
ከ 6 ሰአት በፊት
ዶናልድ ትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ አብሯቸው ኤለን መስክ ተገኝቶ ነበር። ጥቁር ‘ሜክ አሜሪካ ግሬት አጌን’ (አሜሪካን በድጋሚ ታላቅ እናድርግ) የሚል ኮፍያ አጥልቆ ነው የተገኘው።
“ታላቅ ሰው ነው። የንግግር ነጻነትን አድኗል” ሲሉ ትራምፕ ስለ ኤለን በምርጫ ቅስቀሳቸው ላይ ተናግረዋል።
ቅስቀሳው እየተካሄደ የነበረው በፔንስልቬንያ ግዛት ነበር። እዚሁ ግዛት ከሦስት ወራት በፊት ትራምፕ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸውም ነበር።
ትራምፕ የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ ኤለን በይፋ ይደግፋቸው ጀመር።
መጀመሪያ ላይ በኤክስ ገጹ ነበር ድጋፉን ይሰጥ የነበረው። ቀጥሎ ግን በምርጫ ቅስቀሳ መድረክ አብሮ መገኘት ጀመረ።
ኤለን የንግግር ነጻነትን እንደታደገ ሲናገር ይደመጣል።
ከኤሌክትሪክ መኪና እስከ ኤክስ
ኤለን በኤሌክትሪክ መኪና፣ በሕዋ ጉዞ፣ በሳተላይት በሚሠራ ኢንተርኔትና በኤክስ ማኅበራዊ ሚዲያው ይታወቃል።
ከዓለማችን የናጠጡ ሃብታሞች አንዱ ነው። የፖለቲካ አቋሙ ግን ያወዛግባል።
እአአ በ2011 ራሱን “ለዘብተኛ፣ በማኅበራዊ ጉዳይ ነጻ እና በፋይናንስ ጉዳይ ቁጥብ” ሲል ይገልጽ ነበር።
በኮቪድ ወረርሽኝና በባይደን አስተዳደር ወቅት የፖለቲካ ዕሳቤው መቀየሩን የኤለንን ሕይወት የሚከታተል ጋዜጠኛ ይናገራል።
ወረርሽኙ የተነሳ ሰሞን ኮቪድ-19 ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ሲጠይቅ ተደምጧል። የእንቅስቃሴ ገደብን በጽኑ ይተች ነበር።
የቴስላ ስብሰባ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብን “ፋሺስት” ሲልም ጠርቷል።
- “በብሪታኒያ የእርስ በእርስ ጦርነት ይነሳል” – ባለሀብቱ ኢላን መስክ የብሪታኒያ ጉዳይ የሚያንገበግበው ለምንድነው?22 ታህሳስ 2024
- ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝደንት በመሆናቸው ቢሊየነሩ ኢላን መስክ ምን ይጠቀማል?7 ህዳር 2024
- ሁለተኛው የዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ምን ሊመስል ይችላል?7 ህዳር 2024
በዚህ ወቅት ከልጆቹ አንዱ ፆታ እየለወጠ ነበር። ይህንንም እንደሚቃወም ተናግሯል።
በማንነት ፓለቲካ ውስጥ ያሉ ተራማጅ አስተሳሰቦችን ይተች ጀመር።
ተራማጅ አመለካከትን ‘ዎክ ማይንድ ቫይረስ’ ሲል ይነቅፋል።
ትዊተር የግራ ዘመም ፖለቲካ ማራመጃ ነው ሲልም ነበር።
በ2022 ከቀድሞ ባለቤቱ ጋር በተለዋወጡት የጽሑፍ መልዕክት ቀኝ ዘመም የስላቅ ድረ ገጽ መታገዱን ተችተዋል።
ኤለን ትዊተርን “የነጻነት ንግግር መድረክ” እንዲያደርገው ሐሳብ መቅረቡን ተከትሎ በ44 ቢሊዮን ዶላር ገዝቶታል። ኤክስ ሲል ስያሜም ሰጥቶታል።

የንግግር ነጻነት
ትዊተርን ለምን መግዛት እንደፈለገ ሲጠየቅ የንግግር ነጻነት “ለጤናማ ዴሞክራሲ” ስለሚጠቅምና “ዲጂታል የከተማ ማዕከል” መሆን ስለሚችል እንደሆነ ተናግሯል።
የንግግር ነጻነትን ማስከበር በሚል ኤክስን ከገዛ በኋላ በርካታ ሠራተኞች ተቀንሰዋል።
በሴራ ትንታኔ ከገጹ ታግዶ የነበረውን አሌክስ ጆንስ ወደ ገጹ መልሷል። ትራምፕ ታግዶ የነበረ ገጻቸውን እንዲያገኙ ፈቅዷል። ውሳኔውነ ሪፐብሊካኖችን አስደስቷል።
የንግግር ነጻነት በመሠረታዊነት ራስን የመግለጽና ሌሎችን የማዳመጥ ነጻነት ሲሆን የጥላቻ ንግግርና ግጭት የሚቀሰቅስ ንግግርን በማገድ ከለላ ይደረግለታል።
ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ ፖለቲካዊ ትርጓሜ ሲሰጠው ይስተዋላል።
በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን የፖለቲካል ፊሎዞፊ መምህር ፕ/ር ጀፍሪ ሀዋርድ “ሪፐብሊካኖች ሕገ መንግሥቱን በመጥቀስ እነሱ በሕገ መንግሥቱ የተሰጡ መብቶችን ሲያስጠብቁ ዴሞክራቶች ግን ለመብቶቹ አደጋ እንደሆኑ ይናገራሉ” ይላል።
ማኅበራዊ ሚዲያዎች ይዘቶችን የሚፈትሹበት መንገድ አነጋጋሪ ነው።
ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች የጥላቻ ንግግር፣ ነውጠኛና አዋራጅ ይዘት የሚሉት የተዛባ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ያስረዳል።
“ክርክሩ የንግግር ነጻነት ይሩር በሚሉና በሚቃወሙ መካከል አይመስለኝም” ሲል ያክላል።
ኤለን የንግግር ነጻነት ብሎ የሚያምንበትን ለመጠበቅ በውጭ አገራት ጉዳዮችም መግባቱ ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ አድርጎታል።

በብራዚል ከተሳሳተ የምርጫ መረጃ ጋር በተያያዘ ስማቸው የተነሳ ገጾችን ከኤክስ ላይ አላግድም ማለቱ በቀድሞው ቀኝ ዘመም ፕሬዝዳንት ጃሂር ቦልሶናሮ ደጋፊዎች እንዲወደድ አድርጎታል።
ሆኖም ግን በሕንድና በቱርክ መንግሥታት ጥያቄ ይዘቶችን ከገጹ ማንሳቱ አስተችቶታል።
ኤክስ ከሚሠራበት አገር ሕግ እንደማይወጣ ይናገራል።
“የንግግር ነጻነት ዋነኛ አቀንቃኝ” ሲል ራሱን ቢጠራም ከንግግሩ ጋር የሚጻረሩ ድርጊቶችም ይፈጽማል።
ኤክስ ሁሉንም ሕጋዊ ንግግሮች አይፈቅድም። አደገኛ ንግግሮችን ባጠቃላይም ከገጹ አያስወግድም።

በ2022 ታዋቂ ጋዜጠኞች ስለ ኤለን የግል ጀት እንቅስቃሴ በመዘገባቸው የኤክስ ገጻቸው በጊዜያዊነት ሲዘጋ ኤለን የንግግር ነጻነትን እደግፋለሁ ማለቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ኤክስ ላይ 200 ሚሊዮን ተከታይ አለው። ይህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኤክስ ገጽ ያደርገዋል።
ኖርድ ኤክስኤል በሠራው ጥናት መሠረት፣ ከ2022 ወዲህ ትዊት የሚያደርግበት መጠን በእጥፍ ጨምሯል።
“ቀኑን ሙሉ መረጃ የሚያገኘው ከኤክስ ነው” ስትል የኤለንን ቅርብ ሰዎች አነጋግራ መጽሐፍ ያሳተመችው የኒው ዮርክ ታይምስ ዘጋቢ ኬት ኮንግነር ትናገራለች።
ኤለን ሐሰተኛ ንግግሮችን በገጹ አጋርቷል። የሴራ ትንታኔ አስተጋብቷል። ስለ ኮቪድ ቫይረስ የተሳሳተ መረጃም አሰራጭቷል።
ትራምፕን የመደገፍ ንቅናቄ
ኤለን ዴሞክራቶችን እንደማይደግፍ ተናግሯል።
ኬት እንደምትለው፣ ለትራምፕ ሙሉ ድጋፍ ነው ያደረገው። በየሰዓቱ ትራምፕን በመደገፍና ካማላ ሀሪስን በመንቀፍ ኤክስ ላይ ይጽፍ ነበር።
ስለ ምርጫ መጭበርበርና ዴሞክራቶች መራጮችን ከሌላ አገር ስለማስመጣቸው የተደረጉ የትራምፕን ያልተረጋገጡ ንግግሮች ያስተጋባ ነበር።
ኤለን በምርጫ ቅስቀሳው “ይሄ ተራ ምርጫ አይደለም። ያኛው ወገን የንግግር ነጻነታችሁን ሊቀማችሁ ይፈልጋል” ሲል ተናግሯል።
መስክ ትራምፕ ከተመረጡ በኋላ የዋይት ሀውስ አማካሪ አማካሪ ቦታ ተሰጥቶታል። ከትራምፕ ጋር ለአሁኑ ወዳጅነታቸው ቀጥሏል።
የንግግር ነጻነትን መታደግ የሚለው ፕሮጀክት የማኅበራዊ ሚዲያን መልክ የቀየረ ሆኗል።
የኤለን ደጋፊዎች “የንግግር ነጻነትን ታድጓል” ይላሉ።
የፖለቲካል ፊሎዞፊ መምህር ፕ/ር ጀፍሪ ሀዋርድ ግን በዚህ አይስማማም።
“ኤለን ኤክስን ከመግዛቱ በፊት እንደነበረው ነጻ የሕዝብ ውይይት የሚደረግበት መድረክ አይደለም” ይላል።
ኤለን በጉዳዩ አስተያየት እንዲሰነዝር ከቢቢሲ ተጠይቆ ምላሽ አልሰጠም።