ባሻር አል-አሳድ
የምስሉ መግለጫ,ባሻር አል-አሳድ

8 ታህሳስ 2024, 12:08 EAT

በፕሬዝዳንት ባሻር አል-አሳድ ሕይወት ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸው ክስተቶች ብዙ ናቸው።

ቤታቸው አቅራቢያ የደረሰባቸው የመኪና አደጋ አይረሴ ከሚባሉ ክስተቶች አንዱ ነው።

ከአባታቸው ሥልጣንን ለመረከብ እየተዘጋጁ አልነበረም። ታላቅ ወንድማቸው ባሲል ከሞተ በኋላ ነው ለሥልጣን መታጨት የጀመሩት።

ደማስቆ አቅራቢያ ነው የመኪና አደጋው የተከሰተው። እአአ በ1994። በወቅቱ አሳድ በለንደን የዓይን ሕክምና እያጠኑ ነበር።

ባሲል ከሞተ በኋላ ታናሽ ወንድም የሆኑት አሳድ ሶሪያን ለመምራት መሰናዳት ያዙ።

ሶሪያን በደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ መርተዋል። በጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ በሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል።

ከዓይን ሐኪምነት በጦር ወንጀል እስከተከሰሰ አምባገነን መሪነት ድረስ ያለው የባሻር አል-አሳድ ሕይወት ምን ይመስላል?

አባትና ልጅ

ባሻር አል-አሳድ የተወለዱት እአአ በ1965 ነው። አባታቸው ሐፊዝ አል-አሳድ እናታቸው ደግሞ አኒሳ ማቅሀሉፍ ናቸው።

ሲወለዱ ሶሪያ በመካከለኛው ምሥራቅ አብዮታዊ ለውጥ ውስጥ ነበረች።

የአረብ ብሔርተኛነት የቀጣናውን ፖለቲካ ተቆጣጥሮት ነበር። ሶሪያም ይህንኑ አካሄድ ትከተል ነበር።

በግብፅና ሶሪያ መካከል የነበረው ውህደት (ከ1958–1961) ሲከስም ባሐት ፓርቲ ሥልጣኑን ጨበጠ።

ፓርቲው የአረብ ብሔርተኛነትን ያቀነቅን ነበር። በሶሪያ በወቅቱ ዴሞክራሲያዊነትና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አልነበረም።

የአሳድ ቤተሰብ የአለዋይት ማኅበረሰብ አካል ነው። በሶሪያ ድሃ ከሆኑ ማኅበረሰቦች አንደኛው ነው። የማኅበረሰቡ ተወላጆች አማራጭ በማጣት የሶሪያን ወታደሮች ይቀላቀሉም ነበር።

ሐፊዝ አል-አሳድ የወታደርነት እርከንን ወጥተው ከፍተኛ አመራር ላይ ደረሱ።

የባሐት ፓርቲ ቀንደኛ ደጋፊ ነበሩ። እአአ በ1966 መከላከያ ሚኒስትር ሆኑ።

በ1971 ፕሬዝዳት ከሆኑ በኋላ በ2000 እስከሚሞቱ ድረስ ሥልጣነ መንበሩን ተቆናጠዋል።

ሶሪያ ነጻ ከወጣች በኋላ ረዥሙ አገዛዝ ነው።

ብዙ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች ተሞክረዋል። ሐፊዝ አል-አሳድ ግን አንቀጥቅጠው ሶሪያን ገዝተዋል።

ተቃዋሚዎችን ሲያሳድዱ፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫንም አልቀበልም ብለዋል።

በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግን ተራማጅ ነበሩ። ከሶቪየት ኅብረት ጋር ቅርብ ቢሆኑም በ1991 የገልፍ ጦርነት ወቅት አሜሪካ መራሹን ቡድን ተቀላቅለዋል።

ሐፊዝ አል-አሳድ
የምስሉ መግለጫ,ሐፊዝ አል-አሳድ አንቀጥቅጠው ሶሪያን ገዝተዋል

ሕክምና በለንደን

ባሻር አል-አሳድ ከፖለቲካም ከወታደርነትም ርቀው ሕክምናን መረጡ።

ከደማስቆ ዩኒቨርስቲ ከተመረቁ በኋላ በ1992 ወደ ዩናይትድ ኪንግደም አቀኑ።

በለንደን ዌስተርን አይ ሆስፒታል ውስጥ የዓይን ሕክምና ተምረዋል።

ቢቢሲ በ2018 በሠራው ‘ኤ ዴንጀረስ ዳይናስቲ፡ ዘ አሳድስ’ በተባለው ዘጋቢ ፊልም ላይ ባሻር አል-አሳድ በለንደን ሕይወትን ሲያጣጥሙ ይታያል።

ምዕራባዊ ኑሮ ተመችቷቸው ይስተዋላሉ። የሚያደንቁት ድምጻዊ ፊል ኮልንስን ነው።

ባለቤታቸው አስማ አል-አክራስን የተዋወቁትም ለንደን ነው።

አስማ በኪንግስ ኮሌጅ የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ነበረች። ከዚያም በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪ ለመማር ተቀባይነት አግኝታለች።

ባሽር በታላቅ ወንድማቸው ባሲል ተሸፍነው ቆይተዋል። ባሲል ሲሞት ግን ከለንደን ወደ ሶሪያ እንዲመለሱ ተደገ።

የሶሪያ ቀጣይ መሪ ለመሆን ዝግጅቱ ተጀመረ።

ባሲል እአአ በ1994 ሲሞት የባሽር ሕይወት እስከወዲያኛው ተለውጧል።

ባሽር ወታደር ሆነው በሕዝቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እንዲጨምር የገፅታ ግንባታ ተጀመረ።

አስማ አል-አክራስ
የምስሉ መግለጫ,በፕሬዝዳንት ባሻር አል-አሳድ ባለቤታቸው አስማ አል-አክራስን የተዋወቁት ለንደን ነው

የለውጥ ሕልም

ሐፊዝ አል-አሳድ ሰኔ 2000 ሲሞቱ የ34 ዓመቱ ባሽር አል-አሳድ ፕሬዝዳት ሆኑ።

ባሽርን ፕሬዝዳንት ለማድረግ ፕሬዝዳት ለመሆን የሚያስፈልገው የዕድሜ ገደብ ከ40 ዝቅ ብሎ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ተደርጓል።

አሳድ ሥልጣን ሲይዙ አዲስ የፖለቲካ አካሄድ ጀመሩ። ግልጽነት፣ ዴሞክራሲ፣ ለውጥ፣ ዘመናዊነት፣ ተጠያቂነትና ተቋማዊ አሠራር እንደሚኖር ተናገሩ።

ሥልጣን ከያዙ ከወራት በኋላ ከአስማ ጋር ተጋቡ። ሐፊዝ፣ ዘይን እና ከሪም የተባሉ ልጆች አፍርተዋል።

አሳድ ሥልጣን ሲይዙ ቃል የገቡት ነጻነትና የፖለቲካ ለውጥ ለበርካታ ሶሪያውያን ተስፋ ፈንጥቆ ነበር።

የአስማ ምዕራባዊ ትምህርትና የአሳድ ተስፋ ሰጪ ንግግር ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ጠቁሟል። ለተወሰነ ጊዜ በሶሪያ የንግግርና የሐሳብ ክርክር ታይቷል። ይህም ‘ደማስንስ ስፕሪክግ’ ይሰኛል።

በ2001 ግን የፀጥታ ኃይሎች አፈና ጀመሩ። የተቃውሞ ድምጾች ይጨቆኑ ጀመር።

አሳድ ውስን የምጣኔ ሃብት ለውጥ ሲያደርጉ በግሉ የንግድ ዘርፍ መነቃቃት ተስተውሎበት ነበር።

የአጎታቸው ልጅ ረሚ ማክህሉፍ ሰፊ የምጣኔ ሃብት ቁጥጥር ማድረግ የጀመሩት በዚህ ወቅት ነው። ሥልጣንና ሃብት ለመጣመራቸው ምክንያት የረሚ ገናና መሆን ነው ብለው የሚያምኑ ተንታኞች አሉ።

ለግማሽ ምዕተ ዓመት ሶሪያን የመራው የአሳድ ቤተሰብ
የምስሉ መግለጫ,ለግማሽ ምዕተ ዓመት ሶሪያን የመራው የአሳድ ቤተሰብ

ኢራቅ እና ሊባኖስ

እአአ በ2003 የኢራቅ ጦርነት በአሳድና በምዕራባውን አገራት ግንኙነት ውስጥ ጣልቃ ገባ።

አሜሪካ መራሹን የኢራቅ ወረራ ፕሬዝዳንቱ አወገዙ። ሶሪያ ቀጣይዋ የአሜሪካ ዒላማ ትሆናለች ብለው እንደፈሩ ይታመናል።

አሜሪካ በበኩሏ ሶሪያ የሕገ ወጥ መሣሪያ ዝውውርን በመፍቀድ አሜሪካ በኢራቅ ያላትን ይዞታ የሚገዳደሩ ኃይሎችን ደግፋለች ስትል ከሳለች።

በሁለቱ አገራት መካከል ጽንፈኞች እንዲዘዋወሩ ሶሪያ መፍቀዷንም አሜሪካ ታምናለች።

በ2003 አሜሪካ ሶሪያ ላይ ማዕቀብ ጣለች። ለዚህም ምክንያቱ ከኢራቅ ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን በሊባኖስ ውስጥ የነበረውን የሶሪያ ጦርም መነሻ በማድረግ ጭምር ነበር።

በ2005 የቀድሞው የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ራፊቅ ሀሪሪ ተገደሉ። ሀሪሪ በሊባኖስ ቀዳሚ የሶሪያ ተቃዋሚ ነበሩ። የተገደሉት በማዕከላዊ ቤሩት ፍንዳታ ነበር።

ከፍንዳታው ጀርባ ሶሪያና አጋሮቿ እንዳሉ ይታመናል።

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ራፊቅ ሀሪሪን ግድያ ተከትሎ በሊባኖስ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነሳ።

ዓለም አቀፍ ጫና ሲበረታ ሶሪያ ጦሯን ከ30 ዓመታት በኋላ ከሊባኖስ አስወጣች።

ዓለም አቀፍ ችሎት በ2020 የሄዝቦላህን አባል በሀሪሪ ግድያ ተጠያቂ ቢያደርግም፣ አሳድ እና የሊባኖስ አጋራቸው ሄዝቦላህ በሀሪሪ ግድያ እጃቸው እንደሌለበት ተናግረዋል።

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ራፊቅ ሀሪሪ
የምስሉ መግለጫ,የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ራፊቅ ሀሪሪን ግድያ ተከትሎ በሊባኖስ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነሳ።

‘አረብ ስፕሪንግ’

በመጀመሪያዎቹ የአሳድ አገዛዝ ዓመታት የሶሪያ እና ኢራን ወዳጅነት ተጠናክሯል።

ሶሪያ ከኳታርና ቱርክ ያላት ግንኙነትም ጨምሯል። ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያለው ግንኙነት በብዙ ከፍና ዝቅ አልፏል።

አሳድ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የአባታቸውን ፈለግ ተከትለው ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ላለመግባት ሞክረዋል።

ዓሥርታትን ያስቆጠረው የአሳድ አገዛዝ አምባገነናዊ ነው። የተቃውሞ ድምጾች ታፍነዋል።

በ2010 የአሳድ ባለቤት አስማ ለቮግ መጽሔት በሰጠችው ቃለ ምልልስ ቤታቸው “በዴሞክራሲ” እንደሚመራ ገልጻለች።

ቱኒዚያዊው አትክልት ሻጭ ሞሐመድ ቦአዚዚ በፖሊስ በጥፊ ከተመታ በኋላ ራሱን ያቃጠለው በዛው ቀን ነበር።

ይህም በቱኒዝያ ፕሬዝዳንት ዚን ኢል አቢዲን ቢን አሊን ከሥልጣን የፈነቀለ አብዮት አስነስቷል።

የቱኒዝያ አብዮት በአረብ አገራቱ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ባሕሬን እና ሶሪያ አብዮትን አቀጣጥሏል።

በ2011 ቮግ ‘ኤ ሮዝ ኢን ዘ ዴዘርት’ ወይም የበረሃ ጽጌረዳ በሚል ያወጣውን ቃለ ምልልስ ኋላ ላይ ሰርዟል።

በቃለ ምልልሱ ሶሪያ ከፍንዳታ፣ ከአፈናና ውጥረት ነጻ አገር ተብላ ተገለጻለች።

ከቃለ ምልልሱ ከወራት በኋላ ነገሮች ተለዋወጡ።

በደማስቆ አብዮት ተነሳ። በደቡባዊቷ ከተማ ዳራ ሕጻናት አሳድን የሚቃወም መፈክር ካሰሙ በኋላ መታሰራቸውን ተከትሎ ተቃውሞው ተቀጣጠለ።

ከሁለት ሳምንት በኋላ አሳድ በምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ሶሪያን ዒላማ ያደረገውን “አሻጥር” እንደሚያስወግዱና የሕዝብ ፍላጎት እንደሚሟላ አስታወቁ።

በዳራ ተቃዋሚዎች ላይ ፖሊሶች መተኮሳቸው ተቃውሞውን አባባሰው። አሳድ ሥልጣን እንዲለቁ ግፊት በረታ።

ለተቃውሞው መነሻ “የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ጫና” ነው በሚል የመንግሥት ኃይሎች ተቃውሞውን በኃይል ማፈን ቀጠሉ።

በወራት ውስጥ የመንግሥት ኃይሎችና ተቃዋሚዎች መካከል ወታደራዊ ግጭት ተነሳ።

የቱኒዝያ አብዮት በአረብ አገራቱ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ባሕሬን እና ሶሪያ አብዮትን አቀጣጥሏል
የምስሉ መግለጫ,የቱኒዝያ አብዮት በአረብ አገራቱ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ባሕሬን እና ሶሪያ አብዮትን አቀጣጥሏል

ጂሃዲስቶችና የጦር ወንጀል

የመንግሥታቱ ድርጅት እንዳለው፣ ግጭቱ መባባሱን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነትም ጨምሯል።

ሩሲያ፣ ኢራን እና በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች ከአሳድ ጎን ሲቆሙ ቱርክ እና የገልፍ አገራት ተቃዋሚዎችን ደግፈዋል።

አሳድን የሚቃወሙ ሰዎች ጥያቄያቸው የዴሞክራሲ መስፈንና የነጻነት ነበር። ሆኖም ግን ብዙም ሳይቆይ ተቃዋሚዎች በአለዋይትና በሱኒ መካከል ተከፋፈሉ።

የቀጣናው አገራት ድጋፍ የሰጡት በተከፋፈለው ቡድን ባላቸው ወገንተኛነት ነበር።

ለኢራን ታማኝ የሆኑ ሺዓ ታጣቂዎች በሄዝቦላይ እየተመሩ ለአሳድ መንግሥት ድጋፋቸውን ቀጠሉ።

ክፍፍሉን ተከትሎ አለዋይቶችን በተመለከተ አደገኛ ትርክቶች በማሰራጨት ሌላኛው ቡድን ትግሉን ገፋበት።

በጎረቤት አገር ኢራቅ ደግሞ የእስልምና ሕግን በአክራሪነት የሚተገብረው ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ንቅናቄውን አጠናከረ።

የእርስ በእርስ ጦርነቱን ተከትሎ አይኤስአይኤስ በሶሪያ ግዛቶችን ይዟል። ምሥራቃዊቷ የሶሪያ ከተማ ራቃ መዲናው እንደሆነች አይኤስ አውጇል።

በ2013 በተቃዋሚዎች ይዞታ ሥር ባለችውና ከደማስቆ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ምሥራቃዊቷ ከተማ ጉታ በደረሰ የኬሚካል ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል።

ምዕራባውያንና የአሳድ ተቃዋሚዎች ለጥቃቱ የአሳድን አስተዳደር ተጠያቂ አድርገዋል።

የአሳድ አስተዳደር ይህንን አስተባብሏል። በዓለም አቀፍ ጫና ምክንያት የኬሚካል መሣሪያዎችን አስወግዷል።

ሆኖም ግን ይህ እርምጃ ጦርነቱን አላቆመውም። በሶሪያ ጦርነት የኬሚካል ጥቃት ቀጠለ።

ተመድ ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች መግደል፣ መድፈርና ማሰቃየትን ጨምሮ የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸው ገልጿል።

በ2015 የአሳድ አስተዳደር የአገሪቱን የተለያዩ አካባቢዎች መቆጣጠር ባለመቻሉ ለመውደቅ ተቃርቦ ነበር። ሆኖም ሩሲያ ጣልቃ ገብታ ቁልፍ ግዛቶች በአሳድ ቁጥጥር ሥር መልሰው እንዲገቡ አስችላለች።

ግጭቱ መባባሱን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል
የምስሉ መግለጫ,ግጭቱ መባባሱን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል

የጋዛ ጦርነት

ከ2018 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት በቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት የመንግሥት ኃይሎች አብዛኛውን ሶሪያ ተቆጣጥረዋል።

ኢስላሚስት ተቃዋሚዎችና የኩርድ ታጣቂዎች ደግሞ ሰሜናዊና ሰሜን ምሥራቅ አካባቢን ይዘዋል።

ወደ ሊባኖስ የተስፋፋው ጦርነት የአሳድ ዋነኛ ደጋፊ ሄዝቦላህን ወደ ጋዛ ጦርነት አስገብቷል
የምስሉ መግለጫ,ወደ ሊባኖስ የተስፋፋው ጦርነት የአሳድ ዋነኛ ደጋፊ ሄዝቦላህን ወደ ጋዛ ጦርነት አስገብቷል

ስምምነቶቹ የአሳድን አስተዳደር አጠናከሩ። አሳድ ወደ አረብ አገራት የዲፕሎማሲ ጠረጴዛም መመለስ ቻሉ።

በ2023 ሶሪያ መልሳ የአረብ ሊግን እንድትቀላቀል ተወሰነ። የአረብ አገራት በደማስቆ ኤምባሲዎቻቸውን መልሰው ከፈቱ።

የሶሪያ ምጣኔ ሃብት ቢሽመደመድም የአሳድ አገዛዝ ወደ ሦስት ዓሥርታት ተሻገረ።

አሳድ ከባድ ፈተና ያለፉ ይመስል ነበር።

ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሲፈጽም ግን የጋዛ ጦርነት ተጀመረ።

ወደ ሊባኖስ የተስፋፋው ጦርነት የአሳድ ዋነኛ ደጋፊ ሄዝቦላህን ወደ ጋዛ ጦርነት አስገብቷል።

የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስረላህ መገደልን ጨምሮ የጋዛ ጦርነት ሄዝቦላህን ዋጋ አስከፍሏል።

ሄዝቦላህ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ለማድረግ የተስማሙ ዕለት በሐያት ታሕሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) አማጽያን የሚመሩ የሶሪያ ተቃዋሚዎች ድንገተኛ ጥቃት በሶሪያ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ አሌፖ ከፍተዋል።

አማጽያኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀማ እና ሌሎችም ከተሞችን መቆጣጠር ችለዋል። በአሳድ መንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩ ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎችን አማጽያኑ ይዘዋል።

የአሳድ ተቃዋሚዎች ጠንካራ ይመስላሉ። የአሳድ ዋነኛ ደጋፊዎች ኢራን እና ሩሲያ አስተዳደሩን ላይታደጉት ይችላሉ።

አሁን የብዙኃን መነጋገሪያ የሆኑት አሳድ ይህንን ጠንካራ ተቃውሞ ያልፉት ይሆን? ወይስ ሥልጣናቸው ያከትምለታል? የሚሉት ዋነኛ ጥያቄዎች ናቸው።

 ባሻር አል-አሳድ
የምስሉ መግለጫ,ባሻር አል-አሳድ