Written by  Administrator

“በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በራስ ተነሳሽነት ራሱን ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ጥረት ሊደገፍና ሊበረታታ እንጂ እንደወንጀል ሊቆጠር አይገባም” - እናት ፓርቲ

እናት ፓርቲ ትናንት ህዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በኦሮሚያ ክልል፣ ምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ የአንዶዴ ዲቾ እና ደጋ ጂጊ ቀበሌዎች ነዋሪዎች “መከላከያ ሰራዊት ነን” ያሉ ሃይሎች ሰኞ ህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ከንጋት 12 ሰዓት እስከ ጠዋት 3 ሰዓት በድንገት ከበባ በማድረግ ከ80 የማያንሱ የጦር መሳሪያዎቻቸውን እንደገፈፏቸው መናገራቸውን ገልጿል። ፓርቲው “በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በራስ ተነሳሽነት ራሱን ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ጥረት ሊደገፍና ሊበረታታ እንጂ እንደወንጀል ሊቆጠር አይገባም” ሲልም አመልክቷል።

ፓርቲው በርካታ አርሶ አደሮች “መሳሪያችንን አንሰጥም” በማለት ጫካ እንደገቡና መሳሪያዎቹን ነጥቀው “የራሳችን” ለሚሉት ሰው “ሰጥተውታል” በማለት እንዳማረሩ “ሰምቼአለሁ” ያለው ፓርቲው፣ “የዞንና ወረዳ ካድሬዎችም ጫካ የገባውን ቤተሰቡን ‘እናስራለን፣ እንቀጣለን’ እያሉ እንደሚዝቱ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል” በማለት አስረድቷል። “በአካባቢው ከፍተኛ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ የተከሰተበት በመሆኑ ራስን መከላከል በሕግና በሥርዓት እንዲመራ ማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደኾነ መታወቅ አለበት” ብሏል፣ እናት ፓርቲ በመግለጫው።

እናት ፓርቲ “የጸጥታ ሃይሉ ትርጉም ያለው ጥበቃ ለዜጎች በማያደርግበት ሁኔታ ነዋሪው ራሱን የሚከላከልበትን መሳሪያ መቀማት በቅርቡ በአርሲ የተከሰተው ዓይነት ጥፋት ለማድረስ ካልሆነ፣ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው እንደማይችል ታውቆ የእርምት እርምጃ በአስቸኳይ እንዲወሰድ” ሲል ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ “በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በራስ ተነሳሽነት ራሱን ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ጥረት ሊደገፍና ሊበረታታ እንጂ እንደወንጀል ሊቆጠር አይገባም” በማለት አጽንዖት ሰጥቶ ነው ያመለከተው።