የኪዬቭ ነዋሪዎች በባቡር ጣብያዎች ተጠልለዋል

26 ታህሳስ 2024, 09:25 EAT

ተሻሽሏል ከ 4 ሰአት በፊት

ሩስያ “ሆን ብላ” የገናን በዓል ጠብቃ በአገራቸው የኃይል መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጥቃት አድርጋለች ሲሉ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ገለጹ።

የዩክሬን አየር ኃይል 184 ሚሳዔሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች እንደነበሩ እና በርካቶቹ መመታታቸውን አስታውቋል።

በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች እንዳሉ ቢገልጽም ቁጥራቸው ይፋ አልሆነም።

ሞስኮው ጥቃቱን መፈጸሟን አረጋግጣ ግቧ መሳካቱን ተናግራለች።

በጥቃቱ ዋና ከተማይዋ ኪዬቭን ጨምሮ በመላ አገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ የተፈጠረ ሲሆን አንዳንድ ነዋሪዎች በባቡር ጣቢያዎች ለመጠለል ተገደዋል።

ሰራዊቱ በዩክሬን ውስጥ “ወሳኝ” የኃይል ማመንጫዎች ላይ “ትልቅ ጥቃት” መፈፀሙን የሩስያ ጦር አረጋግጧል።

ጥቃቱ የተሳካ እንደነበርና ሁሉም ዒላማዎች መምታታቸውንም አክሏል።

በዚህ ዓመት በዩክሬን የኃይል ዘርፍ ላይ ጥቃት ሲሰነዘር የአሁኑ ለ13ኛ ጊዜ መሆኑን የአገሪቱ ትልቁ የግል ኃይል ኩባንያ ዲቴክ ገልጿል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቃቱን ተከትሎ “የዚህ አሰቃቂ ጥቃት ዓላማ ዩክሬናዊያን በክረምት ወቅት የሚያገኙትን ሙቀት እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማቋረጥ እና የኃይል ማመንጫዎቹን ደህንነትን አደጋ ላይ ለመጣል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ከቀናት በኋላ በዶናልድ ትራምፕ የሚተኩት ፕሬዝዳንት ባይደን የመከላከያ ሚንስትራቸው የጦር መሣሪያ ወደ ዩክሬን ማድረሱን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ 80 በመቶ የሚሆነው የዩክሬን የኢነርጂ መሠረተ ልማት በሩሲያ ቦምቦች ወድሟል ሲሉ ባለፈው መስከረም ተናግረው ነበር።

ረቡዕ ዕለት የተደረጉ ጥቃቶች በተመለከተም ዜለንስኪ “ሆን ተብሎ የተደረገ” ነው ብለዋል።

ጥቃቱን “ሰብአዊነት የጎደለው” ሲሉ ገልጸው የኃይል ማመንጫዎችን በተቻለ ፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ነው ብለዋል።

“የሩሲያ ክፋት ዩክሬንን አያፈርስም፤ የገና በዓልንም አያሰናክልም” ሲሉ አክለዋል።

ዩክሬን የገና ዓልን በአውሮፓውያኑ ታህሳስ 16 ስታከብር ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በተለምዶ የጁሊያን የቀን አቆጣጠርን ስለምትከተል እንደ ሩስያ ሁሉ የገና በዓል ታህሳስ 29 ነው የምታከብረው።

አሁንም ግን በአገሪቱ የሚገኙ ቁጥራቸው የበዛ የኦርቶዶክስ አማኞች ገናን በበፊቱ ቀን ያከብራሉ።

በዃርኪቭ 74 ህንጻዎች ጉዳት አስተናግደዋል

በሰሜን ምስራቅ በምትገኘው ዩክሬን ሁለተኛዋ የካርኪቭ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ውሃ፣ ኤሌክትሪክ ወይም ማሞቂያ አጥተው በአስከፊ ቅዝቃዜ ውስጥ እንደሚገኙ የክልሉ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።

በመላ አገሪቱ ያሉ ዩክሬናውያን በማንቂያ ደወል ከእንቅልፋቸው ተቀስቅሰው ከጥቃቱ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ተነግሯቸዋል።

የኪዬቭ ነዋሪዎች በሜትሮ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለዋል። አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ንዴት እና ፍርሃት እንደተሰማት ተናግራለች።

“በእርግጥ ቤት ውስጥ ሆኜ [በዓሉን] ማክበር እፈልጋለሁ። ነገር ግን ቤት ውስጥ መቆየት ስለሚያስፈራ መጠለል ነበረብን” ስትል ሶፊያ ሊቲቪንኮ ገልጻለች።

ኦሌክሳንድራ የተባለች ሌላ የኪዬቭ ነዋሪ ደግሞ ጥቃቱ ቢደርስም “የገና በዓል አልተሰረዘም” ብላለች።

መጠለያውን ለቀው መውጣት ሲችሉ ከቤተሰቧ እና ከጓደኞቿ ጋር በባሕላዊው የዩክሬን ምግብ እና መጠጥ ለመደሰት እንዳቀደች ለሮይተርስ ተናግራለች።

መንግስታዊው የዩክሬን ኃይል ኩባንያ ዩክሬነርጎ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ቢያንስ እስከ ቀኑ መጨረሻ ድረስ ሊቆይ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

አገልግሎቱን ወደነበረበት ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሶ የአጠቃቀም ገደቦችን ይፋ አድርጓል።

የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ ደግሞ ጥቃቱን “የገና ሽብር” ሲሉ ገልጸውታል።

የሩስያ ሚሳኤል በሞልዶቫ እና ሮማኒያ የአየር ክልል ውስጥ ማለፉን በማንሳት “ሩስያ የምታስፈራራው ዩክሬንን ብቻ አለመሆኑን” ለማስታወስ ነው ብለዋል።

የሞልዶቫ ፕሬዝደንት ማይያ ሳንዱ ጥቃቱን አውግዘው በአገሪቱ የአየር ክልል ውስጥ ሚሳዔል ማለፉን አረጋግጠዋል።

ሮማኒያ በአየር ክልሏ ውስጥ ሚሳዔል እንዳላለፈ ተናግራለች።

በሌላ በኩል ደግሞ ዩክሬይን በሩስያዋ ኩርስክ ክልል በፈጸመችው ጥቃት አራት ሰዎች ሲሞቱ አምስት ሰዎች ቆስለዋል ሲሉ የክልሉ ተጠባባቂ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።