
December 4, 2024

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከፊል ገጽታ
አፈላጊውን መሥፈርት አሟልተዋል የተባሉ አሥር ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ ኢኮኖሚክ ዞን መሸጋገራቸውን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድራቸው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ አሥሩ ወደ ልዩ ዞን ማደጋቸውን፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለኮርፖሬሽኑ ባለፈው ሳምንት በላከው ደብዳቤ ገልጿል፡፡
በሥራ ላይ ካሉ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ያደጉት አዳማ፣ ባህር ዳር፣ ቦሌ ለሚ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ ቂሊንጦ፣ ኮምቦልቻ፣ መቀሌና ሰመራ መሆናቸው ታውቋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለማሳደግ አዋጅ ቁጥር 1322/2016 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸው የግል ዘርፉ በተለያዩ ዘርፎች እንዲሳተፍ ለማበረታታት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ እንቅስቃሴን ለማጠናከርና የኢኮኖሚ ክላስተሮችን ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ ታምኖበት ነው ተብሏል።
ፓርኮቹ ወደ ልዩ ኢኮኖሚክ ዞን እንዲሸጋገሩ ሲደረግ የውጭ ምንዛሪ አቅምን ይበልጥ እንደሚያሳድጉ ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን፣ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚገቡና የሚመጡ ዕቃዎች ከቀረጥና ከግብር ክፍያ ነፃ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ በአዋጅ መፈቀዱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በአዋጁ መሠረት ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚገቡ የግንባታ ዕቃዎች ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ እንዳይከፈልባቸው፣ እንዲሁም የካፒታል ዕቃዎች ከማንኛውም ቀረጥና ታክስ ነፃ የመሆን መብት እንደሚያገኙ መገለጹ አይዘነጋም፡፡
አዋጅ ቁጥር 1322/2016 ክፍል አምስት የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ተጠቃሚዎች መብቶችና የኢንቨስትመንት ሥራ ስለሚከናወንበት ሁኔታ ይገልጻል፡፡
በዚህ መሠረት የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አልሚዎች ዲዛይን የማድረግ፣ የመገንባት፣ ሕንፃዎች ግንባታዎችን ተንቀሳቃሽ ሀብቶችን የማከራየት ወይም የመሸጥ መብትን እንዳላቸው በአዋጁ ተፈቅዷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሠረት ብድር፣ የብድር ክምችትና ወይም ሌሎች የገንዘብ ምንጮችን ለማግኘት፣ በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ የፋይናንስ ገቢዎች ላይ መሳተፍ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
በማንኛውም የልዩ ኢኮኖሚ ዞን በአዋጅና አግባብነት ባላቸው ሕጎች የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማበረታቻዎች የማግኘት መብት እንዳለባቸው፣ በአዋጁ ከተሰጡ መብቶች መካከል ይገኙበታል፡፡