

የቱርኪዬ ፕሬዚዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶሃን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድን በአንካራ ካፈራረሙ በኋላ
ዜና የአንካራው ስምምነትና አዲሱ የፖለቲካ ድባብ
ቀን:
December 15, 2024
ረቡዕ ታኅሳስ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት ከቱርኪዬ አንካራ የተሰማው ዜና ከኢትዮጵያዊያን፣ ከሶማሊያዊያን ወይም ከምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች ባለፈ የመላው ዓለምን ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ ላለፈው አንድ ዓመት ወደ ጦርነት ሊገቡ እንደሚችሉ ሲሠጋ የቆየው የሶማሊያና የኢትዮጵያ መሪዎች ሲጨባበጡ መታየታቸው ለሁሉም ወገን ያልተጠበቀ ክስተት ነበር የሆነው፡፡ አምና ታኅሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሶማሌላንድ ፕሬዘዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር በአዲስ አበባ የባህር በር ማግኛ የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ስምምነቱ ከፈጠረው የጂኦ ፖለቲካ እሳት አንፃር ነገሩ ዓመት ሳይደፍን፣ ከሶማሊያ ፕሬዘዳንት ጋር አንካራ ላይ ሌላ ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ አልተገመተም ነበር፡፡

የተባለውን ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር አምና የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረሟ የሶማሊያ መንግሥት የአገሬ ሉዓላዊነት ተጣሰ በማለት ከኢትዮጵያ ጋር ከባድ ውጥረት ውስጥ ገብቶ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በመደራደር ውጥረቱን ለመፍታት በይፋ ስትጠይቅ ቆይታለች፡፡ ይሁን እንጂ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ካልተፋቀ በስተቀር አልደራደርም የሚል ጠንካራ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው የሶማሊያ መንግሥት፣ በቀላሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሌላ አዲስ ስምምነት ይፈራረማል ተብሎ አልተገመተም፡፡ ሆኖም የሶማሊያ ፕሬዘዳንት ሀሰን ሼክም ሆነ መንግሥታቸው የኢትዮ ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ካልተቀደደ ወደ ጠረጴዛ እንደማይመጡ ቢናገሩም፣ ጥብቅ ወዳጃቸው ቱርኪዬ የጀመረችውን ድርድር ግን ገሸሽ ሊያደርጉት አልደፈሩም ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከሶማሊላንድ ፕሬዘዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር እ.ኤ.አ. ጃኑዋሪ 1 ቀን 2024 በአዲስ አበባ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ የባህር በር ዳግም አገኘች የሚል ሰበር ዜና በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ከማስተጋባቱ በስተቀር ግልጽ አልነበረም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ‹‹ፈጣሪ የተመሠገነ ይሁን›› ያሉለት ያ ስምምነት ግን ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ የአገርነት ዕውቅና በመስጠት፣ እንዲሁም እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመሳሰሉ ድርጅቶች ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ በማጋራት በኤደን ባህረ ሰላጤ 20 ኪሎ ሜትር የባህር በር በ50 ዓመት የሊዝ ውል ታገኛለች የሚል ዋና ፍሬ ነገር የያዘ እንደነበር ነው ውሎ አድሮ የተረጋገጠው፡፡
ሶማሌላንድ ለ30 ዓመታት ከሶማሊያ መገንጠሏን በማወጅ እንደ ነፃ አገር ስትኖር የቆየች ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ ጋር ይህን መሰል ስምምነት መፈረሟ ግን የሶማሊያ መንግሥትን ክፉኛ ነበር ያስቆጣውና በኢትዮጵያ ላይ የዲፕሎማሲ ዘመቻ እንዲከፍት ያደረገው፡፡ የሀሰን ሼክ መንግሥት ኢትዮጵያ ስምምነቱን ካልቀደደች ድርድር የሚባል አይታሰብም ሲል በይፋ አስታውቆ ነበር፡፡ የአፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድ፣ ኬንያና ሌሎችም ለቀጣናው ቅርብ የሆኑ ወገኖች የኢትዮጵያና የሶማሊያን ውጥረት በማሸማገል እንፍታ ብለው ሲያቀርቡት የቆየው ጥረት ሳይሰምር ቆይቷል፡፡
የሁለቱ ጎረቤት አገሮች የቃላት ጦርነትና ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ለአራት ወራት ተካሮ ከቀጠለ በኋላ፣ በግንቦት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ቱርኪዬ አንካራ ገቡ፡፡ በዚህ ጉብኝታቸው ወቅትም ቱርኪዬ በጉዳዩ ገብታ እንድታሸማግል ጠይቀው ነበር ተብሏል፡፡ ይህን ተከትሎ ዋናዋ የኢትዮጵያና ሶማሊያ ሸምጋይ ሆና ቀረበች፡፡ ከሁለቱም አገሮች ጋር መልካም ግንኙነት አላት የምትባለዋ ቱርኪዬ ይህ ግንኙነቷና ተፅዕኖ የመፍጠር አቅሟ ማደራደሩን እንዳቀለለላት ነው የተነገረው፡፡
እ.ኤ.አ. ጁላይ 1 ቀን 2024 ዓ.ም. ቱርኪዬ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን እንዲደራደሩ አደረገች የሚለው ዜና የዓለም መነጋገሪያ ሆነ፡፡ በዚህ የቱርኪዬ የመጀመሪያ ዙር የድርድር መድረክ ላይ ከሁለቱ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት መገኘታቸው ከመነገሩ ውጪ እነማን እንደተወከሉም ሆነ በድርድሩ ምን እንደተነሳ በግልጽ ሳይብራራ ነበር የታለፈው፡፡ ያም ሆኖ ግን ለአራት ወራት ኢትዮጵያን ስትወነጅል፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ስታሴር የቆየችዋ ሶማሊያ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ የመጀመሪያ ዙር ድርድር ከኢትዮጵያ ጋር በቱርኪዬ አደረገች መባሉ በራሱ ትልቅ ዕርምጃ ሆኖ ነበር የተቆጠረው፡፡
ቀጥሎ እ.ኤ.አ. የኦገስት 4 ቀን 2024 ዓ.ም. ሁለተኛ ዙር ድርድር መጣ፡፡ በዚህ ዙር ግን እንደቀደመው ጊዜ የተሸፋፈነ ነገር ሳይሆን የቱርኪዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊዳን በወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ (አምባሳደር) ከሶማሊያ አቻቸው ከአህመድ ሞአሊን ፊቂ አህመድ ጋር እያደራደሩ መሆኑ በግልጽ ሲነገርም ተሰማ፡፡ በዚህ የሁለተኛ ዙር ድርድር ላይ የድርድሩ ሒደትንም በተመለከተ ቢሆን መጠነኛ ሐሳቦች ሲንፀባረቁ ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ የባህር ሕጎችን ባከበረ መንገድ በተለይም የተመድን የባህር ሕግ (United Nations Convention on the Law of the Sea) ተከትሎ ድርድሩ መካሄድ አለበት የሚል ሐሳብ መቅረቡ በዚህ ወቅት ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው፡፡ ቀጣዩ ድርድር ደግሞ በመስከረም ወር እንደሚቀጥል ቀጠሮ በመያዝ ነበር ሁለተኛው ድርድር ተገባደደ የተባለው፡፡
ይሁን እንጂ ከዚያ ቀደም በነበሩት ወራት እንደነበረው ሁሉ ይህ የቱርኪዬ አሸማጋይነት በቀጠለባቸው በእነዚያ ወራትም ቢሆን የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት ከመለዘብ ይልቅ የበለጠ ሲካረር ነበር የቀጠለው፡፡ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲን ዘግታ አምባሳደሯንም እስከ ማባረርና ግንኙነት እስከ ማቋረጥ ደርሳ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የባህር በር ስምምነት ስትፈራረም ጀምሮ በሶማሊያ ከተሞች በተካሄዱ የሕዝብ ተቃውሞ ሠልፎች የተጀመረው ቅዋሜ፣ በሶማሊያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርስ ጥቃትን አስከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ የተካረረ የጥላቻ ዘመቻዎችን ፈጥሮ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ሲካሄድ የሶማሊያው ፕሬዘዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ የፈጠሩት አምባጓሮም የሁለቱ አገሮች የፍጥጫ ትኩሳት ደረጃን መለኪያ ሆኖ ነበር፡፡ በእነዚያ ወቅቶች የአየር በረራን የሚያስተጓጉሉ ከባባድ የሲቪል አቪዬሽን ሕግ ጥሰቶች በሶማሊያ በኩል ከመፈጸማቸው በተጨማሪም፣ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንደገና በሌላ ዙር የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንዳይቀጥል ልታደርግ ትችላለች የሚል ዜናም መደመጥ ጀምሮ ነበር፡፡ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ከግብፅ ጋር ከማበር አልፋ ከኤርትራ ጋርም አዲስ አጋርነት ለመፍጠር መጣሯ ሳይበቃ፣ የሶማሊያ መሪዎች በየዓለም አደባባዩ ኢትዮጵያን ማውገዝና ማሳጣት ሥራቸው አድርገውት ነበር የቆዩት፡፡
ይህ ሁሉ ጠላትነትና ግንኙነት መሻከር ቢቀጥልም በቱርኪዬ የሚደረገው ድርድርም ጎን ለጎን ቀጠለ፡፡ እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 17 ቀን 2024 ዓ.ም. ሦስተኛው ዙር ድርድር የሚካሄድበት ቀን መጣ፡፡ ማክሰኞ ዕለት እንደ አመጣቱ መሽቶ ሲነጋ ግን በአንካራ ሲጠበቅ የነበረው ድርድር ሳይደረግ አለፈ፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላ ሐሙስ እ.ኤ.አ. መስከረም 19 ግን የቱርኪዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊዳን አገራቸው በተናጠል ሁለቱን አገሮች ለማነጋገርና ድርድሩን ለማስቀጠል መወሰኗን በይፋ አስታወቁ፡፡
ከሁለቱ አገሮች የቀደሙ ሁለት ዙር ድርድሮች በመነሳት ሦስተኛው ዙር ድርድር የተሻለ ውጤት ይገኝበታል ተብሎ ብዙ ሲባል ቢቆይም፣ የመስከረም መገባደጃው የድርድር ቀጠሮ ባለመካሄዱ ግን ብዙ ተቃራኒ ሐሳብ ጋበዘ፡፡ ቱርኪዬ የምታደርገው አሸማጋይነት የትም አይደርስም የሚል ድምዳሜን ከየአቅጣጫው አሰጠ፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል እየተጠናከረ የመጣውን በተለይም የሶማሊያን የጠላትነት ዲፕሎማሲ ዘመቻ በማከል፣ ሁለቱ ጎረቤት አገሮች ከመታረቅ ይልቅ ወደ ቀጣናዊ ጦርነት ራሳቸውን ሊከቱ ይችላሉ የሚል ሙግት ጉዳዩ ቀሰቀሰ፡፡
የሶማሊያ መሪ ከዚያ ወዲህ በነበሩት ጥቅምትና ኅዳር ወራት አንዴ ካይሮ ሌላ ጊዜ አስመራ በመመላለስ ከአልሲሲና ከኢሳያስ ጋር ፀረ ኢትዮጵያ ግንባር እስከ መፍጠር የደረሰ ዕርምጃ ሲወስዱ ታዩ፡፡ ግብፅ ወደ ሶማሊያ የጦር መሣሪያና ሎጂስቲክስ ላከች የሚለው ዜና ጊዜ እየጠበቀ ጮክ ብሎ መደመጥ ቀጠለ፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ተመድ በሚከታተለው በሶማሊያ በተሰማራው በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ የነበረው ሚና በቀጣይ ዙር እንደማይኖር እርግጠኛ ሆኖ የሚናገረው በዛ፡፡ አሚሶም (AMISOM) እንዲሁም አትሚስ (ATMIS) እየተባለ ለ20 ዓመታት በሶማሊያ የዘለቀው ኢትዮጵያ በሰፊው ስትሳተፍበት የቆየው የኅብረቱ ሰላም አስከባሪ ጦር በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት መግቢያ ከወር በኋላ አውሶም (AUSSOM) በሚል በሌላ የተልዕኮ ስም ሊሰማራ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ተልዕኮ ኢትዮጵያ እንዳትቀጥል ፍላጎቷን ግልጽ ያደረገችው ሶማሊያ፣ ግብፅ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪን የሚተካ አሥር ሺሕ ጦር እንድትልክ እስከመጋበዝ መድረሷ በይፋ ሲነገር ቆይቷል፡፡
በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆኑ አገሮች ሶማሊያ ቀጣናውን በሚገባ ጠንቅቆ የሚያውቀውንና እንደ አልሸባብ ያሉ አሸባሪ ድርጅቶችን በመዋጋት በቂ የሰላም ማስከበር ልምድ ያካበተውን የኢትዮጵያን ጦር ከአዲሱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውጪ እንዲሆን ሶማሊያ ጥረት እንዳታደርግ ሲመክሩ ቆይተዋል፡፡ የሀሰን ሼክ መንግሥት ግን በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ጭምር የኢትዮጵያ ሠራዊት ሉዓላዊነታችንን ጥሶ ወረረን የሚል ክስ ሲያቀርብ ነው የቆየው፡፡ የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ ሰላም ማስከበሩና የተረጋጋ መንግሥት በሞቃዲሾ እንዲመሠረት ማድረጉ ተዘንግቶ፣ ኢትዮጵያን እንዲያውም አልሸባብ እንዲጠናከርና እንዳይደመሰስ የምታደርግ አገር ናት በሚል በሶማሊያ ባለሥልጣናት እስከ መወንጀል ተደርሶ ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ኃይልን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ በግብፅ ጦር የመተካት እንቅስቃሴ ደግሞ፣ ሶማሊያን ከኢትዮጵያ ጋር የተጋጋለ የዲፕሎማሲ ቁርሾ ውስጥ እንድትገባ ነበር ያደረጋት፡፡
የሶማሊያ መንግሥት በሒደት ከሶማሊያ ግዛት አስተዳደሮች ጋር ወደ መጋጨት ውስጥ ገባ፡፡ ከፑንትላንድ ከፊል ራስ ገዝ ግዛት አስተዳደር ጋር በሕገ መንግሥት ማሻሻያና በምርጫ አፈጻጸም ጉዳይ መወዛገብ ቀጠለ፡፡ ብዙም ሳይዘገይ ደግሞ በቅርቡ ከጁባላንድ ግዛት ጋር መጋጨት ጀመረ፡፡ የጁባላንድ ግዛት አስተዳደር ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት የመሠረተ በመሆኑ ብቻ፣ የሀሰን ሼክ መንግሥት የጁባላንድ አስተዳደር ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ መካሄድን እንደ ትልቅ ድፍረት ነበር የቆጠረው፡፡ የጁባላንድ ፕሬዚዳንት አህመድ መሀመድ ኢስላም (አህመድ ማዶቤ) ዳግም መመረጣቸውን ተከትሎ የሞቃዲሾ መንግሥት የእስር ትዕዛዝ እስከ ማውጣትና ጠንካራ ጦር ወደ ጁባላንድ እስከማሰማራት ደረሰ፡፡ በዚህ ውጥረት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ጁባላንድ ጦር አሰማራች የሚል ዜና መሰማት ጀመረ፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ለአንድ ዓመት በቃላት ጦርነት ሲተጋተጉ ቆይተው፣ በጁባላንድ ቀውስ ወደ ወታደራዊ ግጭት ሊገቡ ነው የሚል ግምት መሰንዘር ጀመረ፡፡
የጁባላንዱ ቀውስ ከሁለቱ አገሮች መካረር ባለፈ ብዙ ቀጣናዊ ችግሮችንም የሚያመጣ መሆኑ መነገር ቀጠለ፡፡ ለኬንያ ድንበር በሆነው በጁባላንድ ኢትዮጵያና ሶማሊያ መዋጋት ቢጀምሩ ግጭቱ በቶሎ ወደ ኬንያ ይዘልቃል የሚል ፍራቻም ቀሰቀሰ፡፡ በጁባላንድ የሶማሊያ መንግሥት ያሰማራው ጦር ጥቅም ላይ ማዋል የጀመራቸው ድሮኖችና ሌሎች የጦር መሣሪያዎች በቀጥታ ከግብፅ የመጡ ናቸው የሚል ሪፖርት መውጣት ጀመረ፡፡ ይህን ሪፖርት ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት ለግብፅ ለመላክ የፈቀደውን የወታደራዊ ድጋፍ በቶሎ ማቋረጡ ቢነገርም፣ ነገር ግን በጁባላንድ ቀውስ ጭምር የግብፅ እጅ አለበት መባሉ በራሱ ግጭቱ ከቀጠለ በፍጥነት ቀጣናዊ ቀውስ ይወልዳል የሚለውን ሥጋት የጨመረ ጉዳይ ነበር፡፡
በዚህ መሰል መንገድ ላለፈው አንድ ዓመት ሲከርና ሲባባስ የቆየው የሶማሊያና የኢትዮጵያ ውዝግብ ከሰሞኑ የሁለቱ አገሮች መሪዎች በቱርኪዬ አንካራ ሊገናኙ ነው እየተባለ እንኳን፣ ጋብ ሊል የሚችልበት ዕድል ይፈጠራል ተብሎ አልተገመተም ነበር፡፡ ሆኖም ቀን ቆጥሮ ረቡዕ ምሽት ሲመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ጋር እጅ ሲጨባበጡና ስምምነት ሲፈራረሙ ሳይጠበቅ ታየ፡፡ ይህ ክስተት ዱብ ዕዳ ነበር የሆነው፡፡ የአንድ ዓመቱ ውጥረት አበቃ የሚል መንፈስ ስምምነቱ የሚያሳድር ቢሆንም ነገር ግን በብዙ አቅጣጫዎች ጥያቄ ፈጥሯል፡፡
ከዚህ ጉዳይ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ጉዳይ ያላት ሶማሌላንድ ስምምነቱ ሲፈረም፣ ለስድስተኛውና ለአዲሱ ተመራጭ ፕሬዘዳንት አብዲራህማን መሐመድ አብዱላሂ የበአለ ሲመት ዝግጅት በሀርጌሳ ደግሳ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በልዋጩ የሉዓላዊነት ዕውቅና የሚያስገኝ የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረሟ ሶማሌላንድ ባለፈው አንድ ዓመት ተፈጥሮ የቆየው የዲፕሎማሲ ቀውስ አካል ሆና ነው የዘለቀችው፡፡ ይሁን እንጂ የተካረሩት የሶማሊያና የኢትዮጵያ መሪዎች በአንካራ አዲስ ስምምነት ሲፈራረሙ መታየቱ ሶማሌላንድ ተካደች፣ እንዲሁም ከጫወታ ውጪ ተደረገች የሚል ሙግት ቀሰቀሰ፡፡
በበዓለ ሲመቱ ላይ ሥልጣን ለተተኪያቸው ሲያስረክቡ ንግግር ያደረጉት ተሰናባቹ ፕሬዘዳንተ ሙሴ ቢሂ የሶማሌላንዳዊያንን ስሜት የሚያንፀባርቅ ሐሳብ ማንሳታቸው ተነግሯል፡፡ ‹‹የቱርኪዬ መሪ ኤርዶሃን ዓብይን (ዶ/ር) እና ሀሰንን ሲያጨባብጥ አይተናል፡፡ ሒደቱን እንደ ማንኛውም ሰው በሚዲያ ነው የተመለከትነው፡፡ ሁለቱ አገሮች በጋር ለመሥራት መስማማታቸውንም ሰምተናል፡፡ ይህ የሁለቱ ወገኖች ስምምነት ግን እኛ ከሶማሊያ ጋር ያለንን ጉዳይ አይፈታም፡፡ የእኛ ፍላጎት ነፃነታችንን ማረጋገጥ ነው፡፡ የባህር በሩን ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት ወደንና ፈቅደን እኔ ራሴ ነበርኩ ስምምነት የተፈራረምኩት፡፡ ወደቡን የመጠቀምና ያለ መጠቀሙ ጉዳይ ግን በኢትዮጵያ ፍላጎት ነው የሚወሰነው፡፡ እኛ ከኢትዮጵያም ሆነ ከሶማሊያ ጋር ጎረቤት ነን፡፡ ከጦርነት ርቀን የመኖር ፍላጎት ነው ያለን፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር አሁንም ስምምነት አለን፡፡ እስካሁን ተፈጻሚ ባይሆንም ይህን ስምምነት ደግሞ እንደሚያከብሩት ተስፋ አለን፡፡ ተተኪዬ ይህን ስምምነት እንዲጠብቁ አደራ እላለሁ፤›› በማለት ነበር ተናገሩ የተባለው፡፡
አዲሱ የሶማሊያና የኢትዮጵያ የአንካራ ስምምነት በሞቃዲሾዎች በኩል ፍላጎታችንን አሳካን የሚል ስሜት መፍጠሩ፣ እንዲሁም በሶማሌላንዳዊያን ወገን ደግሞ ተካድን ወይ ተገፋን የሚል መንፈስ መፍጠሩ የሚጠበቅ መሆኑን ነው አንዳንድ ተንታኞች የተናገሩት፡፡ በኢትዮጵያ በኩልም ቢሆን የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት የባህር በር አመጣሁላችሁ ብሎ አሞኘን፣ ከጎረቤቶቻችንም አጣላን የሚል ወገን የመፈጠሩን ያህል፣ በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ፍላጎቷ የሆነውን የባህር በር ጉዳይ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ማድረግ ችላበታለች የሚል ስሜት የተፈጠረባቸውም አሉ፡፡ ኢትዮጵያ በአዲሱ ስምምነት ከቀደመው የመግባቢያ ስምምነት ውጪ ራሷን አለማድረጓን፣ እንዲሁም ከሶማሊያ በተጨማሪ የወደብ አማራጭ ማግኘት የምትችልበት ዕድል መፈጠሩን በመጥቀስ በኢትዮጵያውያን ውስጥ ሙግቱ ቀጥሏል፡፡
አዲሱ ስምምነት ተብሎ በተበተነው ኮሙኒኬ ላይ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የነበራትን ስምምነት ሽራለች የሚል ነገር ፈጽሞ አልሰፈረም፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ የባህር በር የማግኘት መብት እንዳላት በግልጽ ያስነበበው ኮሙኒኬው፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በሶማሊያ የከፈለውን መስዋዕትነት ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡ ያም ቢሆን ግን ኮሙኒኬው ስለሶማሌላንድ ምንም አለማለቱ፣ እንዲሁም ከሶማሌላንድ ጋር ስለተደረገው ስምምነት ዕጣ ፈንታ ምንም ፍንጭ አለመስጠቱ ከየአቅጣጫው በርካታ ግምቶችና ክርክሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡
የአንካራው ስምምነት በተፈረመ ማግሥት ከአስመራም ሆነ ከካይሮ ጥልቅ ዝምታ ነው ያለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሁላችንም ያሸነፍንበትና ቤተሰባዊ ድርድር ውጤት፤›› ሲሉ ስምምነተን ገልጸውታል፡፡ ሶማሊያ ሁሌም የኢትዮጵያ ታማኝ ወዳጅ ነች ሲሉ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ስምምነቱን እንደወደዱት ተናግረዋል፡፡ ከሁሉ በላይ ከባድ ሥጋት ፈጥሮ የቆየውን ጉዳይ በአጭሩ ለስምምነት ያበቃችው ቱርኪዬ ደግሞ በዚህ ስምምነት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ውጤት ማትረፏ ነው የተነገረው፡፡
ኤርዶሃን በበኩላቸው፣ ይህ ስምምነት በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ሰላምና ትብብርን መሠረት ያደረገ አዲስ ጅማሮ እንዲፈጠር ለማድረግ የመጀመሪያው ዕርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ስትፈልገው የቆየውን የባህር በር ማግኘት ጥያቄ የሚመልስ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ የቱርኪዬ የኮሙዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት ዳይሬክተር ሁለቱ አገሮች ያደረጉት ስምምነት የሁለቱንም ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነፃነትና የግዛት አንድነት የሚያስጠብቅ መሆኑን ጠቅሶ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በተለይም የተመድ ቻርተርና የአፍሪካ ኅብረትን ማዕቀፍም ያስከበረ መሆኑን ገልጿል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያና ሶማሊያ ስምምነትን በበጎ እንደተቀበለው አስታውቋል፡፡ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪች ስምምነቱን በደስታ የሚቀበሉት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ቴክኒካዊ ድርድሩን በቀጣይ እንደሚጠብቁ ያስታወቁት ቃል አቀባዩ፣ ሁለቱ አገሮች የተፈራረሙት የመጀመሪያ ስምምነት ወዳጅነትና መተማመንን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሥጊ ችግሮችና አለመግባባቶች ፖለቲካዊ ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት በተሞላ ንግግር ብቻ እንደሚፈቱ ይህ ስምምነት ጠቋሚ እንደሆነ ያመለከቱት ዱጃሪች፣ በቀጣይ ሁለቱ አገሮች ስምምነቱን ለመተግበር የሚያደርጉትን ጥረትም ሆነ ቀጣይ ድርድሮቻቸውን ተመድ ከጎን ሆኖ ለማገዝ ዝግጁ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ባወጡት መግለጫ፣ ስምምነቱ በአስቸኳይ ወደ ትግበራ ሊሄድ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ወደ ስምምነት በመምጣት ጠቃሚ የሆነ ዕርምጃ ቢወስዱም፣ ነገር ግን በዚህ ብቻ መቆም እንደሌለባቸውና በፍጥነት ስምምነቱን ወደ መተግበር እንዲገቡ ነው ያሳሰቡት፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ሊቀመንበር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ በተመሳሳይ ስምምነቱን ጠቃሚ ዕርምጃ ስለመሆኑ ባወጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ ይህ ስምምነት ሁለቱ አገሮች አቻቻይ የሆነ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ለመድረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበት ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ስምምነቱን አወድሰዋል፡፡ ብሊንከን ባወጡት መግለጫ አሜሪካ በቱርኪዬ አደራዳሪነት የተደረገውን የሶማሊያና የኢትዮጵያ ስምምነት በደስታ እንደምትቀበለው የጠቀሱት ብሊንከን ስምምነቱ የሁለቱንም አገሮች ሉዓላዊነት፣ አንድነትና ነፃነት ያረጋገጠ ነው ብለውታል፡፡ ብሊንከን፣ ስምምነቱ በመካሄዱ ቱርኪዬን ያመሠገኑ ሲሆን፣ በቀጣይ በሚደረገው ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባህር በር የምታገኝበትን ዕድል የሚያመቻቸው ድርድር በስኬት እንደሚከናወን ያላቸውን ተስፋም አስታውቀዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ንግግሮችና ግንኙነቶች ለኢትዮጵያም ሆነ ለሶማሊያ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ጀርመንና እንግሊዝም በተናጠል በሰጡት መግለጫ የአንካራውን ስምምነት ደግፈዋል፡፡ የጀርመን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በይፋዊ የኤክስ (ትዊተር) ገጹ በቱርኪዬ አሸማጋይነት ኢትዮጵያና ሶማሊያ በመካከላቸው ውጥረት ፈጥሮ የቆየውን የባህር በር ውዝግብ ለመፍታት መወሰናቸው ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች ሰላም ሰላምና መረጋጋት ጠቃሚ ዕርምጃ መሆኑን ጀርመን እንደምታምን ገልጿል፡፡ በመተማመንና በወዳጅነት መንፈስ የሚደረጉ ቀጣይ ድርድሮችን እንደግፋለን ስትልም ጀርመን ጠቁማለች፡፡
እንግሊዝም በስምምነቱ ቀድመው ተድሰተናል ካሉ አገሮች አንዷ ሆናለች፡፡ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሁለቱ አገሮች አንዱ የሌላውን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ባከበረ መንገድ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አድንቋል፡፡ እንግሊዝ ሁሌም ቢሆን በአፍሪካ ቀንድ መተባበር፣ መረጋጋት፣ ልማትና ብልፅግና እንዲረጋገጥ ድጋፍ ታደርጋለች ሲል ነው በመግለጫው ያስታወቀው፡፡
