December 26, 2024 – Konjit Sitotaw
የሶማሌላንድ መንግሥት፣ የኢትዮጵያው ሶማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች ደዋሌ በተባለ አካባቢ በሲቪሎች ላይ ይፈጽሙታል ያለውን ጥቃት አውግዟል።
የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች ንጹሃን አርብቶ አደሮችን ገድለዋል፤ ባካባቢው ያለውን ግጭት በሽምግልና ለመፍታት የሄዱ የሶማሌላንድ ሽማግሌዎችን አፍነው ወስደዋል በማለት የራስ ገዟ መንግሥት ከሷል።
የክልሉ ልዩ ኃይሎች ድርጊት “ዓለማቀፍ ደንቦችን ይጻረራል” ያለችው ሶማሌላንድ፣ ጥቃቱን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ እንዲኾኑ ጠይቃለች።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር በክስተቱ እንዳዘኑ ለሶማሌላንድ መንግሥት እንደገለጡ፣ ሶማሌላንድም ጉዳዩን ለኢትዮጵያ መንግሥት እንዳሳወቀችና ኹለቱ መንግሥታት በክስተቱ ዙሪያ ለመነጋገር ለዛሬ ቀጠሮ እንደያዙ ተነግሯል።
ደዋሌ የኢሳቅ ጎሳ አባላት በብዛት የሚኖሩባት ስትኾን፣ የሴማሌላንድ ትልቁ ጎሳም ኢሳቅ ነው።