ሕገ መንግሰት እና የኢትዮጵያ ካርታ ከተወሰኑ ቃላት ጋር

8 ታህሳስ 2024

የዛሬ ሰላሳ ዓመት፤ ኅዳር 29/1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ለዓላማዎቻቸው እና እምነቶቻቸው ማሰሪያ የሚሆነውን ሰነድ አጸደቁ።

አስራ አንድ ምዕራፎች፣ 106 አንቀጾች ያሉት ይህ ሰነድ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ ጉራማይሌ መልክ አለው። ሕገ መንግሥቱን “አገሪቱን ቀውስ ውስጥ ከቷል” የሚሉ ትችቶች እንዳሉ ሁሉ፤ “እንከን የማይወጣለት” ነው ሲሉ የሚያወድሱትም አሉ።

በአንድ በኩል አሁን ያለችው ኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ምሰሶ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱን ወደ ገደል ከትቶ እንድተፈርስ ሊያደርግ የሚችል እንደሆነ የሚናገሩ ሰዎች አሉ።

ያም ተባለ ያ ሕገ መንግሥቱ ሥርዓትን ገንብቷል።

አንዳንድ ጊዜ ይህ ሥርዓት የእምቧይ ካብ ባሕሪ ይይዛል። ማዕካለዊ መንግሥቱን የተቆጣጠረው አካል ጠመንጃ አንጋቾችንም ጋዜጠኞችን “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ በመንቀሳቀስ” ይከስሳል።

ልማታዊው ኢህአዴግም፤ ርዕዮተ ዓለም አልባው ብልጽግናም እነዚህን ክሶች ያቀርባሉ።

ነገር በሕገ መንግሥቱ እና እሱ በገነባው ሥርዓት የ30 ዓመት ታሪክ ውስጥ የተናደ ሥርዓትም የፈረሰ ሕገ መንግሥትም የለም። በተቃርኖ የተሞላው፣ ውግዘት እና ውዳሴ የማያጣው ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን እስካሁን አስተዳድሯል።

ከኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በፊት ኢትዮጵያ በሦስት ሕገ መንግሥቶች ተዳድራለች።

ይህ ሕገ መንግሥት ባለፉት 30 ዓመታት ምን አሳካ? ምን ውስንኖችስ ነበሩበት? ዕጣ ፈንታው ምን ይሆናል?

የዘመናዊ ሕገ መንግሥት ታሪክ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት በንጉሡ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ተረቅቆ በ1923 ዓ.ም. ነው የጸደቀው። የንጉሡን ትዕዛዝ ተቀብለው ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁት እርሻ እና ወታደራዊ ሳይንስ የተማሩት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ናቸው።

አቶ ሚኪያስ በቀለ የተባሉ የሕግ ባለሙያ፤ “ሕግ አወጣጥ እና ሕዝባዊ ተሳትፎ በኢትዮጵያ” በተሰኘ ጥናታቸው፤ ንጉሡ ሕገ መንግሥቱን ያወጡት “ሀገሪቷ ተራማጅ እና ሥልጡን መሆኗን ለዓለም ለማስታዋወቅ” መሆኑን ይገልጻሉ።

ይህ ሕገ መንግሥት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እና የሕግ መምሪያ ምክር ቤት የሚባሉ ሁለት ምክር ቤቶችን አቋቁሟል።

ሆኖም ግን የሕግ መንግሥት ማውጣት እና ማርቀቅ ሂደቱ አሳታፊ እና የማኅበረሰቡን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባ አልነበረም። እንዲያውም ይባስ ብሎ ንጉሡ የመጀመሪያውን ሕገ መንግሥት “ለተወዳጁ ሕዝባቸው በስጦታ” ማበርከታቸውን ሕገ መንግሥቱን ባወጁበት ቀን ተናግረው ነበር።

ይህ ሕገ መንግሥት ለ25 ዓመታት ከቆየ በኋላ በ1948 ዓ.ም. ተሻሽሏል።

ጀርመን አገር በሚገኘው የማክስ ፕላንክ ኢንስቲትዩት ፒ.ኤች.ዲ ተማሪ ሆኑት አቶ አብዱለጢፍ ከድር፤ “[ማሻሻያው] ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመጡት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን ታሳቢ ያደረገ እንዲሁም አዲሱን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ፌዴሬሽንን ከግምት ያስገባ” መሆኑን ይገልጻሉ።

አቶ ሚኪያስ በቀለ ይህ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፤ “ከተመረጡ ኮሚቴዎች እና የዘውድ ምክር ቤት አባላት ውጪ ማኅበረሰቡ እንዲወያይበት የተደረገ ጥረት አልነበረም” ይላሉ።

የ1948ቱን ሕገ መንግሥት ሁለት ጊዜ ለማሻሻል ሙከራዎች መደረጋቸውን አቶ ሚኪያስ በጥናታቸው ላይ አስፍረዋል። በመጀመሪያ ማሻሻያውን ለማድረግ የተሞከረው የንዋይ ወንድማማቾች ካደረጉት የመንፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ነው።

ሁለተኛው ማሻሻያ የተሞከረው በንጉሡ የመጨረሻ ዓመታት ነበር። ይህ ማሻሻያ ከበፊቶቹ ሕገ መንግሥቶች አንጻር ተራማጅ ሊባል የሚችል ነበር።

አቶ አብዱለጢፍ ይህ ማሻሻያ፤ “የንጉሣዊውን ሥርዓት ወደ ሕገ መንግሥታዊ የዘውድ ሥርዓት ለማሸጋገር ያሰበ ረቂቅ [ነበር]” ይላሉ።

ማሻሻያው በንጉሡ ሥልጣን እና ስያሜ ላይም ለውጥ ያመጣ ነበር። ረቂቅ ማሻሻያው “ንጉሠ ነገሥቱ የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር እና የሕዝቡ አንድነት እና የታሪኳ ምልክት ነው። ሥልጣኑ እና ተግባሩም በዚህ ሕገ መንግሥት እንደተወሰነው ይሆናል” ሲል ሥልጣናቸው ላይ ገደብ ያስቀምጣል።

ነገር ግን ይህ ሕገ መንግሥቱ ሳይጸድቅ አብዮቱ ፈነዳ። አብዮቱን ተከትሎ ሥልጣን የያዙት ወታደሮች ንግሡንም፣ ዘውዳቸውንም፣ ረቂቅ ሕገ መንግሥቱንም ታሪክ አደረጓቸው።

መለዮ ለባሾቹ፣ ጠመንጃ አንጋቾቹ መኮንኖች የንጉሡን ዙፋን ከወረሱ በኋላ ሕገ መንግሥት ለማውጣት ብዙም አልቸኮሉም። አብዮቱ ፋታ አልሰጣቸው አሊያም ወታደራዊ ባህሪያቸው አልፈቀደላቸው ይሆናል። ብቻ ኢትዮጵያን ያለ ሕገ መንግሥት ለ13 ዓመታት አስተዳደርዋል።

ደርግ በ13 ዓመታቱ ውስጥ አገሪቱን ያስተዳደረው በአዋጆች እና በደንቦች ነበር። አቶ አብዱለጢፍ እነዚህ አዋጆች እና ደንቦች ከፊል መንግሥታዊ ባህሪ ነበራቸው ይላሉ።

ደርግ ከሥልጣን ሊወገድ አራት ዓመታት ሲቀሩት ለኢትዮጵያ ሦስተኛ የሆነውን ሕገ መንግሥት በ1979 አጸደቀ።

አቶ አብዱለጢፍ፤ “[ሕገ መንግሥቱ] በሶሻሊስት ንድፈ ሃሳብ የተቃኘ፤ ዋና ችግር ብሎ የለየውን የመደብ ግንኙነት ማስተካካል የሚል ዓላማ ይዞ የጸደቀ ነው” ይላሉ።

ሕገ መንግሥቱ በጸደቀበት ጊዜ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥተኛ ተሳተፎ ባዘጋጀው ራሱ ባጸደቀው እና በመረጣቸው እንደራሴዎቹ አማካኝነት ሙሉ ሕጋዊ ኃይል ባገኘው አዲስ ዓይነት ሕገ መንግሥት መተዳደር ጀምሯል” ብለው ነበር።

ኮሎኔሉ ይህን ካሉ ከአራት ዓመታት በኋላ ግን እርሳቸው ወደ ዚምባብዌ፣ ነጻ አውጪ ታጋዮቹ ደግሞ ወደ አራት ኪሎ ገብተዋል።

የሕገ መንግሥት ረቂቅ ላይ ከተደረጉ ውይይቶች መካከል
የምስሉ መግለጫ,13 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች በ1987ቱ ሕገ መንግሥት ረቂቅ ላይ ውይይት አድርገዋል

የ1987 የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት

ደርግ ተሸንፎ ከሥልጣን ሲገለል የማዕከላዊ መንግሥትን ሥልጣን የተቆጣጠሩት በብሔር የተደራጁ የነጻ አውጪ ድርጅቶች ነበሩ። አቶ አብዱለጢፍ እነዚህ ድርጅቶች፤ “የኢትዮጵያ የባህሎች እና የቋንቋ ቡድኖች እንዲሁም በብሔር፣ ብሔረሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት የተዛባ ነበር፤ ዋናው የኢትዮጵያ ህጸጽም እሱ ነው፤ እሱን ማስተካከል ይገባል ብለው ነው ወደ ትጥቅ ትግል የሄዱት” ይላሉ።

ኢህአዴግ ማዕከላዊ ሥልጣን ከተቆጣጠረ አንድ ወር በኋላ በአዲስ አበባ የሰላም እና ዴሞክራሲ ጉባኤ ተካሄዷል። በብሔር የተደራጁ ኃይሎች የተሳተፉበት ይህ ጉባኤ የሽግግር ጊዜ ቻርተር እና የሽግግር ጊዜ ምክር ቤትን ወልዷል።

ይህ የሽግግር ቻርተር ከአራት ዓመት በኋላ የጸደቀው የአገሪቱን ሕገ መንግሥት አቅጣጫ ያመላከተ ነበር። ቻርተሩ ለብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ ነጻነት” ሰጥቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ቻርተሩ የሽግግር ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን እንደሚያቋቁም እና የሕገ መንግሥት ረቂቅ እንዲዘጋጅ እንደሚያደርግ ሰፍሯል።

ተጓዳ አለባቸው የተባሉ የሕግ ባለሙያ ከ13 ዓመታት በፊት በሠሩት የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናት 23 ሺህ ገደማ በሚሆኑ ቀበሌዎች በረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ላይ ውይይቶች መደረጋቸውን አስፍረዋል።

ስለ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ቅቡልነት በጻፉት በዚህ ጥናታቸው ተጓዳ፤ 13 ሚሊዮን ሰዎች በረቂቁ ውይይት ላይ መሳተፋቸውን ጽፈዋል።

በኢትዮጵያ የሕግ አወጣጥ ሂደት ላይ ሕዝባዊ ተሳትፎን ያጠኑት አቶ ሚኪያስ በበኩላቸው፤ “የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አወጣጡ አሳታፊ አለመሆኑ እሙን ነው” ይላሉ።

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማግስት የነበሩ ዓለም አቀፋዊ እና ቀጠናዊ የርዕዮተ ዓለም ጉዳዮች ሕገ መንግሥቱን ላይ መንጸባረቃቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በተለይ የሌኒን እና የሶቭየት ኅበረት የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አስተሳሰብ ሕገ መንግሥቱ ላይ በጉልህ ይንጸባረቃል።

የሕገ መንግሥት እና አስተዳደር ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አደም ካሴ ከቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት በኋላ የናኘው የመድብለ ፓርቲ እና የመብት እሳቤ በሕገ መንግሥቱ አንድ መልክ መሆኑን ይገልጻሉ።

በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች ፕሮግራም ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አባድር ኢብራሂም “የኢህዴግ መሪዎች ማርክሲስቶች ቢሆኑም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በዋናነት የሊበራል ሰነድ መሆኑን አያጠራጥርም” ይላሉ። ለዚህ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ የተከሰተውን የሦስተኛው የዴሞክራታይዜሽን ማዕበል መለያዎችን መያዙንም ያነሳሉ።

እነዚህ መለያዎች የመድብለ ፓርቲ ምርጫ ሥርዓት፣ የሥልጣን ክፍፍል እና ገደብ ማስቀመጥ፤ እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ዋና ኦዲተር፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያሉት ማቋቋም መሆናቸውን ያስረዳሉ።

አቶ አብዱለጢፍ “በሕግ የበላይነት የሚመራ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚለው አንደኛ የሊብራል አስተሳሰብ አካል ነው” ሲሉ የዶ/ር አባድርን ሃሳብ ያጠናክራሉ።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግጅት “በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት” ዓላማ እንዳለው መግቢያ ላይ ሰፍሯል።

ዶ/ር አደም ካሴ በበኩላቸው “በምዕራቡ እና ምሥራቁ ካምፕ ከነበረው ታሪካዊ ተጽዕኖ የተነሳ ሕገ መንግሥቱ ምንም ዓይነት አገራዊ መልክ የሌለው የሁለቱ ጎራዎች አስተሳሰብ ቅይጥ ነው” ይላሉ።

በምዕራባውያን ድጋፍ አራት ኪሎ የገቡት የነጻ አውጪ ድርጅቶች ሕገ መንግሥቱን ያቆሙት በብሔር ማንነት እና ራስን በራስ በማስተዳደር ሃሳብ ላይ ነው። ዶ/ር አደም በሕገ መንግሥቱ “ኢትዮጵያ ብዙ ሕዝቦች ያሉባት አገር” ተደርጋ መሳሏን ይገልጻሉ።

አክለውም፤ “የሕዝቦች አገር ተደርጋ ከተገለጸች በኋላ፤ በጨቋኞች እና በተጨቋኝ ብሔሮች ትርክት ላይ ራሷን መሠረተች” ይላሉ። አሁን “እነዚህ ጉዳዮች መጀመሪያ ላይ ከተነሱበት ጊዜ በበለጠ ስር ሰድደዋል” ይላሉ።

የሕገ መንግሥቱ ፀሐፊዎች ይህን ሃሳብ የወረሱት በ1960ዎቹ ከነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ ነው።

እንደ ዶ/ር አባድር ገለጻ የአሁኑ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋስዖ መነሻ የሆነው የተማሪዎች ንቅናቄ በርካታ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች የተደረቱት በመሬት፣ በመደብ፣ ብሔር ጥያቄ ማዕቀፍ ነበር።

የተማሪዎቹን አብዮት የጠለፈው ደርግ እና ከተማሪዎቹ የወጡት ኢህአዴጎች አብዮተኞቹ ያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት አድርገዋል።

ደርግ በሕገ መንግሥቱ ሊመልስ የሞከረው የመደብ ጥያቄን በሕገ መንግሥቱ ለመመለስ መሞከሩን ይገልጻል። በ1979 የወጣው የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት የሚጀምረው “እኛ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ሕዝብ…” ብሎ ነው።

ከ30 ዓመታት በፊት የወጣው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ደግሞ “እኛ ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” የሚል መግቢያ አለው።

በሕገ መንግሥት ቀረጻው ሂደት ላይ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ በአንድ ወቅት፤ “ሕገ መንግሥታችን ዴሞክራሲያዊ ራስ ገዝነትን እና የተገደበ የመንግሥት ሥልጣንን ያከብራል፣ ለሕህዝብ ሉዓላዊነት ከፍተኛ ቦታ ይሰጣል” ሲሉ ተናግረው ነበር።

የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ
የምስሉ መግለጫ,”[ሕገ መንግሥቱ] ሕዝብ በቀጥተኛ በራሱ ተሳትፎ የመረጣቸው የመንግሥት ተወካዮች በተሰጣቸው ገደብ እና ሥልጣን ለሕዝብ ሉዓላዊነት ተጠሪ እንዲሆኑ ይጠይቃል” ፕ/ር እንድሪያስ።

ሕገ መንግሥቱ ባለፉት 30 ዓመታት ምን አሳካ?

አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ዕድሜውን ሙሉ የውዝግብ እና የተቃውሞ ማዕከል ሆኖ ነው ያሳለፈው። አንደኛው ተቃውሞ የሚነሳው ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያን ታሪክ እና አገረ መንግሥት ከተረዳበት አኳኋን ነው።

በተለይ “መጪው የጋራ ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረም እና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል…” የሚለው ሐረግ ብዙ ተቃውሞ ገጥሞታል።

አቶ አብዱለጢፍ፤ “የተዛባ የብሔር ግንኙነት የሚለውን ማስተካከል በሚለው ደረጃ እንደ legitimate ዓላማ ከታየ እኔም በተወሰነ መልኩ legitimate ነው ብዬ አስባለሁ” ይላሉ። ጨምረውም “የማንነት ልዩነቶችን በብሔር ደረጃ የበለጠ በማብቃት ከሰፊው ሕዝብ እስከ ልሂቁ የተለያየ ዓይነት የተጠቃሚነት ደረጃ ቢኖርም ይሄንን በተወሰነ መልኩ አስተካክሏል” ሲሉ ያክላሉ።

ለዚህም ብዙ ሰዎች በቋንቋቸው መማር፣ መዳኘት እና መንግሥታዊ አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ያነሳሉ።

ከዚህ በተጨማሪ “ከዚህ በፊት ከነማንነታቸው ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ሲመጡ ታይተው የማይታወቁ ዓይነት ሰዎች እና ባህሎች በግልጽ አሁን መምጣት ጀምረዋል” ሲሉ አብዱለጢፍ የሕገ መንግሥቱን ትሩፋት ያነሳሉ።

ሕገ መንግሥቱ “ለብሔር ብሔረሰቦች መብት የሰጠ ሥርዓት ነው” የሚሉት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዶ/ር ሚልኬሳ ሚደጋ “ሕገ መንግሥቱ ቢያንስ ክልሎችን አዋቅሯል። እነዚያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች ደግሞ በፈለጉት ቋንቋ እንዲማሩ፣ እንዲተዳደሩ እና እንዲዳኙ አድርጓል” ይላሉ።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የፌደራሉ መንግሥት በክልሎች የተዋቀረ መሆኑን ያትታል። በሕገ መንግሥቱ መሠረት “ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ በቋንቋ፣ በማንነት እና በፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው።”

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለቀዱ የሕገ መንግሥት ባለሙያ ደግሞ ይህ የፌደራል ሥርዓት “ለዘመናት የቆዩ የአካታችነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ለብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ክልላዊ ቡድኖች ትልቅ የፖለቲካ ራስን በራስ የማስተዳደር እንዲሁም በፌዴራል ተቋማት ውስጥ ፍትሃዊ ውክልና ለመስጠት ቃል ገብቷል” ይላሉ።

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የኢትዮጵያ ሪፐብሊክ በፌደራል መንግሥት እና በክልሎች የተዋቀረ ነው። ሕገ መንግሥቱ በፌደራል መንግሥቱ እና በክልሎች መካከል ያለውን የሥልጣን ክፍፍል ዘርዝሯል። ክልሎች የራሳቸውን ሕገ መንግሥት የማውጣት እና የአስተዳደር እርከኖችን የማዋቀር ሥልጣን አላቸው።

ሕገ መንግሥቱ የፌደራል መንግሥቱን በመሠረቱት ክልሎች ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች “በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት” እንዳለቸው ይደነግጋል።

ከዚህ በተጨማሪ በሕገ መንግሥቱ ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ “የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው” ሲል ሕገ መንግሥቱ ያትታል።

ሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ካለው ሐረግ ቀጥሎ ይህ አንቀጽ ብዙ ተቃውሞ ሲገጥመው ይስተዋላል።

አቶ አብዱለጢፍ ይህ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ከታሪካችን ወረስን የሚሉት “የተዛባ ግንኙነት” ተመልሶ እንደማይመጣ ማረጋገጫው ነው” የሚል መከራከሪያ የሚያነሱ መኖራቸውን ይገልጻሉ።

ፕሮፌሰር እንድሪያስ “ሕገ መንግሥቱ የበላይ ሕግ ከመሆኑም በላይ የሕዝብን ሉዓላዊነት በማንኛውም ከራስ ገዝነት እስከ መገንጠል ይፈቅዳል በዚህም ከብዙዎች ሕገ መንግሥቶች ይለያል” ብለው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ “የመንግሥት ሥልጣን በአንድ አካል ስር እንዳይከማች ብዙ ጥረት ተደርጓል” ያሉት ፕ/ር እንድሪያስ፤ “ሕገ መንግሥቱ በተጨማሪ ለሕዝቦች እና ብሔረሰቦች ከፍተኛ ሥልጣን እና ነጻነት ይሰጣል” ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላው የሕገ መንግሥቱ ስኬት ተብሎ ሚነሳው በአንጻራዊነት የተረጋጋ ሥርዓት መገንባቱን ነው። “በኢህአዴግ ጊዜ በአንጻራዊነት ሰላም ነበር” የሚሉት ዶ/ር ሚልኬሳ፤ “ሙሉ በሙሉም ባይሆን በተወሰነ ደረጃ ውክልና ነበር። ከፊል ቅቡልነትም ነበረው” ሲሉ ለቢቢሲ ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

አቶ አብዱለጢፍ በተመሳሳይ፤ “ብዙ ሰዎች ‘ከ1983 ወዲህ ያለው የኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዓት ከተወሰኑ ግጭቶች በስተቀር በአብዛኛው የተረጋጋ ነው። ይህ መረጋጋት የሥርዓት ስኬት ነው” የሚሉ አስተያየቶች እንደሚደመጡ ይናገራሉ።

“ነገር ግን ይህ [መረጋጋት] ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሳይሆን በአንድ ፓርቲ ጥርነፋ የመጣ ነው” ሲሉ ይተቻሉ። የሕግ ባለሙያው አክለውም፤ “ይህ ማለት ኢህአዴግ ገዢ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የብሔር ልሂቃን ፍላጎቶቻቸውን እያነሱ የሚፋተጉበት ቦታ ነበር ማለት ነው” ይላሉ።

ሕገ መንግስትና የተወሰዱ አንቀጾች

የሕገ መንግሥቱ ህጸጾች. . . አተገባበር ወይስ አጻጻፍ?

አቶ አብዱለጢፍ የሕገ መንግሥቱ ትልቅ ህጸጽ “ግለሰብን የሚያይበት መንገድ ነው” ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ መዋቅሩ የቡድን መብትን መሠረት ሲያደርግ “የሰዎች መብት፣ ግዴታ እና ጥቅም የፖለቲካ ተሳትፎ በአብዛኛው በቡድን መነጽር ብቻ ነው የታየው” ሲሉ ይተቻሉ።

ሕገ መንግሥቱ “የቡድኖች እኩልነት ላይ የተሻለ ሥራ ሠርቷል” የሚሉት አብደለጢፍ፤ “የግለሰቦች እኩልነት እንዴት ይረጋገጣል የሚለው ላይ ትልቅ ክፍተት አለ። ክፍተት ብቻ ሳይሆን ቀውስም ነው። አሁን ያለውን [ፖለቲካዊ] ቀውስ ከዚህ አንጻር ነው እኔ የማየው” ይላሉ።

ሕገ መንግሥቱ በአንድ ሙሉ ምዕራፍ የግለሰብ መብቶችን መዘርዘሩን የሚጠቅሱት አቶ አብዱለጢፍ፤ ነገር ግን ‘ለእነዚያ መብቶች ጥበቃ የሚያደርጉ ተቋማትን አሽመድምዶ ነው የጀመረው” ሲሉ ይናገራሉ።

“ፍርድ ቤትን ጨምሮ እነዚህ መብቶች ሊጠብቁ ይችሉ የነበሩ ተቋማት ኃይል እንዳይኖራቸው ተደርገዋል” በማለት፤ “ሕገ መንግሥቱ በዋናነት የብሔር ብሔረሰቦች ነው ስለተባለ የብሔር ብሔረሰቦች ውክልና ላለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው በባለቤትነት የተሰጠው” ሲሉ ያክላሉ።

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፌደራሉ መንግሥት አባል ክልሎች የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚልኳቸው አባላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነው። ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ለምክር ቤቱ ነው የተሰጠው። የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤን የማደራጀት ሥልጣንም አለው።

ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅ ሂደት ውስጥ ይህ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳይ ክርክር ካሰነሱ ጉዳዮች መካከል እንደነበር በአርቃቂ ኮሚሽኑን አማካሪ የሙያ ኮሚቴ ውስጥ የነበሩት መዓዛ አሸናፊ በአንድ ወቅት ገልጸው ነበር።

ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ በሕገ መንግሥቱ ቀረጻ ወቅት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ካደረጉ ግለሰቦች መካከል አንዱ ነበሩ። ፕ/ር እንድሪያስ “ለአጽዳቂ ጉባኤው ሕገ መንግሥታዊ ችሎት ቢኖረን ይሻላል እና ሕገ መንግሥቱን መተርጎም ለፌደራል አካሉ መተው ችግር ይኖረዋል ብዬ ሃሳብ አቅርቤ ነበር” ሲሉ ከአራት ዓመታት በፊት ተናግረዋል።

ነገር ግን “የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን ሉዓላዊነትን አጎልቶ ለማክበር እና ለማስከበር የሕገ መንግሥት ጥያቄዎች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢቀርቡ ይሻላል” የሚለው ሃሳብ ገዢ ሆኖ መጽደቁን ፕሮፌሰሩ አስታውሰዋል።

አቶ አብዱለጢፍ ይህ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሥርዓት “የግለሰብ መብትን ማስጠበቅ አልቻለም። ከዚያ ባለፈ የብሔር፣ ብሔረሰቦችን እና የቡድን መብት የሚባለውንም ከመጠበቅ አንጻር በአወቃቀሩም በንድፈ ሃሳብም እንደማይችል ግልጽ ነው” ይላሉ።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የሕገ መንግሥት ምሁር፤ የሥልጣን ክፍፍል ትርጉምን በተመለከተ አለመግባባቶችን ለመፍታት የመጨረሻውን ቃል የመስጠት ሥልጣን ለፌደራል መንግሥት ወይም ለክልሎች መሰጠት የለበትም ይላሉ።

ምሁሩ አክለውም በሕገ መንግሥቱ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን፤ “በከፋ ማዕከላዊነት እና የአንድ ፓርቲ የበላይነት እየተሰቃየ ሲሆን፣ ክልላዊ መንግሥታት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡትን የራስ ገዝ አስተዳደር ለማስመለስ ብዙም ስኬት ሳያገኙ ትግላቸውን ቀጥለዋል” ይላሉ።

“ፌዴሬሽኑን ከፌዴራል መንፈስ ጋር ባገናዘበ መልኩ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ለማድረግ ሕገ መንግሥቱን የሚተረጉም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወይም ሕገ መንግሥታዊ ችሎት ያስፈልጋል” ሲሉም ያክላሉ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ላይ
የምስሉ መግለጫ,”ሕገ መንግሥቱ በዋነኛነት የብሔር ብሔረሰቦች ነው ስለተባለ የብሔር ብሔረሰቦች ውክልና ላለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው በባለቤትነት የተሰጠው” አቶ አብዱለጢፍ

ሕገ መንግሥቱን እና ሥርዓቱን ሊጠብቅ የሚችል ተቋማዊ ዋስትና ከሌለ ሕገ መንግሥቱ የአንጃዎችን ጥቅም ብቻ የሚያገልግል ጥቅም አልባ መጽሐፍ እንደሚሆን ባለሙያው ይገልጻሉ።

ባለሙያው “አንድ ዜጋ የመንግሥት ተቋማትን በመብት ጥሰት ሲሞግት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔው በአብዛኛው በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት የሚደግፍ ነው” ይላሉ።

“አንድ የመንግሥት አካል የራሱን ሥልጣን እና ጥቅም በሚመለከት ዳኝነት ሊቀመጥ አይገባውም” የሚል የዴሞክራቲክ ሕገ መንግሥታዊ መርኅ መኖሩን ከአራት ዓመታት በፊት ያስታወሱት ፕ/ር እንድሪያስ፤ “አንድ የመንግሥት አካል ስለ ራሱ ሥልጣን እና የሥልጣን ገደብ ዳኝነት ይቀመጣል ይህ የሚፈጥረው ችግር ይኖራል” ሲሉ ተናግረው ነበር።

ነገር ግን የሕገ መንግሥቱ ህጸጽ ከትርጉም ጋር የተያያዘ ብቻ አይደለም።

ዶ/ር አደም ካሴ ዋናው ህጸጽ ሕገ መንግሥቱ ከተጸፋበት እና ከጸደቀበት ሂደት ይመነጫል ይላሉ። ሕገ መንግሥቱ “የእውነተኛ ድርድር እና ምክክር ውጤት ሳይሆን፣ ወታደራዊ ድል ባገኙ የፖለቲካ ተዋናዮች የጸደቀ” መሆኑን ያነሳሉ። በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ዕጣ ፈንታው “ሕገ መንግሥቱን በሚደግፉ ቡድኖች ወታደራዊ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ነው” ሲሉ ያክላሉ።

የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች ተባባሪ ዳይሬክተሩ ዶ/ር አባድርም በዚህ ሃሳብ ተስማምተው “ሕገ መንግሥቱ የነበረበትን የቅቡልነት እና የዴሞክራሲያዊ አሳታፊነት ችግር መፍታት ይችል ነበር ይላሉ።

እንደ ዶ/ር አባድር ገለጻ፤ የሕገ መንግሥቱ ትልቁ ውድቀቱ “በትክክል አለመተግበሩ እና ለዴሞክራሲ ሥርዓቱን እና የሕግ የበላይነት ጨምሮ የሕገ መንግስቱ ጥንካሬዎች በፖለቲካ አገዛዝ መተካቱ ነው።”

“የዴሞክራሲ እጦት ሌላኛው የሕገ መንግሥቱ ህጸጽ ነው” የሚሉት ዶ/ር ሚልኬሳ በበኩላቸው “በዚህ ሳቢያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ሉዓላዊ ሥልጣን መተግበር አልቻሉም” ይላሉ።

ዶ/ር ሚልኬሳ፤ “ምርጫ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ሉዓላዊ ሥልጣናቸውን የሚገልጹበት ሂደት ነው። እስካሁን ይህን ሥልጣናቸውን መተግበር አልቻሉም። ዴሞክራሲ በሌለበት አገር ‘ሉዓላዊ ሥልጣን ለብሔር፣ ብሔረሰቦች ተሰጥቷል’ የሚለው ወረቀት ላይ ነው የሚቀረው” ሲሉ ያብራራሉ።

ሕገ መንግሥቱ ከነ ስኬት እና ህጸጾቹ 30 ዓመት የአገሪቱ የበላይ ሕግ ሆኖ አገልግሏል። ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ምን ያህል አስፈላጊ ነው የሚል ጥያቄ ይቀርብበታል።

አቶ አብዱለጢፍ “1987 ዓ.ም. የነበረው እና አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ዋናው ማዕከል የሆነውን የብሔር ግንኙነት ጭምር ተቀያይሯል” ይላሉ።

“አሁን ያለውን የኃይል አሰላለፍ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት [ሕገ መንግሥቱ] እንደ አዲስ ሌላ ድርድር እና ውይይት የሚያስፈልገው በብዙ መልኩ መሬት ላይ ያሉት ሁኔታዎች ያረጀ ያፈጀ ያደረጉት ይለስለኛል” ሲሉ ያክላሉ።

ሕገ መንግሥቱ በብዙ ሰዎች ዘንድ ያለውን ቅቡልነት ከግምት ውስጥ በማስገባት “መሠረታዊ አቅጣጫውን እንደያዘ መቀጠል አለበት የሚለው አብዛኛው ሰው የሚስማማበት ነው” ይላሉ አብዱለጢፍ።