

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማኅበር ዓለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ንቅናቄ ቀናትን ባከበረበት ወቅት
ማኅበራዊ ፆታዊ ጥቃትን ለመቀልበስ
ቀን: December 4, 2024
ሴቶችን ከፆታዊ ጥቃት ለመከላከልና ኢኮኖሚያቸውን በማጠናከር ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ በመንግሥትና በተለያዩ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም፣ ሴቶችን ካሉባቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በሚገባው መጠን ማላቀቅ አልተቻለም፡፡
የትምህርት፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተሳትፏቸው እየጨመረ መሆኑን መረጃዎች ቢያሳዩም፣ ሴቶች ዛሬም በሚደርስባቸው ፆታዊ ጥቃት ከመንገዳቸው ሲስተጓጎሉ ይስተዋላሉ፡፡
ጦርነትና ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ የሴቶች ስቃይና ሰቆቃ የበረታ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡
እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የታለመውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ16 ቀናት የሚደረገው ፀረ ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ፣ በኢትዮጵያም በተለያዩ ተቋማት አማካይነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማኅበር ‹‹የሴት ጥቃት የእኔም ነው ዝም አልልም!›› በሚል መሪ ቃል ባለፈው ሳምንት ያዘጋጀው መድረክም የዚሁ አካል ነው፡፡
በወቅቱም፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ እናትዓለም እንዳለ እንደገለጹት፣ ሴቶች ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች አንፃር ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑና ለአገሪቱ ዕድገት ዋስትና በመሆናቸው ሁለንተናዊ ብቃታቸውን፣ ዋስትናቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡
መንግሥትም ይህን በመረዳት አስቻይ ፖሊሲዎችን፣ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችንና የሴቶችን መዋቅር ከላይ እስከ ታች በመዘርጋት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን በነፃነት የመደራጀት መብት በመጠቀም የተለያዩ የሴት አደረጃጀቶች ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠረላቸው ከመሆኑ ባሻገር እነዚህ አደረጃጀቶች እንዲጠናከሩ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው ብለዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቷ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማኅበርም የተፈጠረውን መልካም ዕድሎች በመጠቀም ከተመሠረተበት 1990 ዓ.ም. ጀምሮ የአባላቱንና የከተማዋን ሴቶች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍ ያለ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
በዚህም ማኅበሩ ከ499 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ አባላቱ ስለ መብቶቻቸውና የሚደርሱ ጥቃቶችን ከመቀነስ አንፃር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ ባሉት ሁለት መጠለያዎችም የምግብ፣ የአልባሳት፣ የሕክምናና መሰል ድጋፎችን በማስተባበር 1‚446 በሚሆኑ ሴቶችና ሕፃናትን በመደገፍ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
በሥራ ዕድል ፈጠራ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲጨምርና በከተማው ልማትና ሰላም ላይ የራሳቸውን ጉልህ አሻራ እንዲያኖሩ በማድረግም የተሠሩ ሥራዎች ከፍ ያሉ ናቸው ብለዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ እናትዓለም፣ ይህ ሥራም እየተሠራ፣ አሁንም በከተማዋ ውስጥ በሴቶች ላይ የተለያዩ ዓይነቶችና ይዘቶች ያሉት ጥቃቶች በቅርብ በሚባሉ ሰዎች እየተፈጸመ እንደሚገኝ መረጃዎችና ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነኚህ ጥቃቶች የሥነ ልቦና፣ አካላዊና ወሲባዊ ጥቃቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ጥቃቶች ለመከላከልም ማኅበሩ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጥምረት በመሆን ለአባላቱና ለከተማዋ ነዋሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች በመስጠት ላይ ነው፡፡
በተጨማሪም ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ፍትሕ እንዲያገኙ ለማስቻል ከፍትሕ ተቋማት ጋር በመሥራት ላይ መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን እንደገለጹት፣ ፆታዊ ጥቃት በአሁኑ ወቅት አሳሳቢና አነጋጋሪ ከሆኑ አጀንዳዎች መካከል የሚገኝ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ አገር የሚታየውን ፆታዊ ጥቃት ለማስቀረት የተለያዩ የሴት አደረጃጀቶች የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ መንግሥትም ሕጎች እንዲሻሻሉና የመዋቅር ለውጥ እንዲኖር በማድረግ ረገድ የላቀ አበርክቶ ነበረው ብለዋል፡፡
በ16ቱ ፀረ ፆታዊ ጥቃት ንቅናቄ ዘመቻ የነጭ ሪቫን ቀን፣ የኤድስ ቀን፣ የአካል ጉዳተኞች ቀን፣ የጥቃት ሰለባዎች ቀን፣ የሰብዓዊ መብት ተከላካዮች ቀንና የሰብዓዊ መብት ቀን አብረው የሚታሰቡ ቀናት መሆናቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፣ እነኚህም ፆታዊ ጥቃትን በመቃወም ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ናቸው፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ፣ የ16ቱ ፀረ ፆታዊ ጥቃት ንቅናቄ ዘመቻ ቀናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ፆታዊ ጥቃቶችን ለማስቀረት ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ማደራጃ ሥልት ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ዙሪያ የተለያዩ ተግባራት በተለያዩ አካላት እየተከናወኑ ቢሆንም አሁንም በተለያየ ሁኔታና ቦታዎች ላይ የፆታዊ ጥቃት በሰፋ ሁኔታ እየተፈጸመ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ ብለዋል፡፡
ፀረ ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል የተለያዩ የዓለም አገሮች ፖሊሲዎችን አውጥተዋል፡፡ ስትራቴጂዎችንም ነድፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የ16ቱ ቀናት ፀረ ፆታዊ ጥቃት ንቅናቄ አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡
የ16ቱ ፀረ ፆታዊ ጥቃት ንቅናቄ ቀናት የተጀመረው በአሜሪካ ኢንኩዊንተሮ ግዛት ነው፡፡ መነሻ ምክንያቱ ደግሞ በወቅቱ ከአሜሪካ ጋር የጠለቀ ግንኙነት በነበራት ዶሜኒካ ሪፐብሊክ መሪ የነበረውን የትሩጂሎ አምባገነናዊ ሥርዓት በመቃወማቸው በግፍ ለተገደሉ ለሦስት እንስት እህትማማቾች (ፓትርሺያ፣ ሚመኔርቫና ሚራባል) ለተባሉ ጀግኒቶች መታሰቢያ እንዲሆን ነበር፡፡
በአገረ ካናዳ ሞንትሪያል ኩቤክ ከተማ ‹‹በኢኮል ፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ›› የተፈጸመ የ14 ሴቶች ጭፍጨፋ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ፆታዊ ጥቃት ይቁም ለሚለው ዘመቻ መነሻም ሊሆን ችሏል፡፡
የ16 ቀናት ፀረ ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ በመጀመሪያው የሴቶች ዓለም አቀፍ የአመራር ተቋም (Women’s Global Leadership Institute) መሪነት እ.ኤ.አ. በ1991 የተጀመረ ነው፡፡ የጉባዔው ታዳሚዎች የዘመቻው መነሻ ቀን ኖቬምበር 25 እንዲሆንና የንቅናቄው ማብቂያ ዲሴምበር 10 ሆና በእነኚህ መካከል በሚገኙት 16 ቀናት በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን አፅንኦት ለመስጠት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የ16ቱ ቀናት ፀረ ፆታዊ ጥቃት ንቅናቄ ‹‹ዘመቻ በፆታዊ ጥቃት በኢትዮጵያ›› በሚል እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ በኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት መሪነት በአገር አቀፍ ደረጃ ፆታዊ ጥቃትን ለመቀነስና ለማስቆም የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡