
ከ 2 ሰአት በፊት
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመራ ገብተዋል።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስቴር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው እንዳስታወቁት የኤርትራና የሶማሊያ መሪዎች በሁለትዮሽ እና በቀጣናዊ ጉዳይ “ጥልቅ ውይይት” አድርገዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አስመራ ሲገቡ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የአስመራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት በነገሠበት ወቅት ነው።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሰነድ መፈረሟን ተከትሎ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ከዓመት በላይ የቀየ ውጥረት የነበረ ሲሆን፣ ይህን ለማርገብ በቱርክ አንካራ የሁለቱ አገራት መሪዎች ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ሆኖም ግን ከቀናት በፊት የሶማሊያ ልዑካን ከኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ጋር ለመወያየት አዲስ አበባ ሳሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሶማሊያን ድንበር ጥሰው “ጥቃት ፈጽመዋል” ስትል ሞጋዲሹ ከሳለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን አስተባብሎ ለክስተቱ ተጠያቂ “ሦስተኛ ወገኖች” ናቸው ብሏል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ ውስጥ በነበሩበት ወራት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ በተደጋጋሚ ወደ አስመራ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ተጉዘዋል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያው ግንኙነት መሻከሩ እየተገለጸ ባለበት ወቅት፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እንዲሁም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበው ግብፅ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
ሶማሊያ ከግብፅ ጋር የወታደራዊ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ አስመራ ላይ የተፈረመው የሦስትዮሽ ስምምነት ከኢትዮጵያ አንጻር መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።
የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ታኅሣሥ መባቻ ላይ በመንግሥታቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ስለወቅታዊ ጉዳዮች ቃለ ምልልስ በሰጡበት ወቅት ይህንን አስተባብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ መተላለፊያ እንዲሁም ሚና እንዲኖራት ያላትን ፍላጎት ይፋ ካደረገች በኋላ በቀጥታም ባይሆን ኤርትራ ደስተኛ አለመሆኗን ስታሳይ ቆይታለች።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኤርትራ ከሦስት ጊዜ በላይ ጉብኝት አድርገዋል።
- የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመራ ገቡ25 ታህሳስ 2024
- የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስለኢትዮጵያ ምን አሉ?1 ታህሳስ 2024
- ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከስምምነት የደረሱበት ሰነድ ምን ይዟል?12 ታህሳስ 2024

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ለምን አስመራ ይመላለሳሉ?
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ አንካራ ላይ ተገኝተው ውይይት ካደረጉ በኋላ ስምምነት ላይ መድረሳቸው አይዘነጋም።
የአገራቱ መሪዎች ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ስምምነቱ ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የባሕር መተላላፊ በር እንድታገኝ የሚያደርግ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ “በሶማሊያ ሉዓላዊ ሥልጣን ሥር አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ዘላቂ የባሕር መተላለፊያ” እንድታገኝ የሚያስችል የንግድ እና የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ በቅርበት እንደሚሠሩ ተጠቅሷል።
መቀመጫቸውን ለንደን ያደረጉትና የምሥራቅ አፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካዊ ሁኔታን የሚተነትኑት አቶ አብዱራህማን ሰዒድ “ጉብኝቱ ከአንካራ ስምምነት በኋላ ነው የመጣው። ምናልባት በሶማሊያ በኩል የስምምነቱ ይዘትና አተገባበር የጋራ መረዳት እንዲኖራቸው ሊፈልጉ ይችላሉ” ሲሉ የጉብኝቱን ምክንያት ያስረዳሉ።
ኤርትራ፣ ግብፅ እና ሶማሊያ የሦስትዮሽ ስምምነት በመፈራረማቸው “የተለየ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር ሲፈራሙ ሌላ ስምምነት ላይ ላሉ አገሮች ማብራሪያ መስጠትና መወያየት በዲፕሎማሲ ውስጥ ያለ ነገር ነው” ሲሉም ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስለ ባሕር በር የሚከተሉት ፖሊሲ “ሁሉንም አገሮች እያሰጋቸው መምጣቱንም ያሳያል። ሶማሊያና ኤርትራ ይህ ያስጨንቃቸዋል” ሲሉ የጉብኝቱን ሌላ ምክንያት ሊሆን የሚችለውን ያስቀምጣሉ።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአንካራ ስምምነት ላይ ቢደርሱም “ግንኙነታቸው ግን ገና አልተሻሻለም። ጊዜ ሊወስድ ይችላል” ሲሉ ተንታኙ ያስረዳሉ።
“የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ መውጣት ይፈልጋሉ ወይስ አይፈልጉም? የሚለው ሌላ ፈታኝ ጉዳይ ነው። ሊያጋጭ ይችላል። በተለይ በሶማሊያ የግብፅ ሠራዊት የሚኖር ከሆነ ፈጽሞ መውጣት ላይፈልጉ ይችላሉ።”
“ኢትዮጵያውያን ለሶማሊላንድም ይሁን ለጁባላንድ የሚያደርጉት ድጋፍ ሊያቆሙ ይችላሉ? የሚለውም ሌላ ፈታኝ ነጥብ ነው። እነዚህን እየተሻገሩ ነው ስምምነቱን ወደማስተግበር ሊደርሱ የሚችሉት። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ችግር የሚፈጥሩ ነገሮችን ማቆም የሚችሉ አይመስለኝም” ሲሉም አቶ አብዱራህማን ያስረዳሉ።
በእነዚህ “ችግሮች” ምክንያት ሶማሊያ ከግብፅ፣ ከኤርትራ፣ ከቱርክና ከሌሎችም አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት “አጠናክራ መቀጠል ትፈልጋለች” በማለት ያብራራሉ።
በአንካራ ስምምነት የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ሕብረት ደንቦች ላይ የሰፈሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ለማክበር ተስማምተዋል።
ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና እንደምትሰጥም በስምምነቱ ተካቷል።
“የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ” ሲልም የስምምነት ሰነዱ ያትታል።
ሁለቱ አገራት በቱርክ አመቻቻነት በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ የቴክኒካዊ ጉዳዮች ድርድር ማድረግ እንደሚጀምሩና ይህም በአራት ወራት ውስጥ እንደሚቋጭ ተገልጿል።
የሶማሊያ፣ ግብፅ እና ኤርትራ ጥምረት
ሦስቱ አገራት በጋራ መጣመራቸው ኢትዮጵያን ወደ አንካራ ስምምነት ገፍቷት ሊሆን እንደሚችል ተንታኙ አቶ አብዱራህማን ያምናሉ።
የኢትዮጵያ ወደ ስምምነቱ መግባት “ጥምረቱን ለማስቆም ያለመ ሊሆን ይችላል” ይላሉ።
“ሶማሊያ ይሄንን ስለምታውቅ [ከኤርትራና ከግብፅ] ያላትን ግንኙነት በቀላሉ መተው አትፈልግም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ በኩል ማረጋገጫ አልተሰጣቸውም” በማለትም ይገልጻሉ።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ለምን ወደ ኤርትራ በተደጋጋሚ ይጓዛሉ? በሚል የተጠየቁት ተንታኙ “ጉዳዩ የደኅንነት ነው” ሲሉ ይመልሳሉ።
“ለንግድና ለኢኮኖሚ ቢባልም ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ተደርጎ [የምጣኔ ሀብት] ትርፍ የለም። ኤርትራ በኢኮኖሚ ተቋማት የምትመራ አይደለችም። የግሉም የመንግሥትም ዘርፍ ምስቅልቅሉ የወጣ ነው። የሚገናኙበት ዋናው ምክንያት የደኅንነት ጉዳይ ነው። ለሶማሊያና ለኤርትራ የጋራ የደኅንነት ስጋት ደግሞ ኢትዮጵያ ናት።”
ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንበር አልፈው “ጥቃት ፈጽመዋል” ስትል ብትከስም ኢትዮጵያ ግን ለክስተቱ “ሦስተኛ ወገን” ያለቻቸውን አካላት ተጠያቂ አድርጋለች።
ሁለቱ አገራት እርስ በእርስ በሚካሰሱበት ወቅት ደግሞ በአዲስ አበባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ዓሊ ሞሐመድ ኦማር ጋር መወያየታቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሶማሊያው አቻቸው አብዱላሂ ሞሐመድ ጋር መወያየታቸው ተዘግቧል።
ሁለቱ አገራት መካሰሳቸው ለአንካራው ስምምነት ስጋት ይሆናል? በሚል ከቢቢሲ የተጠየቁት የምሥራቅ አፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካዊ ሁኔታን የሚተነትኑት አቶ አብዱራህማን “አዎን ስጋት ይሆናል፤ አደገኛ ነው” ሲሉ ይመልሳሉ።