

ረቂቅ አዋጁ በጸደቀበት ወቅት
ዜና ተቃውሞ የቀረበበት የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ያለማሻሻያ ፀደቀ
ቀን: December 25, 2024
የተጎሳቆለ መሬትን መልሶ ለማገገም ይረዳል የተባለው የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ለማቋቋምና አስተዳደሩን ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ አዋጅ፣ የእያንዳንዱ ክልል ድርሻ የሚወሰነው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጠቅላላ የበጀት ድጋፍ ቀመር አማካይነት ነው ተብሎ መቅረቡ ተቃውሞ ቢቀርብበትም ያለ ማሻሻያ ፀደቀ፡፡
የተጎሳቆለ መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ደኖችን በመጠበቅና በመንከባከብ፣ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ቋሚና ተቋማዊ ሥርዓት ያለው የፋይናንስ አቅም በመፍጠር፣ የመሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ረቂቅ አዋጅ ለሳምንታት ውይይት ሲደረግበት የቆየ ሲሆን፣ ፓርላማው ትናንት ማክሰኞ ታኅሳስ 15 ቀን 2017 ዓ.ም. በሙሉ ድምፅ ፀድቆለታል፡፡
በረቂቁ ውይይቱ ወቅት በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው የነበሩ ቢሆንም፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥቅል ዓላማ የበጀት ክፍፍል አማካይነት ገንዘቡ ይተላለፋል ተብሎ መደንገጉ ከአዋጁ ዓላማ ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
አንድ ተሳታፊ ባቀረቡት አስተያየት፣ የፌደሬሽን የጥቅል ዓላማ በጀት አመዳደብ፣ ክልሎች የካፒታልም ይሁን መደበኛ ወጪ መሸፈኛ ታሳቢ ተደርጎና ገቢያቸውን መነሻ አድርጎ የተቀመጠ መሆኑን፣ ነገር ግን የምኅዳር ተጋላጭነትን ለማስተካከል ተብሎ የቀረበው ሕግ፣ የተጎዳውን መሬት በማየት እንጂ በጥቅል በጀት አመዳደብ መሠረት ከተሄደ አዋጁ ዓላማውን ሊስት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
የልዩ ፈንዱ ዓላማ የተጎሳቆለ መሬት በተፈጥሮና በመልሶ ማልማት መርህ በመታገዝ እንዲያገግም በማድረግ፣ የደን ልማትና የደን መልሶ ማልማትን መደገፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከአንድ ሳምንት በፊት በረቂቁ ላይ በነበረው ውይይት የተጎሳቆለ መሬት እንዲያገግም የሚመደበው በጀት በቀመር የሚተላለፍ ከሆነ፣ የተጎዳው መሬት ያለበት ክልል ሳያገኝ ለሌላ ክልል የሚሄድበት ዕድል ሰፊ ስለሆነ፣ የፈንዱ አደላደል የጉዳት መጠንን መሠረት በማድረግ ጉዳዩ በሚመለከተው ተቋም ከተጠና በኋላ መሆን አለበት የሚል አስተያየቶች ተሰጥተው ነበር፡፡ በወቅቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰጠው ምላሽ የበጀት ቀመሩ ወደ ምክር ቤት እንዲፀድቅ ሲላክ፣ ከክልሎች ጋር ስምምነት መደረግ አለመደረጉን የማጣራት ሥራ እንደሚከናወን ገልጾ ነበር፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የምክር ቤት ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) አዋጁ ከመፅደቁ በፊት በሰጡት አስተያየት፣ ለክልሎች የሚመደበው የልዩ ፈንዱ በጀት በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሠራር አማካይነት መሆን የለበትም የሚል መከራከሪያ አቅርበው ነበር፡፡
አክለውም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያለው መረጃ የእያንዳንዱ ክልል የሕዝብ ቁጥር፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ እንጂ የደን ሽፋንን አለመሆኑን ደሳለኝ (ዶ/ር) ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡
በጀቱ ለታለመለት የአካባቢ ደን ሽፋን መጨመር እንዲውል ከተፈለገ፣ የአገሪቱን የደን መረጃን ለሚከታተሉት የግብርና ሚኒስቴርና የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የመሳሰሉ ተቋማት የሚያወጡትን መረጃ መሠረት አድርጎ መወሰን አለበት ብለዋል፡፡
የመሬት መጎሳቆልና የደን መመንጠር በአገሪቱ ከቦታ ቦታ ይለያያል ያሉት ደሳለኝ (ዶ/ር) በሰሜን፣ በሰሜን ምሥራቅ፣ ምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ያለው የመሬት መጎሳቆልና ምርታማነት ከደቡብ፣ ከደቡብ ምዕራብና ከምዕራቡ ጋር ካለው የተለየ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በጀቱ አመዳደብ የችግሩ ተጋላጭነትንና ከሕጉ ዕሳቤ አንፃር ታይቶ መሆን አለበት የሚል አስተያያት አቅርበው ነበር፡፡
በሌላ በኩል በረቂቁ የቀረቡት ድንጋጌዎች ላይ ማሻሻያ ተደርጎ ይመጣል ብለው ቢያስቡም፣ ለውጥ ሳይደረግበት መምጣቱን የገለጹት የምክር ቤት አባል አቶ ተረፈ ታደሰ፣ አዋጁ ትኩረት የሚሰጠው ለተጎሳቆለና ለተመነጠረ መሬት እንጂ፣ ጥብቅ ሆኖ ለቆየ ደን ምንም ዓይነት ትኩረት የሚሰጥ አይደለም ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
በዚህም ምክንያት የተፈጥሮ ደንን ጠብቀው ያቆዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚገባቸውን ትኩረት እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያና በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ተጠብቀው ለኖሩት ደኖች ዕውቅናና የሚገባቸውን ትኩረት የሚሰጥ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹ምናልባት መሬታችሁን አጎሳቁሉና ማገገሚያ ፈንድ ተጠቃሚ ሁኑ የሚል አንድምታ የያዘ አዋጅ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ በሰጡት ምላሽ፣ አዋጁ ደን ጠብቀው ላቆዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሰጠው ምንም ዓይነት ድጋፍ አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡
ፈንድ ለመደልደል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመርን መጠቀም ያስፈለገው አሁን ባለው ሁኔታ ቀመርን ለማከፋፈል የሚያስችል መንገድ ባለመኖሩ እንደሆነ፣ ለዚህ የሚሆን ራሱን የቻለ ቀመር በሦስት ዓመታት ውስጥ እንዲዘጋጅ ዕቅድ መያዙን አስረድተዋል፡፡