
December 4, 2024

በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ኦዲት መሠረት የኢትዮጵያ የአየር ትራንስፖርት የደኅንነት ደረጃ 88.5 በመቶ መድረሱን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ይህንን ያስታወቀው 80ኛው የዓለም ሲቪል አቪዬሼን ድርጅት የምሥረታ በዓል የቺካጎ ኮንቬንሽን የተፈረመበትን ቀን መታሰቢያ በማድረግ ከኅዳር 30 እስከ ታኅሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ ኩነቶች ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስመልክቶ፣ ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ነው፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ እንደገለጹት፣ በዓለም የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ኦዲት መሠረት ኢትዮጵያ ደኅንነቱ የተረጋገጠ የአየር ትራንስፖርት ከሚሰጡ ጥቂት የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗ ተረጋግጧል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከአገሮች ጋር በሚያደርጋቸው ስምምነቶች መሠረት በአሁኑ ወቅት 141 መዳረሻ አገሮች እንዳሉ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በዚህም ምክንያት በአፍሪካ ውስጥ በርካታ መዳረሻ አገሮች ካላቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት ብለዋል፡፡
የአቪዬሸን ኢንዱስትሪው ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክት ብቻ ሳይሆን፣ ዋነኛው የአፍሪካ ማዕከል እንዲሆን እየተሠራ እንደሆነም አክለው ገልጸዋል፡፡
ይህ ሥራ አሁን ባለውና በነበረው ሁኔታ ብቻ መቀጠል የሚያስችል አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ወደፊት ዘርፉን ለማሳደግ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ የኢትዮጵያ አቪዬሸን ዘርፍ ለኢትዮጵያ ለባህል፣ ለቱሪዝም፣ ለንግድና ለኢንዱስትሪ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚበረክት መሆኑንና በአሁኑ ወቅት በዓመት 17 ሚሊዮን መንገደኞችና ከ750 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ዕቃ የማመላለስ አቅም መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ከኅዳር 30 ቀን ጀምሮ በስካይላይት ሆቴል በሚካሄደው ኩነት በአቪዬሽን ዘርፍ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ አገሮች ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ ተናግረዋል፡፡
የዓለም ሲቪል አቪዬሼን ባለሥልጣን ከአራት ዓመት በፊት ባደረገው የደኅንነት ኦዲት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከ73 ከደኅንነት ጋር የተያያዙ ግኝቶች ላይ ዕርምት እንደሚያደርግ ማሳወቁን የ2016 በጀት ዓመት ሪፖርት ይጠቁማል፡፡
ሪፖርቱ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሸን ባለሥልጣን በ34 ግኝቶች ላይ ዕርምት አድርጎ ከዓለም አቀፍ ተቋም ማረጋገጫ ማግኘቱ ሲገለጽ፣ በተቀሩት ላይ ማሻሻያ በማድረግ ዕውቅና እንዲሰጠው እየተጠባበቀ መሆኑን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
እ.ኤ.አ. በ2012 አፍሪካ በዓለም ሕይወት ቀጣፊ የሆኑ የአየር ትራንስፖርት አደጋዎች ከሚከሰትባቸው ሥፍራዎች ተቀዳሚ ሆኗ በመገኘቷ፣ የአውሮፓ ኅብረት 20 ያህል የአኅጉሪቷን አየር መንገዶች በአውሮፓ አገሮች የአየር ክልል እንዳያልፉ አግዶ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
በዚህም ምክንያት 35 የአፍሪካ አገሮች የአቪዬሽን ሚኒስትሮችና ባለሥልጣናት በናይጄሪያ አቡጃ ተሰባስበው፣ ‹‹የአቡጃ የደኅንነት ግቦች›› (Abuja Safety Targetes) ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የአቡጃ ግቦች የአደጋዎችን መጠን መቀነስ፣ ራስ ገዝ የሆኑ የአቪዬሸን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶችን መቋቋምና ማጠናከር፣ ዋና ዋና የተባሉ አሳሳቢ የደኅንነት ጉዳዮችን መፍትሔ መስጠት፣ ለዓለም የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የደኅንነት ኦዲት ፕሮግራም መተዳደሪያዎችና ዕቅዶች (ICAO Universal Safety Oversight Audit Programme (USAOP) State Action Plan) ጋር የተጣጣሙ አሠራሮችን ተግባር ላይ ማዋል፣ እንዲሁም የዓለም የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) የሥራ ላይ ደኅንነትና ኦዲቶች ከፍ ማሳደግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
እነዚህ ግቦች ለማስፈጸም የተቀረፁት አጠቃላይ የትግበራ መንገዶች (Overall Mechanism Used to Track the Implementation) ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ. በ2008 ከአጠቃላይ ግቦቹ 60 በመቶውን ያህል ያሳኩት አገሮች 13 ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ወደ 31 ከፍ ብለዋል፡፡
ሌሎች 19 አገሮች ከደረጃ በታች የሆነ የደኅንነት ሽፋን እንዳላቸው የሚጠቁመው ሪፖርቱ፣ ከ75 በመቶና ከዚያ በላይ አፈጻጸም ያላቸው አገሮች 11 ብቻ መሆናቸውን አሳውቋል፡፡
ከፍተኛ አፈጻጸም ካላቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካና ሞሮኮ ተቀዳሚ እንደሆኑም ተጠቁሟል፡፡ የዓለም ሲቪል አቪዬሸን ባለሥልጣን የአፍሪካ አገሮች አቪዬሽን ደኅንነት እ.ኤ.አ. 2028 ሲደርስ 95 በመቶ ላይ ማድረስ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡