ሔለን ተስፋዬ

December 4, 2024

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ደንበኞች የባንክ ሒሳብ ሲከፍቱ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በአስገዳጅነት እንዲያቀርቡ ቀነ ገደብ ማስቀመጡን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሁሉም ባንኮች በላከው ደብዳቤ ከታኅሳስ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የሁሉም ባንኮች ቅርንጫፎች፣ ደንበኞች አዲስ ሒሳብ ሲከፍቱ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሊኖራቸው ይገባል ብሏል፡፡ 

ከሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ በዋና ዋና ከተሞች ተግባራዊ እንደሚደረግ፣ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የባንክ ደንበኞች ሒሳብ ለመክፈት ከአንድ ዓመት በኋላ ከታኅሳስ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በአስገዳጅነት እንደሚጠይቁ ተገልጿል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በአስገዳጅነት ተግባራዊ ለማድረግ ያስፈለገው፣ የፋይናንስ ሥርዓቱን ደኅንነትና ታማኝነትን ለማሳደግ መሆኑን፣ ለሁሉም ባንኮች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም የፋይናንስ ማጭበርበሮችን ለመከላከል፣ የመረጃ ባለቤትነት ጥበቃ ለማረገገጥና ከተጠቀሰው ጊዜ ጀምሮ የባንክ አገልግሎት ለማግኘት የግድ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ማቅረብ አስገዳጅ ካደረገባቸው ምክንያቶች ውስጥ እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ደንበኞች የትኛውንም የባንክ አገልግሎት ለማግኘት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡  

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የሕዝብ ግንኙነት ስፔሻሊቲ ወ/ሪት ቃል ኪዳን አብርሃም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት ለሚሰጡት አገልግሎት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ቅድመ ሁኔታ ያደረጉ ተቋማት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ምዘገባና የነዋሪነት አገልግሎት፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎትና የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ናቸው፡፡

በ2015 ዓ.ም. በፀደቀው የኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ መሠረት ተቋማቱ አገልግሎት ለመስጠት፣ እንደ ቅድመ ሁኔታ ወይም ግዴታ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን እየጠየቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ማንነትን የሚገልጽ፣ በአገልግሎት ሰጪና በተቀባይ መካከል ያለውን ሥርዓት ቀልጣፋና ተዓማኒ የሚያደርግ ሥርዓት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን የተለያዩ ተቋማት አስገዳጅ እያደረጉ ያሉት የቀበሌ መታወቂያን ሊተካ ስለሆነ ነው ወይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወ/ሪት ቃል ኪዳን ሲመልሱ፣ ዲጂታል መታወቂያ የቀበሌን መታወቂያን የሚተካ እንዳልሆነና የቀበሌ መታወቂያ በዋናነት የሚያስፈልገው የግለሰብ የመኖሪያ አድራሻን ለማወቅ ነው ብለዋል፡፡  

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ፕሮግራም በአዋጁ መሠረት ዜጎች እንዲመዘገቡ የማስገደድ ሥልጣን እንዳልተሰጠወው፣ ነገር ግን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መታወቂያውን አስገዳጅ ማድረግ እንዲችሉ ተፈቅዷል ሲሉም አክለዋል፡፡

የጣት አሻራ፣ የዓይን፣ አይሪስ ስካንና የፊት ምሥል ነዋሪዎች መታወቂያውን ለማግኘት የሚያቀርቧቸው የባዮ ሜትሪክ መረጃዎች እንደሆኑ ገልጸው፣ እያንዳንዱ ሰው የሚለይበት ባለ12 ልዩ መለያ ቁጥር ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ዜጎች ማግኘታቸውንና በክልሎችም በኢትዮ ቴሌኮም፣ በገቢዎችና በሌሎች ተቋማት አማካይነት ምዝገባ መጀመሩን ወ/ሪት ቃል ኪዳን ተናግረዋል፡፡

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት የሚፈልጉ ዜጎች የዕቁብና የዕድር ካርድ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የባንክ ሒሳብ ደብተርና ፓስፖርት በመያዝ መመዝገብ ይችላሉ ብለዋል፡፡