(መሠረት ሚድያ)- ከተመሰረተ 12 አመታትን ያስቆጠረው እና በ2013 ዓ/ም በምርጫ ዋዜማ የተመረቀው ግዙፉ የጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክት የመፍረስ አደጋ ላይ እንደሚገኝ ለመሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
በተለያዩ ምክንያቶች በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ያልገባው ፕሮጀክቱ ከ1,500 እስከ 1,600 ቋሚ ሰራተኞች እና በርካታ ጊዚያዊ የቀን ሰራተኞችን ይዞ የነበረ ቢሆንም ከዚህ ውስጥ 430 ሰራተኞች ብቻ እንደሚቀሩ እና የተወሰኑ ሰራተኞች ወደ ሌሎች የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች እንዲሄዱ እየተደረገ እንደሆነ ታውቋል፣ በተጨማሪም አብዛኛው ሰራተኛ ከስራ የመፈናቀል ስጋት ላይ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ ይህን ያደረገው በዋናነት በአገዳ እጥረት ነው ቢልም የሀገራችን እና የክልሉ ውስብስብ ፖለቲካ መጥፎ አሻራውን ማሳረፍ ቀጥሏል ተብሏል።
ለዚህ ማሳያ ደግሞ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም መከላከያ እንደ ካምፕ እየተጠቀሙበት የሚገኙ ሲሆን ፕሮጀክቱ ውስጥ ያሉ አልሙናየም እና ብረታ ብረት በችርቻሮ በኮንትሮባንድ እየተሸጡ መሆኑ ተደርሶበታል።
ፕሮጀክቱ የአካባቢው ማህበረሰብ መሬቱን ለልማት ሲለቅ እና ያለ በቂ ካሳ ይህን ያህል ዓመት ወደ ምርት አለመግባቱ ትልቅ ቁጭት ፈጥሯል ።
በክልሉ ብሎም በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግም ፕሮጀክቱ በቀጣይ ከስኳር ልማት ይልቅ ወደ ወታደራዊ ካምፕነት ሊቀየር የታሰበ ይመስላል ያሉን ምንጮቻችን ይህም በክልሉ አንድ ለእናቱ የሆነን ግዙፍ ፕሮጀክት ለመዝጋት ጫፍ ደርሷል ብለዋል።
“በክልሉ ብሎም ሀገሪቷ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ከማድረሱ በፊት ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ይህን ፕሮጀክት ከመፍረስ እንድታድኑ ጥሪ እናቀርባለን” ብለው ሰራተኞቹ ለመሠረት ሚድያ ጥቆማቸውን ልከዋል።