ ማስመዝገባቸውን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት ሪፖርቱ ይፋ አደረገ፡፡
በ2016 የሒሳብ ዓመት ከትርፍ ግኝት አኳያ የሊዝ ፋይናንስ ዘርፉ ከፍተኛ የሚባል ኪሳራ ላይ መውደቁ ተገልጾ፣ ለዚህም ዋነኛ መንስዔው በመፍረስ ላይ ባለ አንድ የግል ኩባንያ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ከካፒታልና ሀብት ትርፍ ጋር በተገናኘ የሊዝ ፋይናንስ ዘርፉ ባለፉት ዓመታት ምንም ያልተገኘበት (ዜሮ) እንደነበር የሚገልጽ አስረጅ ያቀረበው ሪፖርቱ፣ በተለይ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከካፒታል ትርፍ ጋር በተገናኘ የተመዘገበው ኪሳራ 15 በመቶ፣ እንዲሁም የሀብት ትርፍ ውጤቱ 5.3 በመቶ ኪሳራ የተመዘገበበት እንደሆነ ያሳያል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ ካሉት የሊዝ ፋይናንስ ኩባንያዎች ውጪ ሌሎች ኩባንያዎች ዘርፉን አለመቀላቀላቸው ተጠቅሶ፣ ያሉትም ኩባንያዎች ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ሳይጨምሩ ባሉበት መቀጠላቸው ተመላክቷል፡፡
በዚህም ምክንያት ዘርፉ ከመዋቅራዊ ችግሮች ባሻገር ለአገልግሎቱ ዘላቂነት ከፍተኛ ሥጋት ያለበት እንደሆነ አመላካችነቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ወደ ትርፋማነት እንዲያመራ የሚያስችል የፖሊሲ ዕርምጃዎች ያስፈልጋሉ ብሏል፡፡
ብሔራዊ ባንክ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ እንደቀረበው የሊዝ ፋይናንስ ዘርፉ እ.ኤ.አ. በ2020 እና 2023 ከታክስ በፊት 8.3 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም 28.6 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን በአንፃሩ እ.ኤ.አ. በ2021 አንድ ሚሊዮን ብር፣ በ2022 17.5 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም በ2023 የ343 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዝግቧል፡፡ በጥቅሉ ባለፉት አምስት ዓመታት የ1.2 ቢሊዮን ብር ኪሳራ መመዝገቡ ተገልጿል፡፡
ከላይ የተገለጹት አፈጻጸሞች እንደተጠበቁ ሆነው ለካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ተቋማት የሚያቀርቡት ብድር የ35.3 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ለአብነትም የልማት ባንክ የሚያቀርበው የሊዝ ፋይናንስን ጨምሮ ከ3.7 ቢሊዮን ብር በላይ መቅረቡ ተብራርቷል፡፡ ይህ አኃዝ ካቻምና 2.8 ቢሊዮን እንደነበር ሪፖርቱ አክሏል፡፡
ለካፒታል ዕቃዎች ከፋይናንስ ተቋማት ተቀማጭ ገንዘብ የማይቀበሉ በአብዛኛው የፋይናንስ ምንጫቸው በባንኮች ላይ ጥገኛ በመሆናቸው፣ በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ የሚፈጠሩ ሥጋቶች በእነሱ ላይ ጥላ እንዲያጠላ የሚያደርግባቸው እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ የፋይናንስ ምንጮችን የማግኘት ችግር፣ በብድር ላይ ከፍተኛ ጥገኛ መሆን ዘርፉ የአገልግሎት አድማሱን እንዳያሰፋ እንቅፋት ሆኖበታል ተብሏል፡፡
ግብርና ከካፒታል ፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ ድርሻ የሚወስድ መሆኑን፣ በ2016 የሒሳብ ዓመት 68 በመቶ የሚሆነውን የካፒታል ፋይናንስ መውሰዱ ተጠቁሟል፡፡ የአገልግሎት ዘርፍ 13.5 በመቶ፣ ኮንስትራክሽን 9.1 በመቶ ሲወስዱ በግብርና ላይ የተሰማሩ ደንበኞች የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ ብድር እንደቀረበላቸው ተነግሯል፡፡
ሌላው በብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ዕመርታ አስመዝግቧል የተባለው የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ሲሆን፣ በተለይም በ2016 የሒሳብ ዓመት የተረጋጋና ዕድገት የተመዘገበበት ሪፖርት አስመዝግቧል ተብሏል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የዘርፉ አጠቃላይ ሀብት 21.6 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ መሆኑን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ከነበረው 49.4 ቢሊዮን ብር ወደ 60.1 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመላክቷል፡፡