

ድጋፉ ይፋ ሲደረግ
ማኅበራዊ አሜሪካ በኢትዮጵያ የግልና አካባቢ ንፅህናን ለማሻሻል የ31 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አደረገች
ቀን: December 4, 2024
አሜሪካ በኢትዮጵያ የግልና አካባቢ ንፅህና እንዲሁም የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ለተቀረፀው ኤም4ኤስ ፕሮጀክት የ31 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ይፋ አደረገች፡፡
በአሜሪካ ልማት ተራድኦ ድርጅት ሥር በሚገኘው ኤም4ኤስ ፕሮጀክት የሚተገበረው የግልና አካባቢ ንፅህና እንዲሁም የፆታ እኩልነት ሥራ፣ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፣ ኢንሺየቲቩ በኢትዮጵያ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚያስችል በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለችግሩ ተጋላጫ የሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይ ሴቶችና ልጃገረዶችን ለመድረስ ትኩረት ማድረጉንና በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በሶማሌ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንደሚተገበርም አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለ5.4 ሚሊዮን ሕዝቦች መሠረታዊ የግልና አካባቢ ንፅህናን ተደራሽ ማድረግና ለ180 ሺሕ ሴቶችና ልጃገረዶች የወር አበባ ጤናና የግል ንፅህና ጤና መጠበቂያ ምርቶችን ተደራሽ ለማድረግ ያለመም ነው፡፡
የአሜሪካ ልማት ተራድኦ ድርጅት ኤም4ኤስ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት ችግር ሆኖ ለዘለቀው የአካባቢና የግል ንፅህና አጠባበቅ አቅርቦቶች መስተጓጎል መፍትሔ እንዲሆን ገበያን መሠረት ያደረገ፣ ዘላቂና አካታች ዕድገት ለማምጣት የሚያስችል አሠራር የሚከተል መሆኑም ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ልማት ተራድኦ ድርጅት በአሁኑ ወቅት የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሻሻልና በገጠርና በከተማ አካባቢዎች የአካባቢ ንፅህናን ለመጠበቅ 190 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እያደረገ መሆኑን በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡