
ከ 6 ሰአት በፊት
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን ከዩክሬን ጦርነትና ሌሎችም የውጭ አገራት ጉዳዮች በነጠሉ ንግግሮች ነበር ለምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበረው።
በንግድ አጋሮች ላይ የክፍያ ገንዘብ ለመጨመርና የአገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ ቃል ሲገቡ ተደምጠዋል።
ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ወጣ ያሉ ሐሳቦችን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ እየተናገሩ ነው።
እንደ ቀልድ ካናዳ የአሜሪካ ግዛት ናት ከማለት ጀመሩ።
ከዚያም የፓናማ ካናልን ለመውሰድ ዛቱ። ራስ ገዝ የዴንማርክ ግዛት የሆነውን ግሪንላንድ መቆጣጠር እንደሚፈልጉ ተናገሩ።
ፓናማ ካናልም ሆነ ግሪንላንድ ለገበያ አልቀረቡም። አሜሪካ ሁለቱንም ግዛቶች ልትቆጣጠር አትችልም። ግን የትራምፕ ‘ቅድሚያ ለአሜሪካ’ (America First) ዕሳቤ ከአሜሪካ ግዛት ተሻግሮ አገራትን የሚገዳደር መሆኑን ይጠቁማል።
ከአሜሪካ የንግድና ብሔራዊ ደኅንነት አሻግረው እንደሚያልሙም ጠቋሚ ንግግሮች ናቸው።
ትራምፕ በአሪዞና የወግ አጥባቂዎች ውይይት ላይ ፓናማ የአሜሪካን መርከቦች “ከፍተኛ ገንዘብ እያስከፈለች ነው” ብለዋል።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አሜሪካ የፓናማ ካናልን ከገነባች በኋላ እአአ በ1970ዎቹ በተፈረመ ስምምነት ኃላፊነቱን ለአሜሪካ አስረክባለች።
ትራምፕ ግን “የገንዘብ ብዝበዛው” ካልቆመ አሜሪካ ፓናማ ካናልን እንደምትወስድ ተናግረዋል። እንዴት ይህ እንደሚሆን ግን አልገለጹም።
“ፓናማ ካናል በተሳሳተ እጅ መውደቅ የለበትም” ብለዋል። ይህን ያሉት ቻይናን አስመልክተው ነው። ቻይና በቦታው ፍላጎት አላት።
በላቲን አሜሪካ ተመራማሪው ዊል ፍሪማን “አሜሪካ ገለልተኛ በመሆን ብሔራዊ ጥቅሟን ታስጠብቃለች” ብለዋል።
ከአሜሪካ ቀጥሎ ፓናማ ካናልን የምትጠቀመው ቻይና ናት። በፓናማ ከፍተኛ ኢንቨስትመንትም አላት።
እአአ በ2017 ፓናማ ከታይዋን ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት አቋርጣለች። ታይዋን የቻይና ግዛት መሆኗንም ዕውቅና ሰጥታለች።
ፓናማ ካናል አሜሪካ በፓስፊክ ከምታደርገው ንግድ ባሻገር ከቻይና ጋር ወታደራዊ ግጭት ቢኖርም የአሜሪካን መርከቦች ለማስጠጋት እንደሚጠቅም ዊል ፍሪማን ያስረዳሉ።
- ዴንማርክ የትራምፕን ግሪላንድን “እቆጣጠራለሁ” ንግግር ተከትሎ የግዛቲቷን መከላከያ በጀት አሳደገች25 ታህሳስ 2024
- ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፀሐይ ለመጠጋት እየሞከረች ያለችው የናሳ መንኩራኩር25 ታህሳስ 2024
- በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባት የነበረች የሩስያ መርከብ ሞተሯ ላይ ካጋጠመ ፍንዳታ በኋላ ሰጠመች25 ታህሳስ 2024
ትራምፕ የአሜሪካ የንግድ አጋሮች አሜሪካን እየጎዷት እንደሆነ ይናገራሉ። በዋናነት በቻይና ላይና በሌሎችም የውጭ ምርቶች ላይ ቀረጥ ለመጨመርም ዝተዋል።
በመርከብ ለማጓጓዝ የሚወጣውን ወጪም በተመለከተ ትራምፕ ሲያማርሩ ይደመጣሉ።
ዊል ፍሪማን እንደሚሉት፣ ትራምፕ ያሉትን ማስፈጸማቸው ለወደፊት የሚታይ ይሆናል።
“በዚህ ዛቻ ምክንያት የፓናማ ካናል ክፍያ ለአሜሪካ መርከቦች የሚቀንስ ከሆነ እናያለን” ይላሉ።
የፓናማ ፕሬዝዳንት ሆሴ ራውል ሙሊኖ ባወጡት መግለጫ ፓናማ ካናልና አካባቢው የፓናማ ንብረት ሆኖ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ትራምፕ “ግሪንላንድን መቆጣጠር ለአሜሪካ እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል።
ለዚህም ምክንያት ያሉት ብሔራዊ ደኅንነትና ዓለም አቀፋዊ ነጻነትን ነው።
አሜሪካ በግሪን ላንድ ፒቱፊክ ስፔስ ቤዝ የተባለ ወታደራዊ መቀመጫ አላት።
አካባቢው ነዳጅን ጨምሮ በበርካታ የተፈጥሮ ሃብት የበለጸገ ነው።
ኃያላን አገራት በአርክቲክ ሰርክል ተደራሽነታቸውን ለማስፋት እሽቅድድም ላይ ይገኛሉ።
ሩሲያ አካባቢውን ስትራቴጂያዊ አድርጋ ትወስደዋለች።
እአአ በ2019 ትራምፕ ግሪንላንድን ለመግዛት ሐሳብ አቅርበው ነበር። ግን ዕውን አልሆነም።
የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙቲ ቢ ኤድጅ የትራምፕን አስተያየት በተመለለተ “ለገበያ አልቀረብንም፣ አንቀርብምም” ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።
ትራምፕ ግን አቋማቸውን መግለጽ ቀጥለዋል።
የአሜሪካ ሰንደቅ አላማ በፓናማ ካናል መሀል ተተክሎ የሚያሳይ ምሥል በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ለጥፈዋል።
ልጃቸው ኤሪክ ትራምፕ ደግሞ አሜሪካ የአማዞን የገበያ ቅርጫት ውስጥ ፓናማ ካናል፣ ካናዳ እና ግሪንላንድን ስትጨምር የሚያሳይ ምሥል በኤክስ ገጹ አጋርቷል።
ትራምፕ አሜሪካን ኃያል ስለማድረግ ማውራታቸው ከአንድም ሁለቴ ምርጫ እንዲያሸንፉ ረድቷቸዋል።
ሜክሲኮ ከአሜሪካ ጋር የምትጋራውን ድንበር ጥበቃውን ከፍ እንድታደርግ ‘ወታደሮች’ ለማሰማራት ቃል የገቡት መጀመሪያ ሲመረጡ ነበር።
በሁለተኛው ምርጫቸውም ተመሳሳይ ቃል እየገቡ ነው።
ዴንማርክ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር አብራ እንደምትሠራ ብትገልጽም፣ ለግሪንላንድ መከላከያ ተጨማሪ በጀት እንደምትመድብ አስታውቃለች።