የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ

ዜና አባል ያልሆኑ ነጋዴዎች በአመራሮችና በቦርድ አባላት ምርጫ ይሳተፋሉ መባሉ ውዝግብ አስነሳ

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: December 25, 2024

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያሻሻለው የቦርድ አመራረጥና መተዳደሪያ ደንብን ለማፅደቅ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ፣ የምርጫ አጣሪ ኮሚቴ ከኃላፊነቱ የማንሳትና አባላት ያልሆኑ ነጋዴዎችን የምርጫ ተሳትፎ በተመለከተ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ነባር አባል ነጋዴዎችን ግራ ማጋባቱና ሌላ ውዝግብ እየፈጠረ መሆኑ ታወቀ፡፡

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ከሁለት ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን ከትናንት በስቲያ ሰኞ ታኅሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በምክር ቤቱ ዙሪያ ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው፣ ታኅሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት ጠቅላላ ጉባዔ ወደ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም. መዘዋወሩ የተገለጸ ሲሆን፣ በዕለቱም የምክር ቤቱ የቦርድ አመራረጥና የመተዳደሪያ ደንብ ተሻሽሎ እንደሚፀድቅ ተገልጿል።

አዲስ አበባ አላት ከተባለው 483,895 የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ውስጥ፣ በየዓመቱ የአባላት ክፍያቸውን የሚፈጽሙ አባላት ከጠቅላላ ነጋዴዎች ከአንድ በመቶ በታች ወይም አራት ሺሕ ብቻ መሆናቸው መታወቁንና ቦርዱ በድክመት መገምገሙም ተጠቅሷል።

ወ/ሮ መሰንበት ‹‹የአባላቱን ቁጥር ከፍ በማድረግ ከተማዋን የሚመጥን ንግድ ምክር ቤት እንዲኖር በሚል የመተዳደሪያ ደንቡን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በዚህ ወር የምናደርገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ደንቡን በማሻሻል ከተማዋን የሚወክል ምርጫ እንዲካሄድ፣ ሁሉንም የንግድ ማኅበረሰብ እንዲወክልና ሁሉም የፀና ፈቃድ ያለው ነጋዴ አባል በመሆን መራጭና ተመራጭ እንዲሆን ይደረጋል፤›› ብለዋል።

በሥራ ላይ ያለው የምክር ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብ እንደሚያብራራው፣ አባል የሚኮነው በፈቃደኝነት ላይ መሠረት ባደረገ መልኩ፣ የቦርድ አባላትም የሚመረጡትም ከአባላት መካከል እንደሆነ ቢጠቅስም፣ በጠቅላላ ጉባዔው ዕለት የሚገኙ አባል ያልሆኑ ሰዎች እንዲመረጡ የሚያደርግ፣ ለዚህም የሚያስፈልገው አዋጅ ያለ ቅድመ ውይይት በዕለቱ እንዲፀድቅ መታቀዱ እያስነሳ ያለውን ውዝግብ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡ ለምክር ቤት አመራሮች ጥያቄ ቀርቧል።

ፕሬዚዳንቷም ‹‹አባል ያልሆኑ ሰዎች እንዲመረጡ ለምን ታደርጋላችሁ? ለሚለው፣ ሕጉን ለጊዜው እንተወውና አባልም ባይሆን ለምንድነው የተሟላ የንግድ ፈቃድ ያለውን ነጋዴ የማይመረጠው ለምንድነው? ይህ ዶግማ ይባላል። ሕግ ይቀመጥና ሕግ አይነኬ ሆኖ ሰዎች እጃቸውን አጣጥፈው ከአዲሱ ጊዜ ጋር ባለመሄዱ የዛሬ አሥራ ምናምን ዓመት የወጣ መመርያ አላስኬድ እያለ ለምን ይተዋል? ማየት የሚገባን አመክንዮውንና የነጋዴውን ፍላጎት (Interest) መጠበቅ የሚለው የመጀመሪያው ማሰብ ያለብን ነገር ይህ ነው፤›› በማለት ለተጠየቁት ጥያቄ ሌላ ጥያቄ በማቅረብ ምላሽ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በሚደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ይፀድቃል የተባለው የተሻሻለው ደንብ ያለውን በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አባልነት መሥፈርትን እንደማይቀይር ገልጸዋል።

ይሁንና የማሻሻያውን ይዘቶች በተመለከተ ከጠቅላላው ጉባዔ ቀድሞ የሚደረግ አጠቃላይ ጉባዔ እንደማይኖር አስታውቀው፣ ነገር ግን የተሻሻለው ሰነድ ቀደም ብሎ ለአባላቱ ተበትኖ እንዲደርሳቸው ተደርጎ ውይይት እየተደረገበት ነው ብለዋል።

‹‹ጊዜም ስለሌለን ደንቡ እስከ ታኅሳስ 30 ቀን ድረስ ብቻ ባለው ጊዜ ውስጥ (በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ መካሄድ ይገባዋል) ስለሚል፣ ቀደም ሲል ሁሉም ያወቀውን ሕግ አቅርበን ውይይት እንዲደረግበትና ስብሰባውን ለመምራት ብዙም ያስቸግራል ብለን ስላላሰብን ነው ይህ የተወሰነው፤›› ብለዋል ወ/ሮ መሰንበት።

ምክር ቤቱ ለሚያደርገው የፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላት ምርጫ ለመወዳደር የሚጠቁሙ ግለሰቦችን ብቃት፣ የትምህርት ደረጃ፣ እንዲሁም የምክር ቤቱ አባል መሆናቸውንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የሚያጣራ የምርጫ አጣሪ ኮሚቴ ከተሰየመ አሥር ቀናት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ ሥራውን እንዲያቋርጥ በምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ታኅሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ተፈርሞ በወጣ ደብዳቤ መታዘዙን መዘገባችን አይዘነጋም።

ከትናንት በስቲያ በተሰጠው መግለጫ ኮሚቴው ሥራውን ለምን እንዲያቋርጥ እንደተደረገ ፕሬዚዳንቷ ሲገልጹ፣ ‹‹ይህ በአጣሪ ኮሚቴውና የምርጫ አካሄዳችን ላይ ለብዙ ጊዜ ብዙ ቅሬታዎች ሲቀርቡበት የነበረ ነው። የምርጫ አካሄዳችን ላይ የነበረው አሠራር ብዙዎች ቅሬታ ሲያቀርቡበት ስለቆየ፣ ምርጫውን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግ ከመመርያው ጋር ስናነፃፅረው የአጣሪ ኮሚቴው ሥራ በግልጽና ተጠያቂነት ባለው መንገድ እንዲሄድ ስላመንበት ነው አጣሪ ኮሚቴውን ያስቀረነው፤›› ብለዋል።

የሪፖርተር ምንጮች አጣሪ ኮሚቴው ሥራውን እንዲያቋርጥ የተደረገው፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ጣልቃ ገብነት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት የገዥው የፖለቲካ ፓርቲ ብልፅግና ተመራጭ በመሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የቦሌ ክፍለ ከተማ ተወካዩች መካከል አንዷ መሆናቸው ይታወቃል።

መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በምክር ቤቱ በተደረገ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ተመርጠው፣ ከሌሎች ተመራጭ የቦርድ አባላት ጋር የሁለት ዓመት የአገልግሎት ቆይታ በደንቡ መሠረት ተሰጥቷቸው በሥራ ላይ የቆዩ ሲሆን፣ የሥልጣን ዘመናቸው ካበቃ ከሦስት ወራት በላይ አስቆጥሯል።

ወ/ሮ መሰንበት ባለፈው ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ካነሷቸው ዓበይት ጉዳዩች መካከል የኦዲት ምርመራ ክፍተት ይገኝበታል።

በማብራሪያቸው የምክር ቤቱ ዳይሬክተሮች ቦርድ ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ መሠረት፣ ‹‹የንግዱ ማኅበረሰብ ሀብት ባክኗል፣ ቦርዱ የሚያውቃቸው የውጭ ጉዞዎችና የተጋነኑ የውጭ ምንዛሪ ተስተውሏል፡፡ ያልታወቁ ግንኙነቶች ተደርገዋል፡፡ በአዳዲስ ቅጥር፣ የውስጥ ዕድገት አሠራርና የትልልቅ ግዥ የፖሊሲ ጥናት ተፈጽሟል፡፡ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች በምክር ቤቱ ይስተዋላሉ፤›› በሚል በቀረቡ 23 ጥቆማዎች ሳቢያ፣ የኦዲት ኮሚቴ ከቦርዱ አባላት በማዋቀር በጽሕፈት ቤቱ ላይ ልዩ የኦዲት ምርመራ እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውሰዋል።

ቦርዱ በንግድ ምክር ቤቱ ተፈጽመዋል የተባሉትን ጥቆማዎች በአገሪቱም ሆነ በምክር ቤቱ ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና አሠራሮች ስለመፈጸማቸው እንዲያጣራ ልዩ አጣሪ የውስጥ ኦዲተር ለመቅጠር ወስኖ፣ መሥፈርት ተዘጋጅቶ የውስጥ ኦዲተር አወዳድሮ በመቅጠርና የልዩ የኦዲት ምርመራ ላይ በመሰየም፣ በኦዲት ኮሚቴ የበላይ አመራርነት ላለፉት ስድስት ወራት ያለፉት ሁለት ዓመታት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ፍተሻና ማጣራት መደረጉም ተጠቅሷል።

የተሰየመው የምክር ቤቱ የውስጥ ኦዲተርም የመጨረሻ ግኝቱን በማስረጃ በማስደገፍ ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እንዲቀርብ ተደርጓል ተብሏል።

ወ/ሮ መሰንበት ‹‹የነበረው ኦዲተር እንደ ኦዲተርነቱ የሚያቀርባቸው ሪፖርቶች በሰነድ ማረጋገጥ በሚቻል መልኩ እጅግ በጣም የተሳሳቱ ነበሩ። የኦዲት ግኝቶች መቅረብ የሚገባቸውና ያለውን ክፍተቶች ከማሳየት ይልቅ በጣም ጥሩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ሁሉም ነገር አበባ በአበባ ነው የሚሉ ሪፖርቶች ነበሩ ይቀርቡ የነበሩት፤›› ብለዋል።

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት አሁን በምክር ቤቱ የውስጥ ውድድር በማድረግ ኦዲተር መቀጠሩ የተጠቆመ ቢሆንም፣ የተቀጠረው ባለሙያ ሥራው ከመሆኑ ባሻገር፣ ለሠራው ትክክለኛ ሥራ በሚል ከምክር ቤቱ አሠራርና መመርያ ውጪ ከ300 ሺሕ ብር በላይ መሸለሙንና አግባብ አይደለም የሚል ተቃውሞ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

የምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ ስብሰባ የልዩ ኦዲቱን ግኝት መሠረት አድርጎ የፖሊሲ፣ የሕግና አሠራር ጥሰት ፈጽመዋል ባላቸው ኃላፊዎች ላይ የአስተዳደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድና የሪፎርም ሥራዎች እንዲጀመሩ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል።

ከእነዚህም መካከል ቀደም ብሎ የነበረው ኦዲተር ሲያቀርባቸው ለቆዩት የተሳሳቱ ሪፖርቶች ምክር ቤቱ ክስ ለመመሥረት እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ተገልጿል።