የሶሪያው አማጺ መሪ አቡ መሐመድ አል-ጃውላኒ
የምስሉ መግለጫ,የሶሪያው አማጺ መሪ አቡ መሐመድ አል-ጃውላኒ

8 ታህሳስ 2024, 11:05 EAT

የእስላማዊው ታጣቂ ቡድን ሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) ተዋጊዎች ድንገተኛ ጥቃት ከፍተው በቀናት ውስጥ በርካታ ከተሞችን በመቆጣጠር የሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ ገብተዋል።

በኤችቲኤስ የሚመሩ ታጣቂዎች ወደ ዋና ከተማዋ ሲገሰግሱ ሶሪያን ከአባታቸው ተረክበው ለዓመታት አንቀጥቅጠው የገዙት ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ ከአገር ሸሽተው ወጥተዋል።

የታጣቂ ቡድኑ ኤችቲኤስ መሪ አቡ መሐመድ አል-ጃውላኒ የሰብአዊ መብት ረገጣ ፈጽሟል በሚል ይከሰሳል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለዘብተኛ መሆኑን የሚያሳይ ምሥል ለዓለም ሕዝብ ለመፍጠር እየሞከረ ቢሆንም ዩናይትድ ስቴትስ መሪውን ለያዘ ሰው 10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ለመስጠት የገባችውን ቃል እንደጠበቀች ነው።

አማጺ ቡድኑ በመንግሥት ላይ ጥቃት መፈጸም ጀምሯል
የምስሉ መግለጫ,አማጺ ቡድኑ በመንግሥት ላይ ጥቃት መፈጸም ጀምሯል

የአል-ጀውላኒ መነሻ የት ነው?

አቡ መሐመድ አል-ጀውላኒ የውሸት ስም ነው። ትክክለኛው ስሙ እና ዕድሜው አከራካሪ ነው።

አል-ጃውላኒ ለአሜሪካው ፒቢኤስ እንደተናገረው ከሆነ አህመድ አል ሻራአ ይባላል፣ ቤተሰቦቹም ከጎላን አካባቢ የመጡ ሶሪያዊ ናቸው።

የተወለደው በሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ ነው። በወቅቱ አባቱ ሪያድ ይሠሩ ነበር። ያደገው ግን ደማስቆ እንደሆነ ተናግሯል።

የተወለደው በምሥራቅ ሶሪያዋ በዲር ዞር ውስጥ እንደሆነ የሚገልጹ ዘገባዎችም አሉ። እስላማዊ ታጣቂ ከመሆኑ በፊት ሕክምና ማጥናቱን የሚገልጹ ወሬዎችም አልፎ አልፎም ቢሆን ይሰማሉ።

በተባበሩት መንግሥታት እና በአውሮፓ ኅብረት ዘገባዎች መሠረት የተወለደው በ1975 እና 1979 መካከል ነው።

ኢንተርፖል በ1979 እንደተወለደ ገልጿል። የአስ-ሳፊር ዘገባ ደግሞ በ1981 መወለዱን ይገልጻል።

አል-ጀውላኒ እንዴት የቡድኑ መሪ ለመሆን በቃ?

እአአ በ2003 በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራው ጥምር ጦር ኢራቅን መውረሩን ተከትሎ አል-ጃውላኒ ወደ በአገሪቱ የሚገኘውን የጂሃዲስት ቡድን አልቃይዳ እንደተቀላቀለ ይታመናል።

ጥምረቱ ፕሬዝዳንት ሳዳም ሁሴንን እና ባዝ የተሰኘውን ፓርቲያቸውን ከሥልጣን አስወገደ። ከተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ግን የተቀናጀ ተቃውሞ ገጥሞታል።

አቡ መሐመድ አል-ጃውላኒ
የምስሉ መግለጫ,አቡ መሐመድ አል-ጃውላኒ

እአአ በ 2010 በኢራቅ የሚገኙ አሜሪካ ወታደሮች አል-ጃውላኒን ይዘውት ከኩዌት ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ቡካ በተሰኘው ጣብያ ውስጥ አሰሩት።

በጣብያው የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) መሪዎችን እና በኋላ ላይ የአይኤስ የኢራቅ መሪ ለመሆን የበቃውን አቡበከር አል ባግዳዲን እንደተዋወቀ ይታመናል።

የፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድን አገዛዝ በመቃወም እአአ በ 2011 በሶሪያ የትጥቅ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ አል-ባግዳዲ ወደ አገሪቱ በመሄድ የድርጅቱን ክንፍ አንዲመሠርት እንዳደረገ አል-ጀውላኒ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።

አል-ጀውላኒ የኑስራ ግንባር (ወይም ጀብሃ አል-ኑስራ) የሚባለው ታጣቂ ቡድን አዛዥ ሆነ። ቡድኑ በድብቅ ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ነበረው። በጦር ሜዳም ብዙ ስኬት አስመዝግቧል።

አል-ጀውላኒ ወደ ሶሪያ በማቅናት ጦር እንዲመሠርት በአቡ ባከር አል-ባግዳዲ ፈቃድ እንደተሰጠው ይታመናል
የምስሉ መግለጫ,አል-ጀውላኒ ወደ ሶሪያ በማቅናት ጦር እንዲመሠርት በአቡ ባከር አል-ባግዳዲ ፈቃድ እንደተሰጠው ይታመናል

አል-ጀውላኒ እአአ በ2013 የኑስራ ግንባር ከአይኤስ ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጦ በአልቃይዳ ቁጥጥር ሥር አዋለው።

ከአልቃይዳ መለያየቱን ደግሞ እአአ በ2016 በተቀረጸ መልዕክቱ ይፋ አደረገ።

እአአ በ 2017 ደግሞ አል-ጃውላኒ ተዋጊዎቹ በሶሪያ ከሚገኙ ሌሎች አማጺ ቡድኖች ጋር በመቀላቀል ሃያት ታህሪር አል ሻምን (ኤችቲኤስ) መመስረታቸውን ተናግሯል። አል-ጀውላኒ አዲሱን ቡድን ይመራል።

የሶሪያ አማጽያን
የምስሉ መግለጫ,የሶሪያ አማጽያን

አል-ጀውላኒ ምን ዓይነት አዛዥ ነው?

በአል-ጃውላኒ መሪነት ኤችቲኤስ በሰሜን ምዕራብ ሶሪያዋ ኢድሊብ እና በአካባቢው ዋነኛው አማጺ ቡድን ለመሆን በቅቷል።

ከተማዋ ከጦርነቱ በፊት 2.7 ሚሊዮን ሕዝብ ቢኖራትም ይህ ቁጥር በተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት ወደ አራት ሚሊዮን ማሻቀቡን አንዳንድ ግምቶች ይጠቁማሉ።

የጤና አገልግሎትን፣ ትምህርትን እና ደኅንነትን በማስጠበቅ በኢድሊብ ግዛት እንደ አንድ የክልል አስተዳር የሚሠራውን “የመዳን መንግሥት” ይመራል።

አል-ጃውላኒ በ2021 ለፒቢኤስ እንደተናገረው ከሆነ የአልቃይዳን ዓለም አቀፍ የጂሃድ ስትራቴጂ አይከተልም።

ዋና ዓላማቸው የሶሪያውን ፕሬዝዳንት አል-አሳድን ከሥልጣን ማባረር ሲሆን ይህንን ዓላማ አሜሪካ እና ምዕራባውያን አገራት እንደሚጋሩት ተናግረዋል።

“ይህ ክልል ለአውሮፓ እና አሜሪካ ደኅንነት ስጋት አይደለም። ይህ ክልል የውጭ ጂሃድ ማስፈጸሚያ መድረክ አይሆንም” ብሏል።

ኤችቲኤስ እአአ በ2020 በኢድሊብ የሚገኘውን የአልቃይዳ ጦር ሰፈር ዘግቷል፤ መሣሪያዎቹን በቁጥጥር ሥር አውሎ የተወሰኑ መሪዎቹን አስሯል።

አይኤስ በኢድሊብ ያሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይም እርምጃ ወስዷል።

አል-ጃውላኒ
የምስሉ መግለጫ,መሐመድ አል-ጃውላኒ

ኤችቲኤስ በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች እስላማዊ ሕግን ቢተገብርም እንደ ጂሃዲስት ቡድኖች ጥብቅ ባልሆነ መንገድ ይተገብረዋል።

ከክርስቲያኖች እና ከሌሎች ሙስሊም ያልሆኑ አካላት ጋር በይፋ ይገናኛል። የጂሃዲስት ቡድኖች በጣም ለዘብተኛ ነው በማለት ይተቹታል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ኤችቲኤስ ሕዝባዊ ተቃውሞን በማፈን እና በሰብአዊ መብት ረገጣዎች ይከሰዋል። አል-ጀውላኒ እነዚህን ክሶች በሙሉ ውድቅ አድርጓል።

ኤችቲኤስ በበርካታ የምዕራብ እና መካከለኛው ምሥራቅ መንግሥታት እና በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጇል።

አል-ጃውላኒ ከአልቃይዳ ጋር ቀድሞ በነበረው ግንኙነት ምክንያት የአሜሪካ መንግስት እሱ እንዲያዝ ለሚሰጥ ማንኛውም መረጃ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጥ አስታውቋል።