በኢትዮጵያ ከሚገኙ በርካታ የውኃ አካላት መካከል ሐይቆች ይጠቀሳሉ

ዜና አደገኛና መርዛማ ኬሚካሎችን ወደ ውኃ አካላት መልቀቅ በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ…

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: December 4, 2024

አደገኛ ወይም መርዛማ ኬሚካሎች መድፋት፣ መልቀቅ፣ መጣል፣ ማከማቸት ወይም መቅበር፣ በወንጀል ተጠያቂ  የሚያደርግ ረቂቀ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀረበ፡፡

ረቂቅ ሕጉ ዓይነ ምድር መፀዳዳት፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓት ወይም የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ የሌለው ተቋም ግንባታ፣ የፍሳሽ ማጣሪያ የሌለው የተሽከርካሪ እጥበት፣ እንዲሁም ሌሎች የውኃ አካላት ሥነ ምኅዳርን የሚጎዱ ድርጊቶችን ማከናወን በወንጀል እንደሚያስቀጣና የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሠረት አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ያብራራል፡፡

በተከለለ የውኃ አካል ዳርቻ ውስጥ የተከለከለ ድርጊት እንዳይፈጸም አግባብ ያለው አካል ተቆጣጣሪ እንደሚመደብ በረቂቁ የተገለጸ ሲሆን፣ ተቆጣጣሪው አካል በቅድሚያ ሳያሳውቅ ወይም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይዝ ጥፋት ተፈጽሞበታል ብሎ ወደ ጠረጠረው ቦታ ወይም ቅጥር ግቢ በሥራ ሰዓት የመግባት ሥልጣን ተሰጥቶቷል፡፡

በተከለለ የውኃ አካል ዳርቻ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ነባር ልማት ባለበት ሁኔታ ሊቀጥል የሚችለው፣ በውኃ አካሉና በብዝኃ ሕይወቱ ላይ ጉዳት ወይም ብክለት የማያስከትል መሆኑ አግባብ ባለው አካል ከተረጋገጠ ብቻ መሆኑን ረቂቁ ያብራራል፡፡

በተጨማሪም ተቆጣጣሪው የተከለለ የውኃ አካል ዳርቻ ሕጋዊ ዕውቅና እንዲያገኝ የማድረግ፣ በፌዴራል ወይም በክልል መንግሥታት የተከለለ የውኃ አካል ዳርቻን የማልማት፣ የመንከባከብ፣ የመጠበቅና የመቆጣጠር፣ ግለሰቦች፣ ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የንግድ ድርጅቶች በውኃ አካል ዳርቻዎች ልማትና ጥበቃ እንዲሳተፉ የማስተባበር ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

በውኃ አካል ዳርቻ ርቀት አወሳሰን፣ ልማትና እንክብካቤ ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያ የውኃ አካላት በተለያዩ ሰው ሠራሽ ምክንያቶች በጥራትም ሆነ በመጠን ጉዳት እየደረሰባቸው መሆናቸው ተብራርቷል፡፡

የውኃ አካላት ዳርቻ በተፈጥሮ በካይ ነገሮችን የመያዝ ወይም የማጣራት ባህርይ የነበራቸው ዕፅዋት በመመንጠራቸው፣ የውኃ አካል ጠርዝ ድረስ የእርሻ ሥራ በመከናወኑ፣ በካይ ቆሻሻ በውኃ አካላትና ዳርቻዎቻቸው በመደፋቱ ወይም በመለቀቁ፣ የውኃ አካላትን ደኅንነት የሚያዛቡ ልዩ ልዩ ድርጊቶች በመከናወናቸው ምክንያት የውኃ አካላቱ እየተበከሉ መሆናቸውን ረቂቁ  ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም በመጤ አረም እየተወረሩ፣ መጠናቸው እየቀነሰና እየደረቁ በመሆናቸው በውኃ አካላት ሥርዓተ ምኅዳር አገልግሎቶች ላይ ማኅበራዊ፣ አካባቢያዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እያስከተለ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡

በረቂቁ የውኃ አካል ዳርቻ ፍፁም ጥብቅ፣ ጥብቅና ቁጥጥር የሚባሉ ሦስት ዓይነት አከላለሎች ሊኖሩት እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ እነዚህን አከላለሎችንም ለይቶ ማወቅ ይቻል ዘንድ መለያ አጥር ወይም የወሰን ምልክት እንደሚደረግባቸው፣ እንዲሁም በተከለሉ የውኃ አካል ዳርቻዎች ውስጥ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ማከናወን እንዲቻል መዳረሻ መንገድ ታሳቢ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

 በጥብቅ የውኃ አካል ዳርቻ ላይ ከፍራፍሬ ልማት ውጪ የሆነ እርሻ፣ የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓት ወይም የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ካለው የቱሪዝም መዳረሻ ተቋም በስተቀር የማንኛውም ተቋም ግንባታ የውኃ አካል ብዝኃ ሕይወት ደኅንነትን ወይም የወንዝ የተፈጥሮ ፍሰትን የሚያዛባ የማዕድን ማውጣት፣ የቀብር ቦታ ማዘጋጀትና የተሽከርካሪ እጥበት የተከለከለ መሆኑ ተደንግጓል፡፡

በፍፁም ጥብቅ ቦታዎች እርሻ ወይም ከብት እርባታ፣ ከተፈቀደ መግቢያና መሸጋገርያ ግንባታ ውጪ የተሸከርካሪ መንገድ ሥራ ወይም እንቅስቃሴ ማድረግ የተከለከለ መሆኑ በረቂቁ ተካቷል፡፡

በቁጥጥር የውኃ አካል ዳርቻ ውስጥ አደገኛ ወይም መርዛማ ኬሚካል መድፋት፣መልቀቅ፣ መጣል፣ ማከማቸት ወይም መቅበር፣ ደረቅ ወይም ፍሳሸ ቆሻሻ መድፋት፣ መልቀቅ፣ ማከማቸት ወይም መጣል፣ ዓይነ ምድር መፀዳዳት፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓት ወይም የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ የሌለው ተቋም ግንባታ፣ የፍሳሽ ማጣሪያ የሌለው የተሽከርካሪ እጥበት፣ ዛፍ መቁረጥ ወይም ዕፅዋት መመንጠርና  ልቅ ግጦሽ የተከለከሉ ተግባራት ናችው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ባደረገው አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ስምንተኛ መደበኛ ስብሰባ በረቂቁ ከተወያየበት በኋላ ለዝርዝር ዕይታ በዋናነት ለውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ በተባባሪነት  ለከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡