ቭላድሚር ፑቲን

ዓለም የሩሲያና ዩክሬን የድርድር ተስፋና የኑክሌር ሥጋት

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: December 4, 2024

ባለፈው ዓርብ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮለድሚር ዘለኒስኪ ከስካይ ኒውስ ጋር ዘለግ ያለ ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር፡፡ በቃለ መጠይቁም ‹‹ዩክሬን በአሁኑ ወቅት በምትቆጣጠራቸው ግዛቶቿ የሰሜን ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ብትሆን ጦርነቱ ያበቃል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሩሲያና ዩክሬን የድርድር ተስፋና የኑክሌር ሥጋት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ዶናልድ ትራምፕ

እ.ኤ.አ. በፌብሯሪ 2022 ሩሲያ በዩክሬን ምድር ጦሯን ካስገባች ጀምሮ በማንም አካል ተሰንዝሮ የማያውቅ ሐሳብ ነበር ዘለኒስኪ የሰነዘሩት፡፡ ሐሳባቸው ዩክሬንን በአፋጣኝ የኔቶ አባል ለማድረግ ያላቸውን ከፍተኛ ጉጉት የሚገልጽ ከመሆኑ ባሻገር፣ አውሮፓውያንና አሜሪካ ዩክሬንን በአፋጣኝ የኔቶ አባል ለማድረግ ያን ያህል ዝግጁነት ያላቸው አይመስልም፡፡

ከዚህ ቀደም የኔቶ መሪዎች በቤልጂየም ዋና ከተማ ብራስልስ ባደረጉት ስብሰባ፣ ዘለኒስኪ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር፣ ኔቶ በአፋጣኝ ለዩክሬን የኔቶ አባልነት ጥሪ ማቅረብ እንዳለበት አሳስበው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ‹‹ዩክሬን የያዘችውን ይዛ›› የሚለው መለሳለስ ነው፡፡ ሆኖም እንደ ዘለኒስኪ አባባል፣ ኔቶ ጥያቄውን ሲያቀርብ፣ በቅድመ ጦርነት የነበሩ የዩክሬን ይዞታዎች በሙሉ የዩክሬን አካል ለመሆናቸው በግልጽ መመልከት ይኖርበታል፡፡

ዘ ኪዬቭ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው፣ የዘሊንስኪ አዲስ ሐሳብ በፊት ያንፀባርቁት ከነበረው ጋር ይፃረራል፡፡ ዘሊንስኪ እንዳሉት፣ ዩክሬን የኔቶ አባልነቷ የሚረጋገጥ ከሆነ አሁን በሩሲያ ይዞታ ሥር ያሉ ግዛቶቿን ለወደፊት በዲፕሎማሲ ድርድር እንዲመለስላት ጥረት የምታደርግ ይሆናል፡፡ ክሪሚያን ጨምሮ በሩሲያ የተያዙ ግዛቶችን በምዕራባውያን የጦርና የገንዘብ ድጋፍ ማስመለስ ይቻላል የሚለው የኪዬቭ የቆየ አቋም ሸብረክ ማለት መጀመሩን ሪስፖንሲብል ስቴት ክራፍት የተሰኘ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

ዩክሬን ባለፈው ሳምንት ማክሰኞና ሐሙስ ከባድና በርካታ ከተሞችን

የሩሲያና ዩክሬን የድርድር ተስፋና የኑክሌር ሥጋት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ቮለድሚር ዘለኒስኪ

ያዳረሱ የሩሲያ ድብደባዎችን አስተናግዳለች፡፡ የዩክሬን ጦር በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ሩሲያ በሐሙሱ ድብደባ ብቻ 91 ሚሳይሎችና 97 ድሮኖች ተጠቅማለች፡፡

በዚህም አንድ ሚሊዮን ዩክሬናውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸዋል፡፡ እነዚህ የሩሲያ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች ያነጣጠሩት በዩክሬይን የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶች ላይ እንደነበር ሲዘገብ፣ ግማሽ ያህሉን የኤሌክትሪክ አቅርቦቷን ከኑክሌር ኃይል የምታገኘው ዩክሬን በድብደባው ወቅት በርካታ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቿ ኃይል ማስተላለፍ አቁመው እንደነበር ታውቋል፡፡ የዩክሬን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ሩሲያ የዩክሬንን የኃይል አቅርቦት የጥቃት ዒላማ ስታደርግ ከመጋቢት አንስቶ 11ኛዋ ነው፡፡   

ዘሊንስኪ ይህንን የሩሲያ ጥቃት ‹‹ነውረኛና አባባሽ›› ሲሉ ቢገልጹትም፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ‹‹ጥቃቱ ዩክሬን የአሜሪካንን አታካምስና የእንግሊዝን ብላክ ሻዶው መካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይሎችን በመጠቀም፣ በሩሲያ ላይ ለሰነዘረችው ጥቃት መልስ ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሩሲያ ቀደም ባሉ ቀናት በሰከንድ ሦስት ኪሎ ሜትር የሚበሩ ኦሬሽኒክ የተሰኙ አዲስ ሥሪት ሚሳይል ወደ ዩክሬን በማስወንጨፍ ያስተዋወቀች ሲሆን፣ ፑቲን አገራቸው እነዚህን መብረቅ እቶን ዘለላዎች በብዛት እያመረተች እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡

አክለውም፣ አሜሪካና  አውሮፓ ለዩክሬን ኑክሌር ጦር መሣሪያ የሚያስታጥቁ ከሆነ ሩሲያ ያላትን የጦር አቅም ሁሉ ተጠቅማ እንደምታጠቃ ዝተዋል፡፡ ሩሲያ በቅፅል ስሙ ‹‹የሐዜል ዛፍ›› በመባል የሚታወቀውን ሚሳይል በመተኮስ በዲኒፕሮ የሚገኙ ወታደራዊ ተቋማትን ከማውደሟም በተጨማሪ፣ የኑክሌር አጠቃቀም ስምምነትን በማላላት የዩክሬን ብቻ ሳይሆን የሚሳይል አቅራቢ አገሮችም ተቋማት ዒላማ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታዎች እንዳሉ አስምራበታለች፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ኸማይሃል ቅዳሜ ዕለት እንዳሉት ከሆነ፣ ዩክሬን ካሏት 20 የሲቪል አየር ማረፊዎች አሥራ አምስት ያህሉ በጦርነቱ ወድመውባታል፡፡

በበርሚንግሀም ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ደኅንነት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ስቴፈን ዎልፍ ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ባሠፈሩት ጽሑፍ፣ ሁለቱም ተፋላሚ አገሮች እጅግ በተጠና አካሄድ ግጭቱን ገፍተውበት ሳለ፣ የሩሲያ ጦር በምሥራቅ ዩክሬን በሚያደርገው ግስጋሴ በዩክሬን ሁነኛ መሠረተ ልማቶች ላይ ውድመት እያደረሰ ይገኛል፡፡

‹‹ሁለቱም አገሮች የትራምፕን (የአሜሪካውን ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለማለት ነው) በመጪው ጃንዋሪ ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ በማሰላሰል ነው ድርጊቶቻቸውን የሚቃኙት፤›› ይላሉ ዎልፍ፡፡ እንደ እኚህ ምሁር፣ በቅርብ የተጠናቀሩ የሕዝብ አስተያየቶች የሚያሳዩት የሚበዙት ዩክሬናውያን የሩሲያ ግስጋሴ ባልተገታበት በአሁኑ ወቅት ግጭቱ በድርድር እንዲፈታ ይሻሉ፡፡

የጋሉፕ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ አስተያየት ከሰጡ ዩክሬናውያን 52 በመቶው ዩክሬን ጦርነቱ በአፋጣኝ ይቆም ዘንድ ድርድር መጠየቅ እንደሚኖርባት ይስማማሉ፡፡ 38 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አገራቸው እስክታሸንፍ መዋጋት መቀጠል አለባት ይላሉ፡፡ ‹‹ይህ አኃዝ ከዓመት በፊት ከነበረው የተገላቢጦሽ ነው፤›› ይላሉ ዎልፍ፡፡

የዛሬ ዓመት ገደማ በተሰበሰበ ተመሳሳይ አስተያየት፣ ‹ጦርነት መቀጠል ይኖርባታል› የሚሉት 63 በመቶ የነበሩ ሲሆን፣ ‹ድርድር ይሻላል› የሚሉት 27 በመቶ ብቻ ነበሩ፡፡ ጦርነቱ በተጀመረበት እ.ኤ.አ. 2022 ደግሞ ‹‹ግፋ በለው›› የሚሉ ወደ 73 በመቶ፣ ‹‹ድርድር›› ደግሞ 22 በመቶ እንደነበር ያስታውሳሉ፣ ዩክሬናውያን ምን ያህል በጦርነት ቀውስ እየዛሉ እንደመጡም ‹‹ይህ ግን ዩክሬናውያንን ትራምፕ ለሚያመነጩት፣ ፑቲን ለሚቀበሉት ሐሳብ ተገዥ ይሆናሉ ማለት አይደለም፤›› ይላሉ ምሁሩ፡፡

ከዚህ በኋላ ዘለኒስኪና ዩክሬንን የሚጠብቃቸው ዋና ተግዳሮት ከጦርነት ወደ ሰላም የሚደረግን ንግግር በቅጡ ማስተዳደር ሲሆን፣ ይህንን ሲያደርጉም በአሜሪካ ጫና ሥር እንደሚሆኑና የሩሲያ ፍላጎቶችም ይታከሉበታል ሲሉ ዎልፍ ይተነብያሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንደለ ትራምፕ ለዩክሬን የሰየሟቸው ልዩ ልዑክ ኬዝ ኬሎግ የማግባባት ሥራቸውን ለመጀመር እያሟሟቁ ያገኛሉ፡፡

ኬሎግን ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ አሜሪካ በሌላ ግጭት መሳተፍ አትሻም፡፡ የጦር መሣሪያ ክምችቷም ዩክሬይንን ለማገዝ ሲባል መቀነሱ አሜሪካ ታይዋን ለመከላከል በምትሠራው ሥራ ከቻይና ሊመጣ በሚችል ማንኛውም ፍጥጫ ተጋላጭ ሊያደርጋት ይችላል፡፡

ኬሎግ የዩክሬን የኔቶ አባልነት እንዲቆምና በምትኩ የዩክሬንን ደኅንነት ዋስትና የሚያረጋግጥ፣ ሁሉን አቀፍ የሚቆጣጠርና የሚለካ የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ያሳስባሉ፡፡

እንደ ዘገባው ከሆነ፣ አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠው የወደፊት ዕርዳታ ዩክሬን ከሩሲያ ለመደራደር ያላት ቁጠኝነት ላይ የሚመሠረት ሲሆን፣ ዩክሬን ራሷን ለመከላከል የሚያስችላትን የጦር መሣሪያም ትለግሳለች፡፡ የጦርነት ግንባሮች ፀጥ እረጭ እንዲሉ ይደረጋል፣ ከጦር እንቅስቃሴዎች ነፃ ቀጣና ይመሠረታል፣ ሩሲያ ወደ ውጭ ከምትልከው የኃይል አቅርቦቶች በሚጣል ቀረጥ ለዩክሬን መልሶ ግንባታ እንዲውል ይደረጋል፡፡ ዕቅዱ ቀላልና ቀጥተኛ ቢሆንም፣ የሞስኮ ፍላጎቶች በድርድሩ ምን ጉዳዮችን ሊያካትቱ እንደሚችሉ አልተገለጸም፡፡

ለዩክሬን የሚደረግን ዕርዳታ ቀጣይነት የሚተቹ ተንታኞች የአሜሪካ ዘላቂ ጥቅሞች ቸል የመባላቸውን ሁኔታ ያነሳሉ፡፡ አሜሪካ በግጭቱ በቀጥታ መሳተፏና ከሩሲያ ጋርም የኑክሌር ፍጥጫ ውስጥ መግባቷ አይዋጥላቸውም፣ ያሳስባቸዋል፣ ያስፈራቸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ያሰፈኑት ዓለም አቀፋዊነት የሚል መርህ ላይ የተመሠረተ የአሜሪካንን የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች እሴቶችን የማያራምድ አካሄድ፣ የአውሮፓን ደኅንነት አስይዞ ለመደራደር የማያስችል ድንግዝግዝ መንገድ ነውም ይላሉ፡፡

ስለዚህ የዶናልድ ትራምፕ የድርድርና ጦርነቱን በአስቸኳይ የማስቆም ዕቅድ ለዩክሬን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚቆጠር መሆኑን በአጽንኦት ያብራራሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ነው ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ባይደን ዩክሬንን በኑክሌር የማስታጠቅ አማራጭ እያሰቡ እንደሚገኙ ከነጩ ቤተ መንግሥት መረጃዎች ያፈተለኩት፡፡ ትራምፕ ደግሞ የኑክሌር ሥጋት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት ምክንያት ከመቼውም ጊዜ በከፋ መልኩ ሥጋት የሆነበት ጊዜ መፈጠሩን ሲናገሩ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡

በኑክሌር ጦርነት ላይ በጻፉት መጽሐፍ የፑሊትዘር ሽልማት ዕጩ ለመሆን የበቁት አኔ ጃኮብሰን እንደሚሉት፣ የኑክሌር ጦርነት በወራት ሳይሆን በጥቂት ቀናት ውስጥ የዓለምን አብዛኛው ሕዝብ ሊፈጅ የሚችል ስለሆነ ጉዳዩ በዋዛ የሚታይ መሆን የለበትም፡፡

የቻይና ዜና አገልግሎት ሺንኋ ተንታኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው ግም እያለ ያለው ረዥሙና በረዷማው ክረምት የኤሌክትሪክ አቅርቦቷ በጦርነት በእጀጉ በተዳከሙባት ዩክሬን፣ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከትላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ክረምቱ ደግሞ ጦርነቱ ከተጀመረ ከ1,000 ቀናት በላይ በሆነ ጊዜ ከታየው በእጅጉ የከፋ እንደሚሆን ተፈርቷል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያስረዳው፣ 65 በመቶ የሚሆነው የዩክሬን የኃይል ማመንጨት ብቃት ወድሟል፡፡ ይህ ደግሞ በእያንዳንዱ ቤት በየቀኑ ከአራት እስከ 18 ሰዓታት መብራት እንዳይኖር አድርጓል፡፡

ሺንኋ እንደዘገበው በሩሲያም፣ በዩክሬንም በኩል በየዕለቱ የሚጨምር ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሰላምን ሲጓጉ ይስተዋላሉ፡፡

ዩክሬኔርጎ የተባለው የመንግሥት ኤሌክትሪክ አቅራቢ ድርጅት በዋና ከተማዋ ኪዬቭና በ16 ክልሎች ኮስተር ያለ የኤሌክትሪክ አጠቃቀም መመርያ አውጥቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 17 የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ፣ በጥቁር ባህር የወደብ ከተማዋ ኦዴሳ የ14 ሰዓታት የመብራት መቋረጥ ተከስቶ ነበር ይላል ሺንኋ በቅዳሜ ዘገባው፡፡

በዚህ ሁሉ ሥጋትና ውድመት ውስጥ የጃንዋሪ 20 ቀን 2025 የትራምፕ ቃለ መሃላ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት በገቡ በ24 ሰዓታት ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ ቃል መግባታቸውም አይዘነጋም፡፡