ውሃ አምቆ በመያዝና በመጥፎ የአየር ሁኔታ ውስጥ መኖር በመቻል ይታወቃል።
የምስሉ መግለጫ,ውሃ አምቆ በመያዝና በመጥፎ የአየር ሁኔታ ውስጥ መኖር በመቻል ይታወቃል

ከ 5 ሰአት በፊት

በደቡብ አፍሪካ በብዝሀ ሕይወት የሚታወቀው አካባቢ በሕገ ወጥ ዕፅዋት አዘዋዋሪዎች ዒላማ ተደርጓል።

ሕገ ወጥ የዕፅዋት ዝውውሩ ማኅበራዊ ቀውስ እንደሚያሳድርና ተፈጥሮንም እንደሚጎዳ የአካባቢው አርኦ አደር ለቢቢሲ ገልጻለች።

“መሬታችንን እና ዕፅዋታችንን ብቻ አይደለም የሰረቁት ባህላችንንም ጭምር ነው የወሰዱት” ብላለች።

ዕፅዋቱ ሰኪዩለንት (succulent) ይባላል። ውሃ አምቆ በመያዝና በመጥፎ የአየር ሁኔታ ውስጥ መኖር በመቻል ይታወቃል።

ዕፅዋቱ የሚገኘው በደቡብ አፍሪካና ናሚቢያ ሰኪዩለንት ካሮ በረሃ ነው።

በመጠን በቅርጽና በቀለም የተለያየ ዝርያ አለው።

ዕፅዋቱን ማሳደግ የሚቻል ቢሆንም ከበረሃ በሕገ ወጥ መንገድ የተሰረቀው ዕፅዋት በዓለም አቀፍ ገበያ በስፋት እየተሸጠ ነው።

አሜሪካ፣ አውሮፓና ምሥራቅ እስያ ዕፅዋቱ ይሸጣል።

በደቡብ አፍሪካ በምትገኘው ካሚክሮን ከተማ ሕገ ወጥ ዕፅዋት አዘዋዋሪዎች ስርቆት ይፈጽማሉ።

አንዳንዶቹ የዕፅዋቱ ዓይነቶች እዛው ተዳቅለው የተሠሩ ስለሆኑ ሲቆረጡ ዝርያቸው ሊጠፋ ይችላል።

ኤስ ሪቻትስቨልድ ትራንስፍሮንቴር ፓርክ ውስጥ ዕፅዋት የሚያበቅለው ባለሙያ ፒተር ቫን ዌክ “በደቡብ አፍሪካ የጠፉ ሰባት ዝርያዎች አሉ። በቅርቡ የሚጠፉ እንዳሉም እናውቃለን” ይላል።

በሕገ ወጥ መንገድ ምን ያህል ዕፅዋት እየተሰረቁ እንደሆነ ትክክለኛ መረጃ ባይኖርም፣ እአአ ከ2019 እስከ 2024 በደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች 1.6 ሚሊዮን የተሰረቁ ዕፅዋት ተይዘዋል።

እነዚህ የተያዙ ብቻ ስለሆኑ ቁጥሩ ከዚም ከፍ ሊል ይችላል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የአካባቢ ጥበቃን ጨምሮ በ2022 ዕቅድ አውጥቶ ነበር።

ፒተር እንደሚለው የዕፅዋትና እንሰሳት ዝርፊያ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ተባብሷል።

በእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ወደ ደቡብ አፍሪካ መግባት ያልቻሉ ዘራፊዎች የአገሬው ሰዎች ከድብቅ እንዲያስወጡ ማድረግ ጀመሩ።

በዚህ ምክንያት ዓለም አቀፍ ፍላጎት መጨመሩን ፒተር ይናገራል።

“ሰዎች ቤታቸው ውስጥ ዕፅዋት በማሳደግ ነበር በወረርሽኙ ወቅት ጊዜ የሚያሳልፉት” ይላል።

የተደራጁ ወንጀለኛ ቡድኖች ከሕገ ወጥ ዕፅዋት ዘራፊዎች ጋር በመቀናጀት የበይረ መረብ ሽያጭ ያከናውናሉ።

በመጠን በቅርጽና በቀለም የተለያየ ዝርያ አለው።
የምስሉ መግለጫ,በመጠን በቅርጽና በቀለም የተለያየ ዝርያ አለው።

“ወንጀለኛ ቡድኖች ‘በጣም የተለየ መልክ ያለው የአፍሪካ ዕፅዋት’ እያሉ በበይነ መረብ መሸጥ ጀመሩ። ሰዎች የመግዛት ፍላጎት ስላሳዩ ሕገ ወጥ ንግዱ ተጧጧፈ” ይላል ፒተር።

ዝርፊያው ማኅበረሰቡ ላይ ጫና አሳድሯል።

በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራው ኮንሰርቬሽን ሳውዝ አፍሪካ ባለሙያ መሊንዳ ጋርዲንር “በአካባቢው ብዙ ሰው ድሃ ነው። ስለዚህ ክፍተቱን ዘራፊዎች ተጠቀሙበት” ስትል ታስረዳለች።

በአካባቢው የምትኖር አርሶ አደርም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥታለች።

“ወደ ተራራው የሚወጡ ወጣቶች ስናይ ዘራፊዎች እንደሆኑ እናውቃለን” ብላለች።

አርሶ አደሯ “ዕፅዋቱን ከሥሩ ይነቅሉትና በቦርሳ ይዘው ይጓዛሉ” ስትልም ትናገራለች።

“ገንዘብ ሲያገኙ አንዛዥ ዕፅና መጠጥ ይገዙበታል። እናትና አባት ስለሚሰክሩ ልጆች አሳዳጊ የላቸውም፤ የሚበሉት የሚሰጣቸውም የለም” ትላለች።

በሒደት ማኅበረሰቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ያሰጋታል።

“ትንሽ ነዋሪ ያላቸው ማኅበረሰቦች አንዳቸው ሌላቸውን ይፈልጋሉ። ይሄ ስርቆት ግን ማኅበረሰቡንም ይከፋፍላል” ትላለች።

ፒተር እንደሚለው ሕገ ወጥ የዕፅዋት አዘዋዋሪዎቹን ሰዎችን እየበዘቡ ነው።

ገዢዎችም ስለ ዕፅዋቱ በመረዳት እንዳይጭበረበሩ ለማድረግ እየተሠራ ነው።

ዕፅዋቱ በስፋት በሚሸጥበት ቻይና ግንዛቤ ለማስጨበት የተደረገው ሙከራ ውስን ውጤት አሳይቷል።

በ2023 በቻይና የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ተቋም የተጀመረው ንቅናቄ ዋና ጸሐፊ ሊንዳ ዎንግ እንደምትለው፣ በበይነ መረብ ንቅናቄ አማካይነት 80% የሕገ ወጥ ግብይት መቀነስ ተችሏል።

በቻይና የዕፅዋቱ አንድ ዝርያ የሆነው ኮንፓይተም ነበር የሚሸጠው።

“ዋናው ግንዛቤ መፍጠር ነው። ሰዎች ካወቁ እርምጃ ይወስዳሉ። የሚገዙት ዕፅዋት ውብና ሕጋዊ እንዲሆን ይሻሉ” ትላለች ሊንዳ።

የትኛው ዕፅዋት ከየት እንደመጣ ጠይቆ መገዛት እንዳለበት የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የዩኬ የዕፅዋት ጥበቃና ሽያጭ ድርጅቶች ከበይነ መረብ መገበያያው ኢቤይ ጋር በመተባበር ዕፅዋቱ እንዳይሸጥ ንቅናቄ እያደረጉ ነው።

ፒተር እንደሚለው፣ ዕፅዋቱን በሕጋዊ መንገድ ማብቀል የሚቻልበትን መንገድ በማስተማር ሕገ ወጥ ግብይትን መቀነስ ይቻላል።

“የኛ ዕፅዋት ነው። የምንጠቀምበት ግን እኛ ሳንሆን ሌሎች አገራት ናቸው። ለምን?” ሲል ይጠይቀል።

በፖሊስ የተያዙ ዕፅዋትን መልሶ በመትከል ያሳድጋል። እስካሁን 200,000 ተረክቧል።

“በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው በዕፅዋቱ ላይ የሚደርሰው። ግን ዕፅዋቱን ማሳደግ ደስ የሚል ሒደት ስለሆነ ዓለም ላይ ያለውን ክፉ ነገር ሁሉ ያረሳሳል” ይላል።