(መሠረት ሚድያ)- በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ በቅርብ ግዜያት ከተሰሩ የኮሪደር ልማቶች ጋር ተያይዞ ለተተከሉ የመንገድ ዳር አትክልትና ሳር ለማጠጣት የሚውለው ውሀ ለነዋሪዎች መጠጥ ከሚያገለግል የውሀ መስመር በመሆኑ ህዝቡ ውሀ መቸገሩ ታወቀ።
በኮሪደር ልማት ለተተከሉት አትክልትና ሳር ጠዋትና ማታ ውሀ የሚያጠጡት ተሽከርካሪዎች ለነዋሪው ለመጠጥ ከሚያገለግል የውሀ መስመር ሀይድራንቶች ላይ እንደሚቀዱ መሠረት ሚድያ ከአዲስ አበባ ውሀ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ምንጮቹ አረጋግጧል።
ሀያ ሺህ ሊትር ገደማ የሚይዙ ትልልቅ ቦቴዎች ለመጠጥ ከሚውል የውሀ ሀይድራንቶች እየቀዱ አትክልት ማጠጣታቸው ወትሮም የውሀ እጥረት ላለባት ከተማ ፈተና እንደሆነ ታውቋል።
“በሳምንት አንድ ቀን ውሀ ሲያገኝ የነበረው የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም እና ሌሎች ተመሳሳይ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች የውሀ ፈረቃቸው በሁለት ሳምንት አንዴ እየሆ ነው” ያሉት የመረጃው ባለቤት በእነዚህ ቦታዎች ያሉ ነዋሪዎች በውሀ እጥረት ክፉኛ እየተጎዱ ነው ብለዋል።
“ቤቶቹ የሽንት ቤቶቻቸው ሽታ ሳሎን አያስቀምጡም፣ የውሀ እጥረት ስላለ ፎቅ ላይ አይወጣም” ያሉን አንድ የኮዬ ፈጬ ነዋሪ “ስንት ወንዝ ባለበት ከተማ ከዛ ውሀ ቀድተው ለአትክልት መጠቀም ሲችሉ ነዋሪውን በውሀ ችግር ማሰቃየታቸው ሚያሳዝን ነው” ብለዋል።