DireTube
የሀገር ዋርካው ሰብአዊ ሰው፤ አቶ ሽመልስ አዱኛ አረፉ
በኢትዮጵያ በተከሰተው እጅግ አስከፊ ድርቅ የእርዳታ ማሰባሰብና ማከፋፈል ኃላፊ ነበሩ ። በ80ዎቹ መጀመሪያ የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል። አቶ ሽመልስ አዱኛ በ1977 ዓም አደገኛው ረሃብ በሀገራችን ሲከሰት የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ድርጅት ኮሚሽነርና ሆነው በሰሩባቸው ሁሉ አመታት በበዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት እየቀረቡ በከፋ ረሃብ ለተጋለጡ ዜጎቻችን ለመታደግ እንባ እያዘሩ ከፍ ያለ እርዳታ እንዲገኝ ደክመው ሚሊዮኖችን ከረሃብ አደጋ የታደጉ የሀገርና የወገን ባለውለታ ናቸው ።
ስለ ደጉ የህዝብ አገልጋይ ስለ አቶ ሽመልስ አብረዋቸው የሰሩና የስራ ትጋት በቅርብ የሚያውቁ የሚሰጡት ምስክርነት ያስረዳል ። በድርቅ የተጎዱ ሚሊዮኖችን አብልተውና አጠጥተው ከሞት የታደጉት አቶ ሽመለስ አዱኛ የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኃላፊ ሆነው ሲሰሩም በመልካም አስተዳደር ምስጉን ሰው ነበሩ ። ቢሯቸው ለሁሉም ከፍተው አድርገው ችግር አለብኝ ለሚሉ ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው የሚቀበሉ የህዝብ አገልጋይ ነበሩ።
በ1977 ዓም ድርቅ እንባቸውን እያዘሩ እርዳታ ለምነው ሚሊዮን ወገኖቻችን ከከፋው የረሃብ አደጋ የታደጉትን አቶ ሽመልስ አዱኛን በጡረታ ዘመናቸው አግኝቶ ስለ ሰሩት ሁሉ መልካም አመስግኖ ሲጨዋወቱ የሰጡት ቃል እንዲህ ይላል “ሰው ስትሆን ለሌሎች መኖርና መሥራት እንዳለብህ ለአፍታም መዘንጋት የለብህም። እኔም ያን ከማድረግ ዉጪ የተለየ ነገር አላደረግኩም። የገዛ ቤተሰቤ እንደሆኑ አድርጌ መመልከቴ ይመስለኛል ከስሜት ውጪ ያደርገኝ የነበረው” ብለዋል ።
ዛሬ ማለዳ የዚህን የገዘፈ ሰብእና ባለቤት የሀገር ዋርካው ባለውለታውን የአቶ ሽመልስ አዱኛ ህልፈት በሰማሁ ጊዜ ነፍሴ አዘነች ዳሩ ግን ከፈጣሪ በታች ለሀገርና ለወገን በሃቀኝነት አገልግለው ያለፉት አቶ ሽመልስ በስጋ ቢለዩንም በሰሯቸው ስማቸው በሰሩት መልካመ ስራ ይዘከራልና አቶ ሽመልስ አዱኛ በትውልድ ህያው ስማቸው ይዘከራል ።
ነፍስዎ በሰላም ትረፍ!!
ነቢዩ ሲራክ
ታህሳስ 16 ቀን 2017 ዓ.ም
***
#ድሬቲዩብ :- በአቶ ሽመልስ አዱኛ ሞት የተሰማውን ሐዘን እየገለፀ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛል።