
December 25, 2024

‹‹የአገር ውስጥ ባንኮች ሲስተም ኋላቀር በመሆኑ ከውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር ይቸገራሉ›› ኤመራልድ ኢንተርናሽናል ኮሌጅ
በናርዶስ ዮሴፍና በተመስገን ተጋፋው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ሥነ ምኅዳር እንቅስቃሴ፣ ኢትዮጵያ በአገልግሎት ዘርፉ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ተርታ ከተሠለፉት አራት አገሮች መካከል እንድትመደብ እንዳስቻላትና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከ198 ሚሊዮን በላይ የዲጂታል የባንክ ሒሳቦች መኖራቸውን ቢያስታውቅም፣ የአገር ውስጥ ባንኮች ኋላቀር የመረጃ ቋት ሲስተም (Data System) ከውጭ ከሚገቡ ባንኮች ጋር የሚኖራቸውን ውድድር አስቸጋሪ እንደሚሆን ደግሞ ኤመራልድ ኢንተርናሽናል ኮሌጅ አደረኩት ባለው ጥናት መረጋገጡን ገልጿል።
ቅዳሜ ታኅሳስ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ቡና ባንክ ከአንድ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት አቅራቢ ጋር በጋራ በመሆን ባዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙት፣ የብሔራዊ ባንክ የክፍያና ሴትልመንት ሲስተምስ (Settlement Systems) ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ዳምጠው ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በዲጅታል የፋይናንስ ዘርፉ ላይ የታዩ ለውጦችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
እንደ ይሬክተሩ ማብራሪያ፣ በአገሪቱ የሚገኙት ከ198 ሚሊዮን በላይ የዲጂታል የባንክ ሒሳቦችን፣ ከ110 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መስጫ ሒሳቦችን፣ ከ47 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት መስጫ ሒሳቦችን፣ እንዲሁም ከ35 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ ማንቀሳቀሻ ሒሳቦችን ያካተተ ነው።
አቶ ሰለሞን በዲጂታል ፋይናንስ በኩል በኢትዮጵያ በየቀኑ በአማካይ ከ7.5 ሚሊዮን በላይ ግብይት እንደሚከናወን ገልጸው፣ በዚህም በአማካይ በየዕለቱ ከ26.5 ቢሊዮን ብር በላይ ዝውውር እንደሚከናወን አስታውቀዋል። የዲጂታል ፋይናንስ ምኅዳር በንግድ ባንኮች ወይም ደግሞ በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማቶች ብቻ የተወሰነ አለመሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ከ11 በላይ ባንክ ያልሆኑ የዲጂታል ክፍያን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ተቋማት በአገሪቱ ውስጥ መኖራቸውንም ገልጸዋል።
‹‹ተጠቃሚዎች በሞባይል ስልካቸው አማካይነት ፈጣንና አስተማማኝ ሁኔታ ገንዘብ መላክንና መቀበልን ጨምሮ የቁጠባና የአነስተኛ ብድርን ያካተቱ አገልግሎቶችን ቀላልና ምቹ በሆነ መንገድ እንዲያገኙ እያስቻለ ይገኛል። ይህም ለፋይናንስ አካታችነት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ፍትሐዊ የፋይናንስ አካታችነት እንዲኖር እያደረገ ሲሆን፣ ደንበኞች በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያላቸው እምነት እየጨመረ መምጣቱን ያመላክታል፤›› ብለዋል።
ይሁንና ኤመራልድ ኢንተርናሽናል ኮሌጅ የባንኮች ጥምረት የሥልጠና ተቋም ከሆነው የካፒታል ፋይናንስ ልህቀት ጋር በመተባበር፣ ለፋይናንስ ኢንዱስትሪው ቀጣይነት ያለው የዲጂታል ለውጥ ለማምጣት ከባንኮች ጋር ማክሰኞ ታኅሳስ 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ውይይት ሲደረግ የፋይናንስ ዘርፉ ያለበት ወቅታዊ ችግርን በተመለከተ የቀረበ ማብራሪያ ባንኮች ላይ የተጋረጡ አደጋዎችን ይፋ አድርጓል፡፡
በወቅቱም የካፒታል ፋይናንስ ልህቀት ማዕከል የሥልጠናና ልማት ዳይሬክተር ሀብታሙ አበባው (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደለገጹት፣ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ፈጠራንና ተወዳዳሪነትን በማጎልበት የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ በፍጥነት እየተቀየረ ካለው የዓለም ገበያ ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል የመረጃ ሥርዓቱን ማዘመን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ዳይሬክተሩ አቶ ሰለሞን ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. ከ2018 ጀምሮ ባደረጋቸው የዲጂታል ፋይናንስ ፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች ለውጥ ምክንያት፣ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላት ከፍ እንዲሉ አድርጓልም ሲሉ ተናግረዋል።
ይህም ማለት ከ2018 በፊት የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡት መደበኛ የሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ብቻ እንደነበሩ፣ ይህንን በመቀየር የዲጂታል ፋይናንስን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲሰጡ ሌሎች ተዋንያን በዘርፉ እንዲካተቱ በማድረግ፣ የዲጂታል ፋይናንስ ምኅዳሩ በገበያ ላይ የተመሠረተና የበለጠ ፉክክርና ትብብር እንዲኖር ማስቻሉን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ሀብታሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚገኙ ተቋማትም ሆኑ ባንኮች ሲስተማቸው ኋላቀር ስለሆነ፣ ከውጭ ከሚገቡ ባንኮች ጋር ተወዳድረው የፋይናንስ ዘርፉ ለመምራት ችግር ውስጥ ይወድቃሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. ከ2021 ጀምሮ ብሔራዊ የዲጂታል ስትራቴጂ በማርቀቅ፣ የዲጂታል ፋይናንስን ለማስፋፋት አስፈላጊና ወሳኝ ዕርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱም ተጠቅሷል። አቶ ሰለሞን፣ ‹‹ስትራቴጂው አስተማማኝ፣ ተወዳዳሪ፣ ውጤታማ፣ አዳዲስና ኃላፊነት የሚሰማው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትና የፋይናንስ ሥነ ምኅዳር ለመፍጠር አስችሏል፤›› ብለዋል።
በተለይ በአገር ደረጃ የፋይናንስ ዘርፉ ላይ ትልቅ የሆነ የዕውቀት ክፍተት እንዳለ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ክፍተቱን ለመሙላትና ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ለባንኮች ቴክኒካዊ ሥልጠናዎች እየተሰጧቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮችን ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ ማዕከሉ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን፣ በመጀመሪያ ባንኮች ከውጭ ከሚገቡ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ ከመሆናቸው በፊት ራሳቸውን በዲጂታል ቴክኖሎጂ መገንባት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉት የዳሸን ባንክ ቺፍ ዲጂታልና ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር አቶ ዮሐንስ ሚሊዮን እንደገለጹት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂውን ዘመኑን የዋጀ በማድረግ ለማኅበረሰቡ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ መዘርጋት የግድ ይላል፡፡
ባንኮች ከዓለም የግብይት ሥርዓት ተነጥለው መቅረት እንደማይችሉ በማመን፣ አሁን የምጠቀምበትን የቴክኖሎጂ ሥርዓት ከጊዜው ጋር መሄድ እንዳለበት በማወቅ ለመጠቀም ቀላል የሆኑ አሠራሮችን መዘርጋት እንደሚያስፈልጋቸው አስረድተዋል፡፡
የፋይናንስ ተቋማትም ሆኑ ባንኮች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚያደርጉበት አንዱ ነገር ከደኅንነት ጥበቃ ጋር የተያይዘ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ሁሉም ባንኮች የዲጂታል ሥርዓቱ ላይ ቀጣይነት ባለው መንገድ ራሳቸውን ማዘመን እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል፡፡
የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በቴክኖሎጂና በካፒታል ረገድ የሚያመጡት ጥቅም በበጎ ጎኑ እንደሚያዩት የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ባንኮች ካላቸው ውስን ካፒታል አንፃር ውድድሩን ከባድ ሊያደርገው እንደሚችል ሥጋት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
ነገር ግን የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የሚፈቅዱ አገልግሎቶች በአንድ ጊዜ እንደማይፈጸሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዳሳወቃቸው፣ ይህም የአገር ውስጥ ባንኮችን አቅም እያገናዘበ የሚሄድ እንደሚሆን እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የቡና ባንክ የኢንተርፕራይዝ ሲስተም ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ባለህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹በዲጂታል ሥርዓቱ በእኛ አገር ያለው የዕድገት ሁኔታ ገና መነሻው ላይ መሆናችንን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ከውጭ የሚገቡ ባንኮች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የዳበሩ በመሆናቸው፣ ከእኛ አገር ጋር የሚኖራው የአሠራር ሥርዓት ሰፊ ልዩነትን እንደሚፈጥር በማመን፣ ከወዲሁ ባንኮች ዝግጁ መሆን አለባቸው፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ በሌሎች አገሮች የቴክኖሎጂ ሥርዓት የሚሠሩ ባንኮች እንዳሉ፣ ነገር ግን ተጠቃሚዎችን ጨምሮ ያለውን የባንክ ሥርዓት በተሻለ ደረጃ ለማስኬድ ብዙ መሥራት የሚጠይቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ የክፍያና ሴትልመንት ሲስተምስ (Settlement Systems) ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን፤ የዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍ ተዋንያን ትብብርን መሠረት ያደረገና የአገልግሎት አቅርቦትን የሚያሻሽል የፋይናንስ አካታችነት እ.ኤ.አ. በ2025 ድረስ ባለው ጊዜ ብቻ 70 በመቶ የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ በፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማካተት የተቀረፀው ይህ ስትራቴጂ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በመሠረተ ልማት፣ በአሠራር ማዕቀፍ፣ በክትትል፣ እንዲሁም ፈጠራን ጨምሮ አራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮር በመተግበሩ ውጤት አምጥቷል ተብሏል፡፡