ማኅበራዊ
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መድኃኒት እጥረት የፈጠረው ሥጋት

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: December 8, 2024

በምስራቅ ደረጄ

በዓለማችን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተሠራጩ መሆናቸውን የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች 74 በመቶ የሚሆነውን የሞት ምጣኔም ይይዛሉ።

በኢትዮጵያም ከሚከሰተው የሞት ምጣኔ 41 ከመቶ ያህሉ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ጋር የተያያዘ መሆኑን የጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር ከዚህ ቀደም ማስታወሱ አይዘነጋም፡፡ በሕክምና ተቋማት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ተጠቅተው የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ መምጣቱ፣ ከዚም ጋር ተያይዞ መድኃኒቶችን ፍለጋ ወደ ተለያዩ መድኃኒት ቤቶች የሚጎርፉ ተካሚዎች መጠናቸው መጨመሩም አንዱ የበሽታው ሥርጭት ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምን ምን ናቸው? መድኃኒቶቹስ ለምን ያህል ጊዜ ነው የሚወሰዱት? የሚለውን ጥያቄ ሪፖርተር በቀበና ጤና ጣቢያ ውስጥ በፋርማሲስትነት የሚያገለግሉትን አቶ ቢኒያም ዓባይን ጠይቆ ነበር፡፡ እንደ ባለሙያው፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በበሽታ አምጪ ተዋህስያን የማይከሰቱ፣ ከአንዱ ወደ ሌላው በንክኪ ወይም በተለያየ መንገድ የማይተላለፋ፣ በአኗኗር፣ በዕድሜ እንዲሁም በጄኔቲክስ የሚመጡ ናቸው፡፡

መድኃኒቶቻቸውም የሚቋርጥ ሳይሆን ለሕይወት ዘመን የሚወሰድ ነው፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ የምንላቸው በሽታዎች አሁን ላይ በዓይነት እየበዙ እንደሆነና ስኳርን፣ አስምን፣ የልብ ሕመምን፣ የደም ግፊትንና የሚጥል በሽታን መጥቀስ ይቻላል ብለዋል።

ከመድኃኒት አቅርቦትና ተደራሽነት ጋር በተያያዘ ላነሳንላቸው ጥያቄ፣ ‹‹መድኃኒት አቅርቦት አለ፡፡ ግን ተደራሽ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የልብ መድኃኒቶችና የካንሰር መድኃኒቶች በቀላሉ አይገኙም፡፡ ቢገኙ እንኳን ዋጋቸው ውድ ነው። ከደም ግፊት መድኃኒቶች ውስጥ ኢናላፕሪል የተባለው እጥረት ካጋጠመ ወደ አራት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ የአስም መድኃኒት የሆነውና ለአስም ሕክምና በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ቤክታሶል ከጠፋ ወደ ስድስት ወራት ሆኖታል። ዋጋውም በጣም ውድ ነው፡፡ አንድ ፍሬ በ1,000 ሺሕ ብር እየሸጥን ነው። የካንሰር መድኃኒት በአገር አቀፍ ደረጃ እጥረት አለ፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር በጤና ጣቢያው በተገኘበት ወቅት ቁጥራቸው በርከት ያሉ ታካሚዎች እነዚህን መድኃኒቶች ፍለጋ ወደ ጤና ጣቢያው ፋርማሲ እንደሚመጡ ማስተዋል ችሏል። በኢትዮጵያ ወስጥ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዋነኛ የጤና ሥጋት ሲሆኑ፣ በአገሪቱ ለሞት ከሚዳርጉት መካከልም በቀዳሚነት ተጠቃሾች ናቸው።

ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል ከአንድ ዓመት በፊት ባወጣው ጥናት መሠረት፣ ከመቶ ሺሕ ሰዎች፣ 554ቱ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የተጠቁ ሲሆን፣ በአንድ ሰዓት ውስጥ 25 ሰዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ።

እነዚህን በሽታዎች ለመቆጣጠር ወሳኝ የሆኑ መድኃኒቶች እጥረት፣ የዋጋቸው መወደድ፣ የመድኃኒት ተጠቃሚዎች የኑሮ ሁኔታን ያማከለ አለመሆን በእጅጉ እንዳሳሰባቸው የተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ሲገልጹ ይስተዋላሉ።

የመድኃኒቶች እጥረትና የዋጋቸው ተመጣጣኝ አለመሆን ምን ዓይነት ሥጋት እንደሆነ ተጠቃሚዎችን አነጋግረን ነበር፡፡

ወ/ሮ በድሪያ ያሲን የ77 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ፣ የስኳር መድኃኒት የሆነው ሜትፎርሚን ተጠቃሚ ናቸው። እሳቸው እንደገለጹትም፣ መድኃኒቱን ለሰባት ዓመታት ያለ ማቋረጥ ተጠቅመዋል። መድኃኒቱን ለማግኘት ግን ሁለት ቀናትና ከዚያ በላይ መፈለግ አለባቸው፡፡ ተፈልጎም ሚታጣበት ጊዜ አለ። በመሆኑም በጣም ከፍተኛ ሥጋትን ፈጥሮባቸዋል፡፡ ‹‹ጠፋ በተባልንበት ወቅት በጣም ብዙ ተሽከርክረን ግዴታ ስለሆነ በተባልነው ዋጋ እንገዛለን፤›› የሚሉት ወ/ሮ በድሪያ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ በሁሉም ፉርማሲዎችና ከነማዎች ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ቢመቻችላቸው ከትልቅ ሥጋትና ጭንቀት ሊላቀቁ እንደሚችሉ አክለዋል፡፡

የ45 ዓመቷ የሺ ገላው የንግድ ባንክ ሠራተኛ ናት። የደም ግፊት መድኃኒት ተጠቃሚ የሆነችው አስተያየት ሰጪያችን እንደገለጹት፣ የመድኃኒቱ ዋጋ ጨምሯል፣ እስከ 400 ብር ድረስ ደርሷል። የጤና ጣቢያ ፋርማሲዎች ውስጥ ስለማይኖር ከውጪ ግዙ ይባላሉ፡፡ ነገር ግን ውጪ ላይም አይገኝም። የተለያዩ ከነማዎች ዞረው መድኃኒቱን ባገኙት ዋጋ ይገዛሉ። የጤና መድኅን ተጠቃሚ ቢሆኑም መድኃኒቱ ከነማ ውስጥ በብዛት ስለማይገኝ፣ በግል ፋርማሲ ከመግዛት ውጪ አማራጭ የላቸውም፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ካፌ ውስጥ በገንዘብ ያዥነት የምታገለግለው ፋሲካ መንግሥቴ፣ በመድኃኒት አለመገኘት ምክንያት ሥጋት ውስጥ ከሚወድቁ ተጠቃሚዎች አንዷ ናት፡፡ የስኳር መድኃኒት የሆነውን ኢንሱሊን ተጠቃሚዋ ፋሲካ፣ ‹‹በጤና መደኅን ነው መድኃኒቱን የምወስደው፡፡ ዋጋው እምብዛም አይቸግረኝም፡፡ ነገር ግን የለም የምባልበት ጊዜ ይኖራል። በፍለጋ ብዙ ከነማዎችን እዞራለሁ። መድኃኒቱን ጠዋትና ማታ በቀን ሁለት ጊዜ የግዴታ ማግኘት አለብኝ፣ ካልሆነ ችግር ይፈጥራል፤›› በማለት ትገልጻለች፡፡

የጠፉ መድኃኒቶች እነ ማን ናቸው? የሚለውን ሪፖርተር ወደ ተለያዩ ፋርማሲዎች በመሄድ ጠይቋል።

በቀበና ፋርማሲ ውስጥ ፋርማሲስት የሆኑት አቶ ደስአለኝ አማረ አንደገለጹት፣ ‹‹የልብ መድኃኒት የሆነው ኢቫስ እንዲሁም ታይሮክሲን፣ የአስም መድኃኒት የሆነው ቤክሎሜታሶንና የስኳር መድኃኒት የሆነው ጋልቨስሜት በገበያ ላይ እንደሌሉና ዋጋቸውም ተመጣጣኝ እንዳልሆነ አስረድተውናል፡፡ በተጨማሪም፣ የልብ መድኃኒት የሆነውን ሜቶፕሮል 14 ፍሬ በ1,000 ብር እንደሚሸጡና ይህ በጣም ውድ ዋጋ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በቱሉ ዲምቱ ታተስ መድኃኒት ቤት በፋርማሲስትነት የሚሠራው አቶ ኢዮብ አይቼው እንደነገረን፣ ‹‹እኛ ጋር ለስኳር የምንጠቀመው ኢንሱሊን ካለቀ ቆይቷል፡፡ ወደ 5 ወራት ሆኖታል። ሰሞኑን ደግሞ ለልብና ለደም ግፊት የምንጠቀመው ኢናላፕሪል ጠፍቷል፡፡ ሌሎች መድኃኒቶች እየገቡ ሲሆን፣ ይህ መድኃኒት ግን እየገባ አይደለም፤›› ሲል ገልጾልናል።

በመደኃኒት እጥረት ምክንያት ታካሚዎች በአስፈላጊው ጊዜ መድኃኒት ሳያገኙ እንደሚቀሩ ይናገራሉ። ይህም ላልተፈለገ እንግልትና ወጪ፣ አልፎ ተርፎም ለበሽታ እስከ መጋለጥ ያደርሳል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የመድኃኒት አቅራቢዎች፣ የግል እንዲሁም የሕዝብ መድኃኒት ቤቶችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ከምንጊዜውም በላይ በተቀናጀ ሁኔታ ቢሠሩ ለታካሚው የተሻለ ዕረፍትን እንደሚፈጥሩ ያነጋገርናቸው ተጠቃሚዎች ገልጸዋል፡፡