- የ2018 ሀገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ሚድያዎችን እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በገፍ ለመዝጋት መታቀዱ ታወቀ
- – ቢያንስ 10 የግል ሚድያዎችን እና ከ80 ያላነሱ ሚድያዎችን ለመዝጋት እቅድ ወጥቷል
(መሠረት ሚድያ)- በግንቦት ወር 2018 ዓ/ም ይደረጋል ተብሎ ከሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ በፊት በርካታ የግል ሚድያዎችን እና የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን መንግስት ሊዘጋ እንዳሰበ መሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ያሳያል።
አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመንግስት አመራር ስሜ አይጠቀስ ብለው ለሚድያችን በሰጡት መረጃ ቢያንስ 10 የግል ሚድያዎችን እና ከ80 ያላነሱ ሚድያዎችን ለመዝጋት እቅድ ወጥቷል።
“እቅዱ ላይ የተቀመጠው ለምርጫው ሂደት ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ፣ ከተሰጣቸው mandate ውጪ እየተንቀሳቀሱ ነው እንዲሁም የውጭ ሀገራትን ተፅእኖ ያስፋፋሉ የሚል ነው” ያሉት ምንጫችን አተገባበሩ በቅርቡ መጀመሩን ጠቅሰው በቀጣይ ሳምንታት በስፋት እንደሚተተገበር ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ሚድያዎችን በተመለከተ ጉዳዩን እያስፈፀሙ ያሉት አካላት ስራቸውን ቀደም ብለው እንደጀመሩ የታወቀ ሲሆን አራት የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ደግሞ ከአሁኑ ተዘግተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን (EHRDC)፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች (LHR) እስካሁን በመንግስት የተዘጉ ተቋማት ናቸው።
ገለልተኛ ባለመሆን እና ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ በመንቀሳቀስ የሚሉ ክሶች የደረሷቸው እነዚህ ተቋማት ውንጀላውን ተቃውመው በህግ አግባብ ጉዳዩን እየተከታተሉ እንደሆነ አሳውቀዋል።