ውሃ የሚካፈሉ ህንዳውያን ስደተኞች
የምስሉ መግለጫ,ሰኔ ወር ላይ ህንዳውያን ስደተኞች ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ ከገቡ በኋላ በነበረው ከፍተኛ ሙቀት የተነሳ ውሃ ሲካፈሉ ታይተዋል።

ከ 6 ሰአት በፊት

ባለፈው ጥቅምት ወር የአሜሪካው ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ማስፈጸሚያ (አይሲኢ) የሕንድ ዜጎችን በቻርተርድ አውሮፕላን ወደ አገራቸው ልኳል።በተመሳሳይ መንገድ ሕንዳውያን ከአሜሪካ ተጠርንፈው የመላካቸው አዝማሚያ እየጨመረ ነው።

በረራው ተራ የሚባል ዓይነት አልነበረም።በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ሕንዳውያንን ወደ አገራቸው ለማባረር ከተደረጉት በርካታ በረራዎች መካከል አንዱ ነው።በእያንዳንዱ በረራ ከ100 በላይ መንገደኞች ናቸው የሚሳፈሩት።እነዚህ አውሮፕላኖች “በአሜሪካ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ሕጋዊ ሂደት ያልጀመሩ” የሕንድ ስደተኞችን ጭነው ይወጣሉ።

እንደ አሜሪካ ባለስልጣናት ገለጻ ከሆነ የመጨረሻው በረራው ሕንዳውያኑን አሳፍሮ ወደ ፑንጃብ ወስዷል። የብዙዎቹ መነሻም ፑንጃብ ናት።የተመላሾቹ ትክክለኛ አድራሻ ግን አልተገለጸም።

በመስከረም ወር 2024 በተጠናቀቀው የአሜሪካ የበጀት ዓመት ከአንድ ሺህ በላይ የሕንድ ዜጎች በቻርተር እና በመደበኛ በረራዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል ሲሉ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት ቢሮ ረዳት ጸሐፊ ሮይስ በርንስታይን ሙሬይ ተናግረዋል።

“ይህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከአሜሪካ የሚባረሩ ሕንዳውያን ቁጥር መጨመሩን ያሳያል።በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ አሜሪካ የሚገቡ የሕንድ ዜጎች ቁጥር መጨመር ጋር የሚገናኝ ነው” ሲሉ ሙሬይ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

በአሜሪካ ጥገኝነት ለመጠየቅ የሚፈልጉ ሕንዳውያን

አሜሪካ የሕንድ ዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለስ ሂደትን ባሳደገችበት በዚህ ወቅት፣የተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ ሁኔታውን ወዴት ይወስደዋል የሚል ስጋት እየጨመረ ነው።

ትራምፕ በታሪክ በርካታ የሆኑ ስደተኞችን እንደሚያባርሩ ቃል ገብተዋል።

ከጥቅምት 2020 ወዲህ የአሜሪካ የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ (ሲፒቢ) ባለስልጣናት በሰሜን እና በደቡብ ድንበሮች በኩል በሕገ ወጥ መንገድ ለመሻገር የሞከሩ ወደ 170 ሺህ የሚጠጉ ሕንዳውያን ስደተኞችን ይዘዋል።

“ከላቲን አሜሪካ እና ከካሪቢያን ዜጎች አንጻር ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም፣ባለፉት አራት ዓመታት በሲቢፒ ባልደረቦች በቁጥጥር ሥር የዋሉ የሕንድ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው” ሲሉ በኒስካነን ማዕከል የኢሚግሬሽን ተንታኞች የሆኑት ጊል ጉሬራ እና ስኔሃ ፑሪ ተናግረዋል።

እአአ እስከ 2022 ድረስ 725 ሺህ የሚገመቱ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የሕንድ ስደተኞች አሜሪካ ውስጥ ይኖሩ ነበር።ይህ ቁጥር ከሜክሲኮ እና ኤል ሳልቫዶር በመቀጠል ሦስተኛው አድርጓቸዋል ሲል በዋሽንግተን ዲሲ ተቀማጭነቱን ያደረገው የፔው የምርምር ማዕከል አዲስ መረጃ ያሳያል።

ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች ከጠቅላላው የአሜሪካ ሕዝብ 3 በመቶውን ሲይዙ በውጭ አገር ከተወለዱት ውስጥ ደግሞ 22 በመቶውን ይሸፍናሉ።

ድንበር አካባቢ እየተራመዱ ያሉ ሕንዳውያን

መረጃውን የተመለከቱት የኢምግሬሽን ተንታኞቹ ጉሬራ እና ፑሪ በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማቋረጥ የሚሞክሩ ሕንዳውያን ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።

አንደኛ፣ስደተኞቹ ዝቅተኛው ኢኮኖሚ ደረጃ ያላቸው አይደሉም።ባላቸው ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ወይም የእንግሊዝኛ ችሎታ ምክንያትም ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያስችላቸውን የቱሪስት ወይም የተማሪ ቪዛ ማግኘት አይችሉም።

ከዚህ ይልቅ እስከ100 ሺህ ዶላር በሚያስከፍሉ ኤጀንሲዎች ላይ ይተማመናሉ።አንዳንዴም ድንበር ጥሰው ለማለፍ ረዥም እና አድካሚ መንገዶችን ይጠቀማሉ።ይህንን ለማሳካት ብዙዎቹ የእርሻ መሬታቸውን ይሸጣሉ አሊያም ብድር ይወስዳሉ።ከአሜሪካ የስደተኞች ፍርድ ቤቶች እአአ በ2024 የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ አብዛኞቹ የሕንድ ስደተኞች ወንዶች ሲሆኑ ዕድሜያቸውም ከ18 እስከ 34 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው።

ሁለተኛ፣በሰሜናዊ አቅጣጫ የምትገኘው ካናዳ ለሕንዶች ምቹ የመግቢያ በር ሆናለች።ለካናዳ የሚሆን የጉብኝት ቪዛ ለማግኘት 76 ቀናት ብቻ ይጠይቃል (በሕንድ ያለው የአሜሪካ ቪዛ ሂደት እስከ አንድ ዓመት ይፈጃል)።

የቬርሞንት ግዛቶችን እና በኒውዮርክ እና ኒው ሃምፕሻየር ግዛቶችን የሚሸፍነው የድንበር ተቆጣጣሪ አካል ከዚህ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ከሕንድ ዜጎች ጋር በተገናኘ ጭማሪ አጋጥሞታል።በሰኔ ወር ቁጥሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ 2 ሺህ 715 እንደነበር አጥኝዎቹ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል አብዛኛዎቹ ሕገወጥ የሕንድ ስደተኞች ወደ አሜሪካ የገቡት በደቡባዊ ድንበር በኩልሜክሲኮን አቋርጠው ነው።ሜክሲኮ የሚደርሱት ደግሞ በኤል ሳልቫዶር ወይም በኒካራጓ አቋርጠው ነው።እስከ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ድረስ የሕንድ ዜጎች ወደ ኤልሳልቫዶር የሚጓዙት ከቪዛ ነጻ ነበር።

እንደ አውሮፓውያኑ 2023 ሕንዳውያን ስደተኞች የአሜሪካ - ሚክሲኮን ድንበር አቋርጠው ወደ አሜሪካ ሲገቡ
የምስሉ መግለጫ,እንደ አውሮፓውያኑ 2023 ሕንዳውያን ስደተኞች የአሜሪካ – ሜክሲኮን ድንበር አቋርጠው ወደ አሜሪካ ሲገቡ

“የአሜሪካ-ካናዳ ድንበር፣ ከአሜሪካ – ሜክሲኮ ድንበር የበለጠ ረዥም እና አነስተኛ ጥበቃ የሚደረግለት ነው። ደኅንነቱ የበለጠ አስተማማኝ ባይሆንም ከደቡብ እና ከማዕከላዊ አሜሪካ ከሚወስደው መንገድ አንጻር ወንጀለኛ ቡድኖች የሉም።” ሲሉ ጉሬራ እና ፑሪ ይናገራሉ።

ሦስተኛ፣ አብዛኞቹ ስደተኞች በርካታ የሲክ እምነት ተከታዮች ካሉባት የሕንዷ ፑንጃብ ግዛት እና ከአጎራባቹ ሃሪያና የሚነሱ ይመስላል።አካባቢው በተለምዶ ሰዎች ወደ ባሕር ማዶ በስፋት የሚሰደዱበት ነው።ሌላው የስደተኞች መነሻ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የትውልድ ግዛት ከሆነችው ጉጃራት ነው።

ሕገወጥ የሕንድ ስደተኞች በብዛት ያሉባት ፑንጃብ ከፍተኛ የሥራ አጥነት፣የእርሻ ችግር እና የመድኃኒት ቀውስን ጨምሮ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋርጠውባታል።

በፑንጃቦች ዘንድ ስደት ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ የተለመደ ነበር።የገጠር ወጣቶች አሁንም ወደ ውጭ አገር የመሰደድ ፍላጎት አላቸው።

በቅርቡ በፑንጃብ 120 ሰዎች ላይ በናቭጆት ካዉር፣ጋጋንፕሪት ካዉር እና ላቭጂት ካኡር የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 56 በመቶ የሚሆኑት ከ18 እስከ 28 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላ ይሰደዳሉ።

ብዙዎቹ ከፋይናንስ ተቋማት ውጭ ብድሮችን ወስደው ከተሰደዱ በኋላ ገንዘቡን ወደ ቤተሰቦቻቸው ይልካሉ።

ለሲኮች ነጻ የሆነች አገር ለመመስረት በሚፈልገው በተገንጣዩ የካሊስታን እንቅስቃሴ ምክንያትም ውጥረት ነግሷል።

“ይህ ደግሞ በሕንድ ባሉ አንዳንድ የሲክ እምነት ተከታዮች ዘንድ ባለስልጣናት ወይም ፖለቲከኞች ፍትሃዊ ያልሆነ ጥቃት ይደርስብናል የሚል ስጋት ፈጥሮባቸዋል።እውነትም ባይሆን እንኳ ይህ ፍርሃት ጥገኝነት እንዲጠይቁ ምክንያት አድርገው ሊያቀርቡት ይችላሉ።” ሲሉ ፑሪ ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ከጉጃራት የተነሱ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት ወደ አሜሪካ ለመግባት ሲሞክሩ ከካናዳ ድንበር 12 ሜትር ርቀት ላይ በቅዝቃዜ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።
የምስሉ መግለጫ,ከሁለት ዓመት በፊት ከጉጃራት የተነሱ አራት የአንድ ቤተሰብ አባላት ወደ አሜሪካ ለመግባት ሲሞክሩ ከካናዳ ድንበር 12 ሜትር ርቀት ላይ በቅዝቃዜ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።

ትክክለኛውን የስደት ምክንያት ማወቅ ፈታኝ ነው።

“ምክንያቱ ቢለያይም ኢኮኖሚያዊ ዕድል ቀዳሚው ሲሆን የተጠናከረ ማኅበራዊ ትስስር እና በአሜሪካ የሚኖሩ የቤተሰብ አባላት መኖር የሚፈጥረው የኩራት ስሜት ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ሆነው ይቀጥላሉ።” ሲሉ ፑሪ ተናግረዋል።

አራተኛ፣በድንበር አካባቢ የሕንድ ዜጎች ቤተሰባዊ ሥነ-ሕዝብ ለውጥ መኖሩን ተመራማሪዎች ተመልክተዋል።

በርካታ ቤተሰቦች ድንበሩን ለማቋረጥ እየሞከሩ ነው።እአአ በ2021 በርካታ ያላገቡ ጎልማሶች በሁለቱም ድንበሮች ተይዘዋል።አሁን ግን በሁለቱም ድንበሮች በኩል ቤተሰብ ሆነው የሚንቀሳቀሱት ቁጥር ከ16 እስከ18 በመቶ ይሆናሉ።

ይህ ግን አንዳንድ ጊዜ አሳዛኝ ውጤቶችን ያስከትላል።እአአ በጥር 2022 ከጉጅራት የተነሳ አንድ የሕንድ ቤተሰብ አራት አባላት ወደ አሜሪካ ለመግባት ሲሞክሩ ከካናዳ ድንበር 12 ሜትር ርቀት ላይ በቅዝቃዜ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።

በቬርሞንት ዩኒቨርሲቲ የፍልሰት እና የከተማ ጥናት ምሁር የሆኑት ፓብሎ ቦዝ በበኩላቸው ሕንዶች በብዛት ወደ አሜሪካ ለመሻገር እየሞከሩ ያሉት በዋነኝነት ኢኮኖሚያዊ ዕድሎች እና እንደ ኒው ዮርክ ወይም ቦስተን ባሉ ትላልቅ “የአሜሪካ ከተሞች ውስጥ መደበኛ ባልሆነ ሥራ ላይ ለመሰማራት የበለጠ ዕድል” ስላላቸው ነው ብለዋል።

ሕንዳዊያን ስደተኞች
የምስሉ መግለጫ,የጉምሩክ እና ድንበር ተቆጣጣሪዎች ባለፈው ሰኔ ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ ሲገቡ የያዟቸውን ስደተኞች ተሽከርካሪ ላይ ሲጭኑ

“እስከማውቀው እና ካደረግኳቸው ቃለ መጠይቆች አብዛኛዎቹ ሕንዳውያን እንደ ቬርሞንት ወይም ሰሜናዊ ኒው ዮርክ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች አይቆዩም።ይልቁንም በተቻላቸው ፍጥነት ወደ ከተማዎች ይሄዳሉ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እዚያ ደርሰው እንደ ቤት ሠራተኛ እና የሬስቶራንት ሥራን የመሳሰሉ መደበኛ ያልሆኑ ሥራዎች ውስጥ ይገባሉ ብለዋል።

ሆኖም ነገሮች በቅርቡ ይበልጥ አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ።በጥር ወር ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ የአገሪቱን ድንበሮች የሚቆጣጠሩት አንጋፋው የኢሚግሬሽን ባለስልጣን ቶም ሆማን እንዳሉት በአካባቢው ያለው ሕገወጥ ስደት “ትልቅ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ” በመሆኑ ከካናዳ ጋር ያለው ሰሜናዊ ድንበር ቅድሚያ ይሰጠዋል።

ቀጥሎ ምን እንደሚሆን ግልጽ አይደለም። “ካናዳ ሰዎች ከድንበሯ ወደ አሜሪካ እንዳይሰደዱ ለመከላከል ተመሳሳይ ፖሊሲዎችን ስለማውጣቷ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።ይህ ከሆነ በድንበር ላይ የሚታሰሩ የሕንድ ዜጎች ቁጥር እየቀነሰ እንደሚሄድ መጠበቅ እንችላለን።” ሲሉ ፑሪ ተናግረዋል።

ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን፣በሺዎች የሚቆጠሩ ተስፋ የሰነቁ ሕንዳውያን በአሜሪካ የተሻለ ኑሮ እንዲያማትሩ የሚያደርጋቸውን ህልሞች የማጥፋት ዕድሉ ግን አነስተኛ ነው።