

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ለመስጠት በተገኙበት ወቅት
ዜና የንግድ ሚኒስትሩ የዋጋ ግሽበቱ ቋሚ ገቢ ያላችው ዜጎች ላይ ጠንካራ ክንዱን አሳርፏል…
ቀን: December 4, 2024
- ‹‹የንግድ ሥርዓቱ እንደ ተባይ ተወሯል›› የምክር ቤት አባል
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ግሽበት፣ ቋሚ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጠንከር ያለ ክንዱን አሳርፏል ሲሉ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ባደረገው ስምንተኛ መደበኛ ሰብሳቢው፣ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነው፡፡
አቶ አበራ አዳሙ የተባሉ የምክር ቤት አባል የሸቀጦች ዋጋ የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው መሆኑን፣ በምክንያት የለሽ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት የሕዝቡ ኑሮ እየተመሰቃቀለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረቱ እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ምስር፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በጥራትም ሆነ በብዛት ገበያ ውስጥ እንደማይገኙ፣ ቢገኙም ዋጋቸው እጅግ የተጋነነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አክለውም የችግሩ ምንጭ ሕጋዊው ነጋዴ በሕገወጦችና በደላላ እየተጠለፉ ሕጋዊ ሥራ መሥራት የማይችልበት ደረጃ በመድረሱ ነው ብለዋል፡፡
‹‹በዚህም የተነሳ ልጆቼን የማበላቸው አጣሁ የሚሉ አዛውንቶች፣ አባዬ ቁራሽ ዳቦ መግዣ ስጠኝ ራበኝ የሚሉና አንጀት የሚበሉ ሕፃናትን ማየት በከተማው እየተለመደ መጥቷል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹በአጭር አነጋገር ደላላ የንግዱን ሥርዓትቱን እንደ ተባይ ወሮታል፣ በዚህም ምክንያት የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አቅቶት ኅብረተሰቡ መድረሻ እያጣ ነው፤›› ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ‹‹ሕገወጥ ነጋዴዎችንና›› ደላላዎችን ሥርዓት ሊያስይዝ የሚችል ዘላቂነት ያለው ሥራ ከመሥራት ይልቅ፣ አልፎ አልፎ ወይም የሆነ አጋጣሚ ሲፈጠር ይህን ያህል የንግድ ድርጅቶችን አሽጌያለሁ፣ ወይም ላሽግ ነው እያሉ በመገኛኛ ብዙኃን ማስታወቂያዎችን ከማስተጋባት የዘለለ የንግድ ተቋማት በምን ምክንያት እንደታሸጉ፣ ምን ዓይነት ሕጋዊ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው፣ የማሸጉ ዕርምጃ ምን ውጤት እንዳስገኘና የንግድ ድርጅቶች ከታሸጉ በኋላ የመጣውን ለውጥ ለሕዝብ ሲያሳውቅ አይሰማም፡፡ በኑሮ ላይም ጠብ የሚል ውጤትም አይታይም፡፡ ታዲያ የአገሪቱን ገበያ እየመራ ያለው ንግድ ሚኒስቴር ነው ወይስ ደላላና ሕገወጥ ነጋዴ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ወ/ሮ እታፈራሁ ሞቴ የተባሉ የምክር ቤት አባል ባለፉት ዓመታት የዋጋ ግሽበቱ እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው ዘይት፣ ስኳርና የግንባታ ዕቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ የዜጎችን ሕይወት እጅግ እየፈተነው ነው ብለዋል፡፡
ምርት በማከማቸት ዋጋ እንዲንር ምክንያት የሚሆኑና በሸማችና በአምራች መካከል እየገቡ የኑሮ ውድነት የሚያስከትሉ ነጋዴዎች ላይ በቂ ዕርምጃ እየተወሰደ አይደለም ያሉት ወ/ሮ እታፈራሁ፣ ‹‹በአገራችን እያየለ ያለው የኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኝ ከቀጠለ፣ አገሪቱን ውስብስብ ወደ ሆነ ችግር ሊያመራት ስለሚችል ሚኒስቴሩ ምን አቅዶ እየሠራ ነው›› ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ወ/ሮ ሐረገወይን ይመር የተባሉ የምክር ቤት አባል በሰጡት አስተያየት መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምና የተለያዩ የመፍትሔ ዕርምጃዎች እየወሰደ ቢሆንም፣ የሚታሰበውን ያህል የኑሮ ውድነቱን ማስተካከልና የሸቀጦችን ዋጋ ውድነት ማስተካከል አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ በተለይም በቀጥታ ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ እህሎችና ሸቀጦች ላይ በየጊዜው እያደገ የሚሄደው ምክንያት አልባ የዋጋ ጭማሪ፣ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮውን መሸከም ከማይችልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል ብለዋል፡፡
ነጋዴው ከመሬት ተነስቶ ዋጋ ሲጨምር ለምን ተብሎ እየተጠየቀ አለመሆኑንና ዕርምጃ አለመውሰዱን ጠቁመው፣ በዚህም የተነሳ የሸቀጦች ዋጋ እየተሰቀለና እየጨመረ በመሆኑ ከፍተኛ የኑሮ ቀውስ ፈጥሯል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ሚኒስትሩ ካሳሁን (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ በአምስት ወራት ውስጥ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከ105 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል፡፡ የተወሰደው ሕጋዊ ዕርምጃ ባለፉት አሥር ዓመታት ተወስዶ አንደማያውቅ ገልጸው፣ ‹‹በዚህ ጉዳይ ልንታማ አንችልም፤›› ሲሉ ለፓርላማው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባቄላና ሰሊጥ በማምረት ከዓለም ሁለተኛ፣ በምስር ከዓለም ስድስተኛ፣ በስንዴ በአፍሪካ ቀዳሚ አምራች መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሩ በብዙ ምርቶች ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር ነች ብለዋል፡፡
የጫት ምርትን በተመለከተ በፌደራልም ሆነ በክልል መንግሥታት አምራች አርሶ አደሮች ገቢያቸው ማደግ ይገባል የሚሉ እንዳሉ፣ በየፌደራል መንግሥት ፍላጎት ደግሞ የጫት የውጭ ገበያ ግኝትን የማሳደግ ፍላጎት መኖሩን፣ በክልሎች ደግሞ ኬላ ወጥረን ከጫት ቁርጥ ገቢ ማግኘት አለብን የሚሉ ሦስት ዓይነት ዕሳቤዎች መኖራቸውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ሦስቱ ፍላጎቶች እርስ በእርስ የሚገፋፉ በመሆናቸው ጫት አገሪቱ ከጫት ወጪ ንግድ ማግኘት የነበረባትን እያገኘች አይደለም ብለዋል፡፡
ክልሎች በጫት ላይ ቀረጥ መጣል ከጀመሩበት ጥቅምት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ አገሪቱ የምታገኘው የውጭ ገበያ ግኝት ማሽቆልቆል መጀመሩን፣ በሶማሊያ ከሁለት ዓመት በፊት የመንግሥት ለውጥ ሳይደረግ የኢትዮጵያ ጫት ብቻ ሞቃዲሾ ይገባ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ባለው መንግሥት የኬንያ ጫት እንዲገባ በመወሰኑ የጫት ገቢ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በጫት ላይ የተጣለው ቀረጥ ከፍተኛ ስለሆነና ነጋዴው ዋጋውን ወደ አርሶ አደሩ ስለሚያሸጋግር፣ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እየሆነ አይደለም ብለዋል፡፡
የቀረጥና የኬላ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ካሳሁን (ዶ/ር) እስከ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ኬላ ይነሳ ተብሎ በመንግሥት ደረጃ ቢወሰንም፣ በተለያዩ ሰበቦች 283 ሕገወጥ ኬላዎች በመላ አገሪቱ ተንሰራፍተው ይገኛሉ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ኬላዎቹ የምርት ነፃ ዝውውርንና የትራንስፖርት ፍጥነትን የሚገድና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ያላቸው መሆናቸውን በመረዳት፣ ፓርላማው ራሱ ትግል እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቃቸውን ጠቅሰው፣ ዕርምጃ ይወስዳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ኬላ ካልተነሳ የሸቀጦችን የዋጋ ግሽበት መቀነስ አይቻልም ብለዋል፡፡
የአገሪቱን ንግድ እየመራው ያለው ደላላ ወይስ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር፣ ሚኒስቴር ተብሎ ከአባላቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ፣ ‹‹እኔ እንደሚገባኝ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ እየመሰከረ ባለው መረጃ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ሥርዓቱን እየመራ በተገቢው ሁኔታ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አስረግጬ መናገር እችላለሁ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በፍራንኮ ቫሉታ ባለፉት አምስት ወራት ከ208 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይትና ከ1.3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር ለማቅረብ መቻሉን ጠቁመው፣ ነገር ግን የፍራንኮ ቫሉታ የውጭ ምንዛሪ መነሻው ጥቁር ገበያ ስለሆነና ማክሮ ኢኮኖሚ በማዛባት የተጀመረውን ሪፎርም ወደኋላ እንዳይቀለብሰው ታስቦ እንዲቆም መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
በአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና የሙከራ ንግድ ለመጀመር የታሪፍ መጽሐፍ እየታተመ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በጥቂት ወራት ውስጥ ከተመረጡ አገሮች ጋር የሙከራ ንግድ እንጀምራለን፤›› ብለዋል፡፡