
December 4, 2024

በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ባንኮች ሕንፃዎቻቸውን የገነቡበት ሰንጋ ተራ አካባቢ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከራሱ ከፋይናንስ ዘርፍም ሆነ ከሌሎች የውስጥና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች የሚመነጩና የዘርፉን መረጋጋት ሊያውኩ የሚችሉ ሥጋቶችን መለየትና መፍትሔ መስጠት አንዱ ኃላፊነቱ እንደሆነ በማመን እነሆ ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት ሪፖርት (Financial Stability Report) ከቀናት በፊት ይፋ አድርጓል፡፡
በሚያዝያ 2016 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ይፋ ከተደረገ በኋላ በየዓመቱ ኅዳር ወር እንደሚቀርብ ከዚህ ቀደም የተገለጸውን ቃል መሠረት ተደርጎ የቀረበው የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት ሪፖርት ካነሳቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንኳር የሆኑት የሚከተሉት ናቸው፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቀጣይ ያስመዘግበዋል ተብሎ የሚጠበቀውን ዕድገት መሠረት በማድረግ መንግሥት በተከታታይ እያደረገ የሚገኘውን የተለያዩ የማክሮ ኢኮኖሚና መዋቅራዊ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ-2 ታሳቢ በማድረግ አገሪቱ ከፍተኛ ዕድገት ከማስመዝገብ ባሻገር በመካከለኛ ጊዜ የዋጋ ንረትን ማቃለል እንደሚቻል ተስፋ ሰንቋል፡፡
የባንክ ዘርፉ አንዳንድ አሉታዊ የሚባሉ ሥጋቶች ቢኖሩትም በጥቅሉ ሲታይ ከጥሬ ገንዘብ አከል ንብረት (ሊኪዊዲቲ) ሥጋት እንዲሁም የተረጋጋ የአጭር ጊዜ የሊኪዊዲቲ ችግር (Shoaks) መቋቋም እንደሚቻል አሳይቷል፡፡ በአንጻሩ ግን የባንክ ኢንዱስትሪው በአጭርና ረዥም ጊዜ ውስጥ ከማጭበርበር፣ ከውስጥ ሥጋት እንዲሁም የሦስተኛ ወገን (አካል) ጋር የተገናኙ አደጋዎች የተረጋገጡበት እንደሆነ በሪፖርቱ ተዳሷል፡፡
የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መሠረተ ልማት እየጎለበተ ቢሆንም አሁንም ከመዋቅራዊ፣ ከአሠራርና ቴክኒካዊ ቅልጥፍናዎች ጋር የተዛመዱ ማሻሻያዎችን እንደሚፈልግ ተጠቁሟል፡፡
የአገሪቱ የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ከዓለም አቀፍ እስከ አገር ውስጥ ባሉ በርካታ ተፅዕኖዎች ጫና ላይ መውደቁን የሚያስረዳው የብሄራዊ ባንክ ሪፖርት፣ ከዚህም ተጠቃሽ ሰበቦች ውስጥ እውነተኛ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች፣ የፋይናንስና ንዑስ ፋይናንስ ዘርፉ አወቃቀርና አሠራር እንዲሁም የፋይናንስ ሥርዓቱ መሠረተ ልማት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም በአጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ ከዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት መቀነስ እንዲሁም ከበርካታ የማክሮ ኢኮኖሚና ጂኦፖለቲካል ቀውስ ‹‹ሾኮች›› ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ሊጋረጡበት እንደሚችሉ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ይህ በመሆኑም የአገር ውስጥ የዋጋ ግሽበቱ ባለሁለት አኃዝ እንዲሆን፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ሸቀጥ ዋጋ እንዲያሻቅብ፣ የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ኤክስፖርትን ጨምሮ ጫና እንዲጋፈጥ የሚያደርግና ይህም በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ሥጋት የሚፈጥር መሆኑን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
ምንም እንኳን አሁናዊው የመንግሥት የማክሮ ምልከታ ለቀጣዩ ዓመት ምቹ ቢሆንም የገንዘብ ፖሊሲዎችን ማጠናከር፣ የአገር ውስጥ የደኅንነት ሥጋቶችና ውጫዊ ተፅዕኖዎች ለምሳሌ የሸቀጦች የዋጋ ተለዋዋጭነት ተያይዞ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ከተጋለጡ አደጋዎች ተጠቃሾቹ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ቁጥራዊ ማስረጃዎችን ለማቅረብ ያህል እ.ኤ.አ. በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ድረስ አጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉ ሀብት 3.,409 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ15.2 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የባንክ ዘርፉ የአንበሳውን ድርሾ የሚወስድ ሲሆን ይህም 96.1 በመቶ የሚሆነውን ይይዛል፡፡ ይህ አኃዝ እንደሚያስረዳው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት መረጋጋት የሚወሰነው በእነዚህ የባንክ ተቋማት ጤናማነትና አለመናወጥ ላይ መሆኑን አስረጂ ነው፡፡
መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ ሀብቱና የተቀማጭ ገንዘቡ ከጠቅላላው የባንክ ዘርፉ 47.9 በመቶ እንዲሁም 47.1 በመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ባንኩ ከቀዳሚው ዓመት ከነበረው የ49.5 በመቶ እንዲሁም 48.7 በመቶ ያነሰ ድርሻ መያዙን ያሳያል ተብሏል፡፡
ከገበያ ድርሻ አንጻር ባላቸው አቀማመጥ መካከለኛ ደረጃ ላይ የተቀጡት አዋሽ፣ አቢሲኒያ፣ ዳሸን፣ ኅብረትና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንኮች ያላቸው ድምር ሀብት ከአጠቃላይ ከባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ 28.9 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ሲሆን ተቀማጭ ገንዘባቸው ደግሞ የ30.3 በመቶ ድርሾ አለው፡፡
ቀሪ 25 የሚሆኑትና ከገበያ ድርሾ አንጻር አነስተኛ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ናቸው የተባሉት ባንኮች ድምር ሀብታቸው ከባንክ ኢንዱስትሪው የ23.3 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን የተቀጭ ገንዘባቸው ድርሻ ደግሞ 22.7 በመቶ የሚሆነውን እንደሚሸፍን ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡
ባንኮች ለሴክተሮች ካቀረቡት ብድር አንጻር የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ 23 በመቶ የንግድና አገልግሎት ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲመሳከር ይኼ ነው የሚባል ለውጭ ያልታየበት መሆኑ ቀርቧል፡፡ በአንጻሩ ለግብርና ዘርፉ የኢትዮጵያ ባንኮች ያቀረቡት ብድር ድርሻ ቀድሞ ከነበረው የ6.4 በመቶ ድርሻ ወደ 6.3 በመቶ ዝቅ ሲል የኤክስፖርት ዘርፉም በ2015 ዓ.ም. ከሸፈነው የ15.7 በመቶ ድርሻ ወደ 14.1 በመቶ ዝቅ ብሎ ተገኝቷል፡፡
የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ከጥሬ ገንዘብ አካል ንብረት ሥጋት (ሊኪዊዲቲ ሪስክ) አንጻር ባለ መመዘኛ ሲታይ ለአብነትም አሥር ዋነኛ የእያንዳንዱ ባንክ ተበዳሪዎች በአንድ ጊዜ ገንዘባቸውን ቢያወጡ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ሲታይ የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ከጥሬ ገንዘብ አካል ንብረት አደጋ መጋለጡን በ2016 የበጀት ዓመት የነበረው ውጤት አመላካች መሆኑ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የገንዘብ ደኅንነት ሪፖርቱ እንደሚያስረዳው የባንኮች የሥራ ላይ ሥጋት (Operational Risk) ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል፡፡ ከዓመት በፊት በአጠቃላይ ከባንክ ዘርፉ በተለያየ መልኩ ያጭበረበረው የገንዘብ መጠን አንድ ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የገንዘብ መጠኑ ወደ 1.3 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን እንዲሁም ይህም ሁሉም በሚያስብል ሁኔታ በ28 ባንኮች ተፈጽሟል፡፡
ከላይ የተገለጹት የማጭበርበር ተግባራት በዋናነት ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን፣ ሐሰተኛ ቼኮችን፣ ሐሰተኛ የባንክ ዋስትናዎችን፣ የተሰረቁ የኤቲኤም ካርዶችን፣ ሐሰተኛ የስልክ ጥሪዎችንና መልዕክቶችን በመጠቀም የተከናወኑ መሆናቸውን ብሔራዊ ባንክ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡ ባንኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳካት በሚል በሚተገብሯቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ምክንያት መሰል ሥጋት እየጨመረ ከመሄዱ አንጻር ባንኮች እነዚህን ሥጋቶች ለመቀነስ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀይሰው እንዲሠሩ ማሳሰቢያ ቀርቧል፡፡
በተጨማሪ የብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ከዳሰሳቸው ጉዳዮች ውስጥ በኢትዮጵያ ያለው የዲጂታል ክፍያ ሥነ ምኅዳር ዕድገትን ይመለከታል፡፡ የዲጂታል ክፍያ ሥነ ምኅዳሩ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም. በነበረው የሒሳብ ዘመን ድረስ ከ110 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ገንዘብ አካውንቶች፣ 47 ሚሊዮን የሞባይል ባንክ አካውንቶችን ጨምሮ ከ198 ሚሊዮን በላይ የዲጂታል አካውንቶች መከታቸውን ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም ከ35 ሚሊዮን በላይ የዴቢት ካርዶች በሠራጨት ላይ መሆናቸው በሪፖርቱ ተዳሷል፡፡
መንግሥት ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ቁጥር ሁለትን ተግባራዊ ለማድረግ በሒደት ላይ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህንንም ለመደገፍ የተቀናጀ የክልሎች የአካታችነት ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ በዘጠኝ ክልሎች መጀመሩ ተጠቅሷል፡፡ ማዕቀፉ በዋናነት የተዘጋጀው የፋይናንስ ተደራሽነቱ ላልተስፋፋባቸው ክልሎች በከፍተኛ ሁኔታ ለማስፋፋት የክልሎች የፋይናንስ አካታትነት ልዩነት ለማጥበብ እንዲሁም ከክልሎች ሁኔታ ጋር ለማጣጣም መሆኑ ታውቋል፡፡
የፋይናንስ ተገልጋዮች ጥበቃ ብሔራዊ ባንክ በጉልህ ጣልቃ ገብቶ ሊያስጠብቃቸው ከሚገቡ ጉዳዮች ውስጥ እንደሚገኝበት በሪፖርቱ የቀረበ ሲሆን፣ ይህም ግልጽነት፣ ፍትሐዊነትና የገልጋዮች (ሸማቾች) መብቶችን በማረጋገጥ የኅብረሰቡን አመኔታ ለማሳደግ ወሳኝ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነው፡፡
በአጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት ሪፖርቱ ማጠቃለያ ጭብጥ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ሥር የሰደደ ሥጋት ባይኖርም ሆኖም አንዳንድ ሥጋቶች እየጨመሩ በመሆናቸው የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነትና ደኅንነት በቀጣይ ለማረጋገጥ ተገቢ ትኩረት መስጠትና የመከላከያ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚባ ያመለክታል፡፡
የሪፖርቱ ማጠቃለያ ጭብጥ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ማለትም በባንክ፣ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፣ የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ ተቋማት፣ ኢንሹራንስ ዘርፍ ውስጥ ሥር የሰደደ ሥጋት ባይኖርም ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንድ ሥጋቶች እየጨመሩ መምጣታቸውንና የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነትና ደኅንነት በቀጣይነት ለማረጋገጥ ተገቢ ትኩረት መስጠትና የመከላከያ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ የሚያመላክት መሆኑን ብሔራዊ ባንክ ጠቅሷል፡፡