ማኅበራዊ
ሳይመዘገቡ ገበያ ውስጥ ሲዘዋወሩ ተገኝተዋል የተባሉ ፀረ ወባ መድኃኒቶች ታገዱ

ኤልያስ ተገኝ

ቀን: December 22, 2024

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ባከናወነው የድኅረ ገበያ ክትትል፣ ያልተመዘገቡ የፀረ ወባ መድኃኒቶች ገበያ ውስጥ ሲዘዋወሩ በመገኘታቸው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አገደ፡፡

ባለሥልጣኑ የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ ለራሱ ቅርንጫፎች ጽሕፈት ቤቶችና ለሁሉም የክልልና የከተማ አስተዳደር የጤና ቢሮዎች በላከው ደብዳቤ እንዳስታወቀው፣ የፀረ ወባ መድኃኒቶቹ በላቦራቶሪ ምርመራ መሥፈርትና ደረጃ ባለማሟላታቸው መታገዳቸውን አስታውቋል፡፡

ኅብረተሰቡ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከተባሉት መድኃኒቶች ውስጥ አንዳቸውም በእጁ ላይ ካሉ ወዲያውኑ መጠቀም እንዲያቆም ያሳሰበው ባለሥልጣኑ፣ መድኃኒቶቹን ለገዛበት ወይም በአቅራቢያው ለሚገኝ የጤና ተቋም መመለስ ይኖርበታል ብሏል፡፡

ባል ፋርማ ሊሚትድ፣ አስኮን ሄልዝ ኬር ኢንዲያ፣ ቲ ኤንድ ጂ ሜዲኬር ኢንዲያ፣ ሃናኖ ኢንዲያ፣ ኬፒሲ ፋርማሲዩቲካል በተባለ የቻይና ኩባንያ፣ እንዲሁም ካቼት ፋርማሲዩቲካል በተባለ የህንድ መድኃኒት አምራቾች የተመረቱ የተለያየ መለያ (ብራንድ) እና ስያሜ ያላቸው አሥር የፀረ ወባ መድኃኒቶች በባለሥልጣኑ ያልተመዘገቡ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ተገቢውን  መሥፈርት ያላሟሉ መሆናቸው መረጋገጡን አስታውቋል፡፡

የጤና ተቋማት፣ የመድኃኒት ችርቻሮ ንግድ ድርጅቶችና የጤና ባለሙያዎች የአቅርቦት ሰንሰለቱን በመከታተል ደረጃቸውን ያልጠበቁና ሐሰተኛ የመድኃኒት ምርቶችን ሥርጭትና አጠቃቀምን ለመከላከል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡

የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የኅብረተሰቡን ጤንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ለመወጣት ገበያ ውስጥ ያሉ ኅብረተሰቡ የሚጠቀምባቸው መድኃኒቶች ደኅንነታቸው፣ ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው የተጠበቀ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ገልጾ፣ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ያልተረጋገጡ መድኃኒቶችን መጠቀም ከባድ የጤና ችግር እንደሚያስከትል አሳስቧል፡፡

ከዚህ ቀደም ሪሊፍ (RELIEF) የሚባል ሕገወጥ መድኃኒት (በውስጡ ዲክሎፌናክ፣ ፓፓራሲታሞል፣ ክሎረፊኒራሚንና ማግኒዥየም ትራይሲሊኬት እንዳለው የሚገመት) በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ እየተዘዋወረ መሆኑን እንደደረሰበት ባለሥልጣኑ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

“RELIEF” የተባለው መድኃኒት በሕጋዊ መንገድ ያልተመዘገበ በመሆኑ ስለጥራቱ፣ ደኅንነቱና ውጤታማነቱ አላውቅም ያለው የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን መድኃኒቱ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የሆድ ሕመም፣ ማቅለሽለሽ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ድካም፣ የዕይታ መዛባት፣ ራስ ምታት፣ የጉበት ኢንዛይም መጨመርና ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል የኩላሊትን ጨምሮ የመሳሰሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳሉት ዘርዝሯል፡፡

ይህንን መድኃኒት ለረዥም ጊዜ መጠቀም ከባድ የጉበት፣ የኩላሊት፣ የልብ ድካምና ስትሮክ የመያዝ ዕድልን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል በጥናት በመረጋገጡ ኅብረተሰቡ ይህንን መድኃኒት ከመጠቀም እንዲቆጠብ ማሳሰቢያ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በተለይም ያልተመዘገቡና የጥራት ደረጃ የማያሟሉ የፀረ ወባ መድኃኒቶች የደኅንነት የጥንቃቄ መልዕክቱ በተዋረድ፣ ለሁሉም ጤና ባለሙያዎችና ጤና ተቋማት ተደራሽ ለመሆኑ የትግበራ ክትትል እንዲደረግ አሳስቧል፡፡