

December 11, 2024
የኢትዮጵያ የፋርማሲ ማኅበር 50ኛውን የወርቅ ኢዮቤልዩ ባከበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ለማኅበሩ መመሥረት፣ ዕድገትና ጥንካሬ ከፍተኛ የሙያ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፋርማሲ ባለሙያዎች ዕውቅናና ሽልማት ሰጥቷል፡፡ የምስክር ወረቀትና ሜዳሊያ ከተሸለሙትም ሙያተኞች መካከል ወ/ሮ ዘነበች ወልደማርያም አንዷ ናቸው፡፡ ተሸላሚዋ የአንደኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ተወልደው ባደጉበት በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ በኋላም ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ. በ1974 በፋርማሲ የመጀመርያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የግላቸውን ፋርማሲ አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ለማኅበሩ ባበረከቱት አስተዋጽኦና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለማኅበሩ አስተዋጽኦ ለማድረግ ያነሳሳዎት ምክንያት ምንድነው? ይህንን ለመጠየቅ ያስገደደኝ ማኅበሩ ሲቋቋም እርስዎ ገና የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ስለነበሩ ነው፡፡
ወ/ሮ ዘነበች፡- በአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ሦስተኛ ዓመት ላይ የደረሰ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጥቶ በተማረው ሙያ ለአንድ ዓመት የሚቆይ አገልግሎት ያበረክት ነበር፡፡ በመሆኑም ለማኅበሩ የየበኩላችንን አገልግሎት ከመስጠት ችላ ያልንበት ጊዜ አልነበረም፡፡ በመጨረሻም የማኅበሩ ተባባሪ አባል ሆንን፡፡ ተባባሪ አባል ለመሆን የቻልነውም ወደፊት አባል ትሆናላችሁ ብለውን ነው፡፡ ተባባሪ አባል ሆነን ለሁለት ዓመት ያህል አገልግለናል፡፡ ሙሉ አባል የሆንነው ሥራ ከገባን በኋላ ነው፡፡ ለዚህም በየዓመቱ ለማኅበሩ የተወሰነ ክፍያ እንከፍል ነበር፡፡ ሲቀጥልም የማኅበሩ ገንዘብ ያዥ ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ ሌሎች ንዑሳን ኮሚቴዎች ሲቋቋሙ በሙያ ማሻሻያ፣ በሥነ ምግባር፣ በሥነ ጽሑፍ የበኩሌን አገልግሎት አበርክቻለሁ፡፡ ከዚህም ሌላ የሽልማት ኮሚቴ ሆኜ ለአራት ዓመት ሠርቻለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በተመረቁበት ሙያ የትኞቹ ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል?
ወ/ሮ ዘነበች፡- ከዩኒቨርሲት የሦስተኛ ዓመት ትምህርት ከጨረስን በኋላ ለአንድ ዓመት በዩኒቨርሲቲ አገልግሎት መስጠት አለ፡፡ በዚህም ጊዜ ዋናው መድኃኒት ቤት (የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት) ግቢ መድኃኒት የሚቀመምበት ክፍል ነበር፡፡ በዚህ ክፍል ለአንድ ዓመት ያህል አገልግያለሁ፡፡ አራተኛ ዓመት ትምህርት ላይ ስደርስ እዚሁ መሥራት ትችያለሽ ስላሉኝ ከተመረቅሁ በኋላ ሥራ የጀመርኩት እዚሁ ክፍል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ዋናው መድኃኒት ቤት እንደገቡ ቀሩ፣ ወይስ ሌላ ተቋም መሥራቱን ተያያዙት?
ወ/ሮ ዘነበች፡- ራስ መስፍን ግቢ በሚገኘው ፋርሚኮር (የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት) ገባሁ፡፡ በዚህም የውጭ ግዥ ኃላፊ ሆኜ ለአሥራ ስምንት ዓመት ሠርቻለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ያለው የመድኃኒት አያያዝ፣ አቅርቦትና አገልግሎት በእርስዎ ጊዜ ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲያዩት እንዴት ይገመግሙታል?
ወ/ሮ ዘነበች፡- ይህንን ጥያቄ ባልመልሰው ይሻለኛል፡፡ ምክንያቱም እኔ ብዙውን ጊዜ የሠራሁት በቢዝነስ ዘርፍ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በእርስዎ የአገልግሎት ዘመን መድኃኒት ከየት ነበር የሚመጣው?
ወ/ሮ ዘነበች፡- በተለይ ከአውሮፓ፣ ከቻይና፣ ከህንድ በብዛት ይመጣ ነበር፡፡ አንዳንድ መልቲ ካምፓኒዎችም አፍሪካ ውስጥ ቅርንጫፍ ነበራቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ኬንያ ናይሮቢ ከተቋቋመው ፋብሪካ የሚገዛበት ወቅት ነበር፡፡ ግዥው ይከናወን የነበረው ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የፋርማሲ ማኅበር ለአባላቱ የሚሰጠውን አገልግሎት አጠር ባለ መልኩ ቢገልጹልን?
ወ/ሮ ዘነበች፡- የኢትዮጵያ የፋርማሲ ማኅበር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው፡፡ ይህም እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለአባላቱ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ ከአባላቱ ጋር ጥሩ ግንኙነት ያለው ማኅበር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የፋርማሲ ትምህርት ቤቶች በብዛት ተከፍተዋል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
ወ/ሮ ዘነበች፡- አዎ በብዛት ተከፍተዋል፡፡ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚሰጡ ትምህርቶች አንድ ዓይነት ስለሆኑ፣ ተመራቂዎችም በዚያው ልክ ጥሩ ዕውቀት ቀስመው ሲመረቁ ይስተዋላል፡፡ የሙያ ማኅበሩም ጥሩ ውጤት አግኝተው ለሚመረቁ ተማሪዎች ማበረታቻ ሽልማት ይሰጣል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የፋርማሲ ማኅበር ለሙያው ዕድገት ያበረከተውን አስተዋጽኦ እንዴት ይገልጹታል?
ወ/ሮ ዘነበች፡- እኛ በተማርንበት ዓመታት ክሊኒካል ፋርማሲ የሚል በፋርማሲ ትምህርት ላይ አልተካተተም ነበር፡፡ ነገር ግን ማኅበሩ ክሊኒካል ፋርማሲ በካሪኩለሙ እንዲካተት በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ሐኪሞችና ፋርማሲስቶች በሕክምና ምርመራ አብረው ወይም ጎን ለጎን ሆነው እንዲሠሩ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ክሊኒካል ፋርማሲ ኮርስ ትምህርት ከመሰጠቱ በፊት የተመረቅነውም ትምህርቱን በኮንቲኒየስ ፕሮፌሽናል ዴቨሎፕመንት ፕሮግራም ለመከታተል ችለናል፡፡
ሪፖርተር፡- በዘመኑ ምን ያህል ነው የተመረቃችሁት? ከተመራቂዎቹ መካከል ሴቶች ስንት ናችሁ፡፡ ሴቶች በመሆናችሁ የደረሰባችሁ ችግር ይኖር ይሆን?
ወ/ሮ ዘነበች፡- የተመረቅነው አሥር ነን፡፡ እኔን ጨምሮ ሁለቱ ሴቶች ነን፡፡ ሴት በመሆናችን የደረሰብን ችግር የለም፡፡ ከመመረቃችን በፊት ማኅበሩን ከማገልገል ወደኋላ አላልንም፡፡ ከተመረቅን በኋላ ግን ሁላችንም የማኅበሩ አባል ሆነናል፡፡
ሪፖርተር፡- የፋርማሲ ሙያ እንዲከታተሉ ያነሳሳዎት ምክንያት ምንድነው?
ወ/ሮ ዘነበች፡- ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ይህ ትምህርት ቤትና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ትምህርት ቤት ጎረቤታሞች ናቸው፡፡ በመካከላቸው የሚለያቸው የሽቦ ወንፊት አጥር ነው፡፡ በመሆኑም የፋርማሲ ተማሪዎች ሲወጡና ሲገቡ እናስተውል ነበር፡፡ የፋርማሲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ወደ ሙያው እንድሳብ አድርጎኛል፡፡ የወላጆቼም ፍላጎት ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡
