ሃን በቅርቡ ነው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት

ከ 5 ሰአት በፊት

የደቡብ ኮሪያ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር እና ተጠባባቂ መሪ ሃን ዳክ-ሱን እንዲከሰሱ ጥያቄ አቀረቡ።

ፓርላማው ወታደራዊ ህግ በመደንገግ ከስልጣን የተነሱትን የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮልን ለመክሰስ ድምጽ ከሰጠ ሁለት ሳምንታት እንኳን ሳይሞላ ነው የአሁኑ ክስ የቀረበው።

ጥያቄው የቀረበው ሃን በዋነኛው ተቃዋሚ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ዲፒ) የተጠቆሙት የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ዳኞችን ለመሾም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው።

“ሃን እራሱን ያቀረበው የአማጺ መሪ አድርጎ እንጂ እንደ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አይደለም” ሲሉ የዲፒ ፓርቲው ፓርክ ቻን ዴይ ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።

ሃን ከጥቂት ሳምንታት በፊት የወጣውን የዩን ወታደራዊ ህግ የማስፈን ሙከራን ደግፈዋል ሲል ፓርቲው ከሷል። ህጉን ባለመቃወማቸው ሃን ቀደም ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል።

ሃን ለአጭር ጊዜ የቆየውን ወታደራዊ ህግ ላይ ልዩ ምርመራ እንዲደረግ ፓርቲው ያቀረበውን ሃሳብ ጨምሮ በተቃዋሚ ፓርቲ የቀረቡ በርካታ ሐሳቦችን ውድቅ አድርገዋል ተብሏል።

የቀረበው ክስ ላይ በሚቀጥሉት 24 እስከ 72 ሰዓታት ውስጥ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ከ300 የፓርላማ አባላት 151ቱ ከደገፉት ተግባራዊ ይደረጋል።

ተቃዋሚው ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከአገሪቱ 300 የፓርላማ መቀመጫዎች 170ቱን ይዟል። ሁሉም የተቃዋሚው ፓርቲዎች ደግሞ 192 መቀመጫዎችን ይዘዋል።

ሃን የአገሪቱ ተጠባቂ ፕሬዝዳንት በሚሆኑበት ወቅት በመንገዳቸው ላይ እንደማይቆሙ እና ህጎችን ያለምንም ተቃውሞ እንዲፀድቁ ይፈቅዳሉ የሚል ተስፋን ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ሰንቀው ነበር።

ይልቁንም በሃሳበቸው ጸንተው የፖለቲካ ውዝግቡን አባብሰውታል።

ሃን ማክሰኞ ዕለት የምክር ቤት ስብሰባ ቢያደርጉም ልዩ ኮሚቴ በወታደራዊ ህጉ እና በቀዳማዊት እመቤት ኪም ኪዮን ሂ ላይ የሙስና ውንጀላዎችን እንዲመረምር ተቃዋሚዎች ያቀረቡትን ሃሳቦች ሳይመለከቱ አጠናቀዋል።

ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች መግባባት ላይ እንዲደርሱ ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት በሚል አጀንዳው ላይ አለመወያየታቸውን ገልጸዋል።

የዴሞክራቲክ ፓርቲው ፓርክ ቻን-ዴይ ግን “ጊዜን በመግዛት እና ችግሩን ለማራዘም እየተደረገ ነው” ሲሉ ነቅፈውታል።

“በታሪክ ውስጥ አሳፋሪ ስራ እንደሰራ፣ እንደ የአመጽ መሪ እና የዩን ሱክ ዮል አሻንጉሊት ወይስ በታማኝነት የህዝብ አገልጋይ መሆኑን የሚለውን አማራጭ የመወሰን የጠቅላይ ሚኒስትር ሃን ዳክ ሱ ውሳኔ ነው” ሲሉ ፓርክ በቴሌቪዥን በተላለፈው የፓርቲው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

ሃን ሐሙስ ዕለት በተቃዋሚዎች የሚመራው ብሔራዊ ምክር ቤት ለህገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤት ያቀረባቸውን ሦስቱን ዳኞች ተቃዋሚ ፓርቲዎች መግባባት ላይ ካልደረሱ አልሾምም ብለዋል።

“ሃን ዳክ ሱ ህገ መንግስቱን ለመከላከል ብቃትምሆነ ፍላጎት እንደሌለው ግልጽ ሆኗል” በማለት ተቃዋሚዎች የክስ ጥያቄውን “በፍጥነት” እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

ሃን አባል የሆኑበት ገዥው ፒፕል ፓወር ፓርቲ የተቃዋሚዎች ዛቻ በሃን “ህጋዊ ስልጣን” ላይ ጣልቃ ገብቷል ብሏል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን በበኩላቸው ዛቻውን “እጅግ በጣም የሚያሳዝን” ሲሉ ተችተዋል።

ዮን በዚህ ወር መጀመሪያ ከስልጣን ከተነሱ በኋላ ነበር ሃን ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት። ህግ አውጭዎች ሃን እንዲከሰሱ ድምጽ ከሰጡ የፋይናንስ ሚኒስትር ቾይ ሳንግ-ሞክ ቦታውን የሚይዙ ይሆናል።

በአገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት ባለችበት ወቅት የመጣው አዲሱ ጉዳይ የሴኡል ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዩን ከስልጣን በቋሚነት መታገድ አለባቸው በሚለው ላይ እየተወያየ ባለበት ወቅት ነው።

ፍርድ ቤቱ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለመጀመሪያ ጊዜ በህዝብ ፊት ችሎቱ ይሰየማል ተብሎ ይጠበቃል።

በችሎቱ ላይ ዩን ስለመገኘታቸው ግልጽ ባይሆንም ተቃዋሚዎች ግን በፍርድ ቤት ችሎት ወቅት ዮን በቋሚነት ስልጣን ከመያዝ እንዲታገዱ መጠየቃቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

ዩን አገሪቱን በወታደራዊ ህግ ስር ለማስተዳደር ያልተሳካ ሙከራ ፈጽመዋል በሚል ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።

በአካል እንዲቀርቡ የቀረበላቸውን ተደጋጋሚ ጥሪ ለመቀበል ፍቃደኛ ያልሆኑ ሲሆን በዚሁ አቋማቸው የሚቀጥሉ ከሆነ መርማሪዎች የእስር ማዘዣ ሊያወጡ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ኪም ዮንግ-ህዩን፣ የቀድሞ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሊ ሳንግሚን እና የጦር ኃይል አዛዥ ፓርክ አን-ሱን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ባለስልጣናትም ምርመራ ተከፍቶባቸዋል።