
December 4, 2024

በታንዛኒያ ዛንዚባር ከአንድም ሁለት ጊዜ ከኦነግ ሸኔ ጋር አምና ድርድር ለማድረግ ሙከራ ቢደረግም፣ ነገር ግን በመጨረሻ ያለ ውጤት ነበር የተበተነው፡፡ ይሁን እንጂ ከአንድ ዓመት በኋላ እሑድ ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራሩ ከጃል ሰኚ ነጋሳ ጋር የሰላም ስምምነት መፈረሙ ተፈርሟል፡፡

ወደ ታንዛኒያ የሚደረግ የበረራ ወጪ ያልጠየቀው ከጃል ሰኚ ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት፣ ለረዥም ዘመን ላስቆጠረውና በኦሮሚያ ክልል ለቀጠለው ግጭትና ጦርነት ምን ፋይዳ ይዞ ይመጣል የሚለው ጉዳይ የወቅቱ ወሳኝ ጥያቄ ይመስላል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ቦሌ መንገድ ‹‹አፍሪካ ጎዳና›› በሚገኘው ጽሕፈት ቤታቸው ከጃል ሰኚ ጋር ስምምነቱን ሲፈርሙ፣ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ በባህልና በወጉ መሠረት በሬዎቹን ጠምዶና ፈረሶቹን ጭኖ በመውጣት ሰላም ይውረድ በማለቱ ጥሪውን ተቀብላችሁ በመምጣታችሁ በራሴና በክልሉ መንግሥት ስም አመሠግናለሁ፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ አቶ ሽመልስና ጃል ሰኚ በተፈራረሙበት የሰላም ስምምነት ሰነድ መሠረት፣ የኦሮሞ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ መግባትና ውሎ ማደር የሚችልበት ዕድል በኦሮሚያ ክልል ይፈጠራል ወይ የሚለው ጉዳይ በስፋት እያነጋገረ ነው፡፡
ከአቶ ሽመልስ ጋር ስምምነት ተፈራራሚው ጃል ሰኚ በበኩላቸው፣ ‹‹የሰው ልጅ የፖለቲካ ልዩነት ይኖረዋል፡፡ እኛም ያለንን የፖለቲካ ልዩነት በጠመንጃ ከመፍታት ይልቅ፣ በሰከነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ወስነን ነው ስምምነቱን የመረጥነው፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡
ጃል ሰኚ ይህን ቢሉም በኦሮሚያ ክልል ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት ለመፈራረም ቀርቶ ትኩስ ውጊያ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ታጣቂዎች አሁንም ድረስ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ጃል ሰኚ የሰላም ሰነዱ ላይ ቢፈርሙም እነ ጃል መሮና በርካታ ተዋጊዎች ከእነ ትጥቃቸው በኦሮሚያ ጫካዎች ውስጥ መገኘታቸው ሌላው የመነጋገሪያ ርዕስ ነው፡፡
ከጃል ሰኚ ጋር የተፈረመው የሰላም ስምምነት በአንዳንዶች በኦሮሚያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት ጥርጊያ መንገድ የሚከፍትና መልካም ጅምር ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ ቀስ በቀስ ወይም ተራ በተራ በጉጂ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በምሥራቅ ሸዋና በወለጋ የሚንቀሳቀሱ የኦነግ ነፃነት ሠራዊት ክንፎች አመራሮች ወደ ድርድርና ወደ ስምምነት የሚገቡ ከሆነ የአሁኑ ጅምር በር ከፋች ሊባል የሚችል እንደሆነ ይገምታሉ፡፡
ይሁን እንጂ በዚያው ልክ ስምምነት ተብሎ ከጃል ሰኚ ጋር የተካሄው የፊርማ ሥነ ሥርዓት በበርካቶች ዘንድ ቀቢፀ ተስፋ ያሳደረም ነው፡፡ የሰላም ስምምነቱ የምር የሰላም ስምምነት ከሆነ ግልጽነት ባለው ሁኔታ የስምምነት ነጥቦቹ ይፋ መሆን ነበረባቸው የሚሉ አሉ፡፡ የስምምነት ሰነዱም ቢሆን በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ለሕዝብ ይፋ መሆን እንዳለበትም ይጠቅሳሉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ነው የተስማማነው ብሎ ለሕዝብ የስምምነቱን ሒደትና ነጥቦች ግልጽ ማድረጉ መልሶ ራሳቸውን ተፈራራሚ ወገኖችን እንደሚጠቅም አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻ ተፈራራሚዎቹ መስማማት ሳይችሉ ቀርተው ስምምነቱ ቢፈርስ እንኳ፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥም ቢሆን ግልጽነትን የተከተለ ስምምነት ማሰሩ እንደሚበጅ ያሳሰቡ አሉ፡፡
‹‹ሰው ሠርግ የሚደግሰው እኮ ወጪውን ወዶና መክሰር ፈልጎ አይደለም፡፡ ሰው የሚሠርገው እኮ ጥሪቱን አሟጦ የሌሎችን ሆድ ለመሙላትና ጨፍሩልኙ ለማለት አይደለም፡፡ ሰው ሠርግ የሚያደርገው ዕወቁልኝ እከሌን አግብቼያለሁ ብሎ ለማወጅ ነው፡፡ ሰው ለሠርግ ብዙ የሚያወጣው ምስክር ሁኑኝ ብሎ ለማኅበረሰቡ ቤተሰብ መመሥረቱን ለማሳወቅ ነው፤›› ሲሉ ነበር አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ፖለቲከኛ የተናገሩት፡፡ ስለስምምነቱ ከዚህ ጋር አያይዘው ሲያነሱም የምር ስምምነት ከሆነ በግልጽ የአገር ውስጥም የውጭም ሚዲያዎች ተጠርተው፣ አሸማጋዮችና ምስክሮች ባሉበት በግልጽ ሊታወጅ የሚገባው ጉዳይ መሆን እንደነበረበት ጠቁመዋል፡፡
የማዕከላዊ ዞን የኦነግ ሸኔ የጦር አዛዥ እንደነበሩ የተነገረው ጃል ሰኚ በመስከረም ወር ከኦነግ ጠቅላይ የጦር አዛዥ ጃል መሮ (ኩምሳ ድሪባ) ዕዝ መነጠላቸውን ተናግረው ነበር፡፡ ግለሰቡ ለሰላም ዝግጁ መሆናቸውንም በወቅቱ የተናገሩ ሲሆን፣ ብዙም ሳይዘገይ ከሰሞኑ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር ስምምነት መፈራረማቸው ይፋ ሆኗል፡፡
ታዋቂው ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ የስምምነት መርሐ ግብሩን በተመለከተ በኤክስ (ትዊተር) ገጹ በእንግሊዝኛ ባስነበበው ጽሑፍ ጠለቅ ያሉ ጉዳዮችን አስፍሯል፡፡ በግንቦት 2016 ዓ.ም. ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊ (ኦነግ ሸኔ) አባልነት የተገነጠለው በጃል ሰኚ የሚመራው ኃይል ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረሙን በመጥቀስ፣ ‹‹ጃል ሰኚ የራሱን ቡድን አደራጅቶ የቀድሞ አጋሮቹን ከመውጋት ይልቅ ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረሙ ሊደነቅ ይገባል፤›› ብሏል፡፡
ይሁን እንጂ ነገሩ ከኦነግ ሸኔ ጋር የተደረገ የሰላም ስምምነት ወይም በኦሮሚያ የሰፈነውን የእርስ በርስ ጦርነት የሚፈታ ተደርጎ መቅረብ እንደሌለበት ጃዋር ይገልጻል፡፡ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ስምምነትን የታከኩ የፖለቲካ ልምዶች ግጭትን ለመፍታት ያበረከቱት አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የማይባሉ እንደነበርም ያስታውሳል፡፡
‹‹በ2010 ዓ.ም. የኦነግ ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳን አስመራ በማግኘት ስምምነት በመፈራረም ጦሩን ይዞ እንዲገባና ለመንግሥት ትጥቅ በማስረከብ ወደ ማሠልጠኛ ገብተው የተሃድሶ ሥልጠና እንዲወስዱ ለማድረግ ቢሞከርም፣ ነገር ግን መንግሥት ሒደቱን በአግባቡ መምራት ባለመቻሉ ወደ ተሃድሶ ሥልጠና ገብተው የነበሩ ዳግም ወደ ጫካ ተበትነው የጃል መሮ (ኩምሳ ድሪባ) ኃይልን ተቀላቅለው ወደ ጦርነት ሲመለሱ ነው የታየው፡፡ የጃል መሮ ምክትል ዲናሪ (ሁንዴ ደሬሳ) በዚህ ውጣ ውረድ ያለፈ ሰው ነው፡፡ ሒደቱም በዚያው ተሰናክሎ ነው የቀረው፡፡ ከዚያ ወዲህ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አድማሱን እያሰፋ፣ የተዋጊዎቹን ቁጥር እየጨመረና ራሱንም እያጠናከረ ነው የሄደው፡፡ በ2013 ዓ.ም. ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ደቡባዊ ዕዝ መሪ ጎሊቻ ዴንጌ እጁን ለመንግሥት የሰጠ ቢሆንም ነገር ግን በደቡባዊ ኦሮሚያ ጥቃቱ ሲብስ ነው የታየው፡፡ ይባስ ብሎም ወደ አርሲና ባሌ ዞኖችም ሲዛመት ነው የታየው፤›› በማለት ነው ጃዋር የከዚህ ቀደም ስምምነቶችን ውጤት አልባነት የዘረዘረው፡፡ ከዚሁ በመንደርደርም ጃዋር የአሁኑ ሰላም ስምምነትም ቢሆን በኦሮሚያ ያለውን ግጭትና ቀውስ የማስቆም አቅም እንደሌለው ያስረዳል፡፡
‹‹ሲጀመር መንግሥት ከመፈራረም በዘለለ ለግጭት ምንጭ የሆኑ የሕዝቡን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ጥረት አላደረገም፡፡ ሁለተኛም መንግሥት በተደጋጋሚ ለሰላምና ለድርድር የገባቸውን ቃሎች ይጥሳል፡፡ የከዚህ ቀደም ልምዶችን ግምት ውስጥ በመክተት ዘላቂ ሰላም እንደማይፈጥር መገመት ይቻላል፤›› በማለት ነው ጃዋር ቀጥተኛ በሆነ አገላለጽ ብዙዎች የሚያስተጋቡትን ሐሳብ የጠቀሰው፡፡
ከሰሞኑ ከኦነግ ሸኔ የቀድሞ አመራር ጃል ሰኚ ጋር ከተደረገው የሰላም ስምምነት መፈረም ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አቀረቡት የተባለው የሰላም ጥሪም መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡
‹‹በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ለምትንቀሳቀሱ ሸማቂ ቡድኖች የሰላም ጥሪዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ለአንድ ሺሕ ዓመታት ብትዋጉ፣ ብትዘሉም ብትደክሙም እኛን አታሸንፉንም…›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
አንዳንዶች የሰላም ጥሪ የሚያቀርብ ሰው ለምን በዚህ መንገድ ጥሪውን ያቀርባል ሲሉ ንግግሩን ተቃውመውታል፡፡ ለአብነት ለቪኦኤ አማርኛ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ሙሉዓለም ተገኝወርቅ (ዶ/ር)፣ ሰላም ለማስፈን ቁርጠኝነት ያለው አካል በዚህ መንገድ ጥሪ እያቀርብም ብለዋል፡፡
‹‹ከንግግር ጀምሮ የምታሳያቸው ቅንነቶች ለሰላም ያለህን ቁርጠኝነት ያንፀባርቃሉ፡፡ ሀቀኛ የሆነ ሰላም የሚያመጣ ንግግር ማድረግን ይጠይቃል፡፡ የሰላም ጥሪ መቅረብ ያለበት ብቸኛው አማራጭ ሰላም መሆኑን በመገንዘብ እንጂ፣ ለአንድ ሺሕ ዓመታት ቢዋጋም የማያሸንፍ ቡድን ስላለ አይደለም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
ሌላው ለቪኦኤ አማርኛ አስተያየት የሰጡት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ባለፉት 50 ዓመታት ከፖለቲካ ቀውስ አዙሪት ኢትዮጵያ መላቀቅ አለመቻሏን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ከመገዳደል ፖለቲካ ወደ ድርድር ፖለቲካ አገሪቱን መምራት አልተቻለም፡፡ ፖለቲካችንን ለማሠልጠን በቁርጠኝነት መሥራት አልተቻለም፡፡ ብዙ ነገሮች መልካቸውን እየቀያየሩ ሲንከባለሉ ይታያል፡፡ ፖለቲካውን የሠለጠነ ለማድረግ በቁርጠኝነት አልተሠራም፡፡ መንግሥት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው ያጣው ፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት ብዙ ነገሮች መልካቸውን እየቀያየሩ ሲመላለሱ ነው የሚታየው፡፡ ሲንከባለሉ ነው የኖሩት፡፡ ዴሞክራሲ ብለን ጠመንጃ ይዘን ነው የምንወጣው፡፡ ሰላማዊ ፖለቲካና ድርድር ብለን እጅ ስጥ እጅ አትስጥ ወደ መባባል ነው የምንገባው፡፡ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ብለን ሌላ ጨዋታ ስንጫወት ነው የምንገኘው፤›› በማለት ነው ኢትዮጵያ ለረዥም ዘመን ከቀውስ አዙሪት ተላቃ እንደማታውቅ ያስረዱት፡፡ ይኸው የቀውስ አዙሪትም ዛሬ ድረስ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ባወጣው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎችን በዳሰሰ መግለጫውም መንግሥትን በከባዱ ወቅሷል፡፡
ከስድስት ዓመት በፊት ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበትን የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አብዮትን ጠልፎ ሥልጣን የተቆናጠጠ ሲል የኮነነውን መንግሥት፣ የተለያየ ብልጣ ብልጥ መንገድ እየተከተለ ነው ሲልም ይከሰዋል፡፡
‹‹በሰላም ሽፋን የትግል አመራሩን ለማማለል የሚያደርገው ጥረት ከንቱ ሆኖ ሲቀርበት ፊቱን ወደ አዲስ እኩይ ስትራቴጂ በመመለስ በሕዝባችን መካከል የጎንዮሽ ደም መፋሰስ ለመጠንሰስ አገዛዙ እየሞከረ ነው፤›› በማለት መግለጫው ገልጿል፡፡ የሃይማኖት ካርድን መጠቀም፣ የኦሮሞ መንግሥት ነኝ እያሉ ማወጅና ተቃዎሚዎች እጅ የሰጡ አስመስሎ ማቅረብ ከመንግሥት መጠቀሚያ ታክቲኮቹ መካከል እንደሚገኙም አክሏል፡፡ መንግሥት አሁን ‹‹በባዶ ዕብሪትና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይገኛል፤›› ሲል የደመደመው መግለጫው፣ ከሁሉ ቀድሞ የአገዛዙን አታላይ ባህሪ ማወቁን በመጠቆም ከትግል መስመሩ ፈቀቅ እንደማይልም አስታውቋል፡፡