
ከ 6 ሰአት በፊት
በመብረቃዊ ወታደራዊ ዘመቻ ከስልጣን የተነሱት በሽር አል አሳድን እግር በመተካት የሶሪያው አማጺ ቡድን መሪ አህመድ አል ሻራ ደማስቆ ደርሶ ንግግር ሲያደርግ አንድ ያነሳው ጉዳይ ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም።
አል ሻራ ባለፉት 10 ዓመታት መካከለኛው ምስራቅን ያጥለቀለቀውን ህገወጥ አደንዛዥ ዕጽን ጉዳይ ጠቀስ አድርጓል።
“በዓለም ላይ ትልቋ የካፕታገን አምራች ሶሪያ ሆናለች። እናም በፈጣሪ ቸርነት ዛሬ ሶሪያ ከዚህ ነጻ ልትሆን ነው” ሲል ተናግሮ ነበር።
ካፕታገን በአብዛኛው ከመካከለኛው ምስራቅ ውጪ አይታወቅም። ሱስ የሚያስይዝ እና አምፌታሚንን የመሰለ እንክብል ሲሆን አንዳንድ ጊዜ “የድሃ ኮኬይን” ተብሎ ይታወቃል።
በጦርነት፣ በማዕቀብ፣ በመፈናቀል በተዳከመችው ሶሪያ ምርቱ ከፍ ብሏል። የጎረቤት አገራት በድንበሮቻቸው የሚካሄደውን ከፍተኛ መጠን ያለው ህገ-ወጥ የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ለመቋቋም ሲቸገሩ ቆይተዋል።
መረጃዎች ሶሪያ የካፕቶገን ህገወጥ ንግድ ዋና ምንጭ መሆኗን ያመለክታሉ። እንደ ዓለም ባንክ ከሆነ ይህ ንግድ በዓመት 5.6 ቢሊዮን ዶላር ያንቀሳቅሳል።
እንክብሎቹ እየተመረቱና እየተላኩ ያሉበትን መጠን ለተመለከተ ከጀርባው የሚገኘው የወንጀለኞች ቡድን ብቻ ሳይሆን በአገዛዙ የሚመራ ኢንዱስትሪ ጭምር እንደሆነ ይጠረጠራል።
በአል ሻራ (በቀድሞ ስሙ አቡ መሐመድ አል-ጆላኒ) ንግግር ካደረገ ከሳምንታት በኋላ ጥርጣሬው ትክክል መሆኑን የሚጠቁሙ አስደናቂ ምስሎች ብቅ ብቅ ብለዋል።

ሶሪያውያን በአሳድ ዘመዶች ተይዘዋል የተባሉ ንብረቶችን ሲፈትሹ የተቀረጹ ናቸው በተባሉ ቪዲዮዎች ላይ በኢንዱስትሪ ምርቶች ውስጥ የተደበቁ አንክብሎች የሚገኙባቸውን ክፍሎች ያሳያሉ።
የሶሪያ አየር ኃይል በሚመስለው እና በአማፂጽያኑ ከተቃጠለ ስፍራ የተቀረጹ ምስሎችም በርካታ እንክብሎች መገኘታቸውን ያሳያል።
ካፒታገን እንደሳዑዲ አረቢያ ካሉ የባህረ ሰላጤው ሃብታም ሀገራት ወጣቶች እስከ ዮርዳኖስ የሠራተኛው መደብ ድረስ ተወዳጅ ሆኗል።
በዮርዳኖስ ዋና ከተማ አማን በሚገኝ የተሃድሶ ክሊኒክ ከሱሱ ለመለያየት ህክምናውን የሚከታተል ያሲር የተባለ ወጣት “ካፒታገን መውሰድ ስጀምር 19 ዓመቴ ነበር። ከዚያ በኋላ ህይወቴ መፈራረስ ጀመረ። ይህን ከሚወስዱ ሰዎች ጋር መገናኘት ጀመርኩ። ትሰራለህ ያለ ምግብ ትኖራለህ። ስለዚህ ሰውነት ይጎዳል” ይላል።
ታዲያ አል-ሻራ እና ቡድኑ ሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) በሶሪያ እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የካፒታገን ሱስ የተጠናወታቸው ሰዎችን ከዕጹ ስርጭት እንዴት ሊያቆራርጡ ይችላሉ?
በኒው ላይን ኢንስቲትዩት የሶሪያ የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ባለሙያ የሆኑት ካሮላይን ሮዝ ስጋት አላቸው። “የእኔ ፍራቻ በአቅርቦት ላይ እርምጃ ቢወስዱም የፍላጎት መቀነስ እንዲኖር ግን ምንም አይሠሩም።”
እንዲህ ያለውን ትርፋማ ንግድ ማቋረጥ በሶሪያ ኢኮኖሚ ላይ ምን ተጽእኖ ይኖረዋል? የሚል ትልቅ ጥያቄም ያስነሳል። ከጀርባ ሆነው የሚሠሩት ወደ ጎን በማለታቸው አጋጣሚውን ለመጠቀም የሚቋምጡትንስ አል-ሻራ እንዴት ይቆጣጠራቸዋል?
የመካከለኛው ምስራቅ የዕፅ ጦርነት
የካፒታገን መስፋፋት መካከለኛውን ምስራቅ ወደ ዕፅ ጦርነት አስገብቶታል።
ዮርዳኖስ ድንበር ላይ ቁጥጥሯን ስታጠናክር በካፒታገን አዘዋዋሪዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ የአገሪቱ ጦር አባላት ተገድለዋል። ከድንበር ባሻገር የሚገኙ የሶሪያ ወታደሮች ሕገወጥ አዘዋዋሪዎቹን ይረዳሉ የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል።
ሌሎች የቀጠናው አገራትም በዕጽ ንግዱ መስፋፋት ተረብሸዋል።
ሳዑዲ አረቢያ ለተወሰነ ጊዜ ከሊባኖስ የሚገቡ የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ እገዳ ጥላ ነበር። ምክንያታቸው ደግሞ አንዳንድ ፍራፍሬዎች ተቦርቡረው በውስጣቸው የካፒታገን እንክብሎች እየተሞሉ በተደጋጋሚ ስለሚያገኙ ነበር።

ቢቢሲ በአገዛዙ እና በአማጽያን ቁጥጥር ስር የሚገኙትን የሶሪያ ግዛቶች ጨምሮ በአምስት አገራት የተደረገ ቀረጻን፣ ጥሩ መረጃ ያላቸውን ምንጮች ከማማከር ባለፈ በጉዳዩ ዙሪያ በጀርመን እና በሊባኖስ የሚገኙ የፍርድ ቤት ምስጢራዊ መረጃዎችን አግኝቷል።
በዚህም በንግዱ ውስጥ እጃቸውን ያስገቡ ሁለት ዋና ዋና አካላት መኖራቸው ታውቋል። እነዚህም የአሳድ ቤተሰብ አባላት እና የሶሪያ ጦር ኃይሎች በተለይም በአሳድ ወንድም ማኽር የሚመራው አራተኛው ክፍለ ጦር ናቸው።
ማኽር አል-አሳድ ከወንድሙ ቀጥሎ በሶሪያ ውስጥ በጣም ኃያለኛው ሰው እንደነበር ይታመናል።
እአአ በ2011 ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነትን በወለደው እና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በተደረገው ሕዝባዊ አመጽ ወቅት በተቃዋሚዎች ላይ ባስፈጸመው የኃይል እርምጃ በብዙ ምዕራባውያን ኃይሎች ማዕቀብ ተጥሎበታል።
የፈረንሳይ የፍትህ አካላት በበኩላቸው እአአ በ2013ቱ የሶሪያ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃት ተጠያቂ ናቸው በሚል በእሱን እና በወንድሙ ላይ ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣ አውጥተዋል።
ሊባኖስ ውስጥ ከታሰረ የካፒታገን ነጋዴ የዋትስአፕ መልዕክት መረዳት እንደሚቻለው የማኽር አል-አሳድ አራተኛ ክፍል ጦር እና ምክትል አዛዡ ጄኔራል ጋሳን ቢላል እጃቸው አለበት።
ይህም የሶሪያ ጦር እና የበሽር አል አሳድ የቅርብ ሰዎች በንግዱ ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማረጋገጥ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነበር።

አማጽያኑ አገሪቱን ለመቆጣጠር ሲገሰግሱ የነበረበት እና የአገዛዙ ጦር የሸሸበት መንገድ ባለፈው ዓመት አንድ የአገዛዙ ወታደር ያደረገውን ቃለ ምልልስ የሚያስታውስ ነው።
ወታደሩ በወር የሚያገኘው 30 ዶላር ከእነቤተሰቦቹ ለሦስት ቀናት የሚያቆውን ምግብ እንኳን እንደማይሸፍን ገልጾ ነበር። በዚህም ምክንያት የጦር አባላቱ በወንጀል እና በካፒታገን ንግድ ይሳተፋሉ።
“አሁን አብዛኛውን ገንዘብ የሚያስገኘው እሱ ነው” ብሎ ነበር።
ህዝባዊ አመጽን በኃይል በማፈን ከተባረረች ከ12 ዓመታት በኋላ ሶሪያን እአአ ግንቦት 2023 እንደገና ለመቀበል የአረብ ሊግ ተስማማ። የካፒታጎንን ንግድ ለመታደግ ቃል በመግባት ሶሪያን ወደ ሊጉ መመለስ ለአሳድ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ድል ተደርጎ ታይቷል።
የአማፂያኑ መሪዎች ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ?
የሶሪያ አማጺ መሪዎች የካፒታገን ንግድ ለመከላከል ቃል መግባታቸው ለጎረቤት አገሮች የሚያስተላልፈውን አዎንታዊ መልዕክቶች በሚገባ የተገነዘቡ ይመስላል።
በመንግስት ጭምር ሲበረታታ እና ለበርካታ ዓመታት አዋጭ የወንጀል ንግድ ሆኖ የቆየውን ንግድ መከላከል ከባድ የቤት ሥራ ሊሆንባቸው ይችላል።
ኢሳም አል ሬስ በአሳድ መንግስት ላይ በተነሳው ህዝባዊ አመጽ መጀመሪያ ላይ እስኪከዳ ድረስ በሶሪያ ጦር ያገለገለ ነበር። በካፒታገንን ንግድ ዙሪያም ምርመራ አካሂዷል። “ዋና ዋና ተዋናዮች” በመሸሻቸው ኤችቲኤስ ንግዱን ለማቆም መጀመሪያ ላይ ብዙ መሥራት አያስፈልገውም ብሎ ያምናል። ወደ ውጭ የሚላከው የካፒታገን መጠንም በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ አሳይቷል። “አዳዲስ ሰዎች” ዕድሉን ለመጠቀም እየጠበቁ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግን አስጠንቅቋል።
ፍላጎቱ አለመቀነሱ ግን ችግር ይፈጥራል። ኤች ቲ ኤስ በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ የሚገኘውን የኢድሊብ ግዛትን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ሱስ ለያዛቸው ሰዎች ሚሆን የህክምና ተቋም ላይ ብዙም ገንዘብ አለማፍሰሳቸውን ሮዝ ተናግረዋል ። “የካፒታገንን ችግር ለመቅረፍ በመሞከር ረገድ በጣም ደካማ ሥራ ነው የተከናወነው” ብለዋል።
በሶሪያ ውስጥ ሌላ ዕጽ ከወዲሁ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።
“ብዙ ተጠቃሚዎች ክሪስታል ሜቲንን እንደ አማራጭ ይፈልጉታል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ካፒታገንን የለመዱ ሰዎች ትንሽ ጠንከር ያለ ነገር ያስፈልጋቸዋል።”
እንደአል ሪስ ሌላኛው ፈተና የገንዘብ ችግር ነው። “ሶሪያውያን ገንዘቡን ይፈልጋሉ” ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰዎች ወደ አደንዛዥ ዕጽ ንግድ እንዳይገቡ ሰብአዊ እርዳታ በማቅረብ እና ማዕቀቡን በማቃለል እንደሚረዳቸው ተስፋ ሰንቀዋል።
ሮዝ በበኩላቸው አዲሶቹ መሪዎች “ሶሪያውያን በመደበኛ ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲሳተፉ ለማበረታታት አዲስ እና አማራጭ ኢኮኖሚያዊ መንገዶችን” መለየት አለባቸው ሲሉ ተከራክረዋል።
ዋና ዋናዎቹ ሰዎች ቢሰደዱም ዕጹን በማምረትና በማዘዋወር ላይ የተሰማሩት ብዙዎቹ ሰዎች አሁንም በአገሪቱ ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል።
“የቆየ ልማድ ለመጥፋት ጊዜ ይፈጃል” ብለዋል።