የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች

ከ 5 ሰአት በፊት

የዩክሬን ጦር ለሩሲያ ወግኖ ሲዋጋ የነበረ የቆሰለ ወታደር ለመጀመሪያ ጊዜ መማረኩን የደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት አስታወቀ።

ወታደሩ ሰሜን ኮሪያ የሩሲያን ጦር ለመደገፍ ወታደሯቿን አሰማርታለች ከተባለበት ታህሳስ ወር ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተማረከ ነው ተብሏል።

የቆሰለውን ወታደር የሚያሳይ ፎቶ በቴሌግራም ከተጋራ በኋላ ነው የደቡብ ኮሪያ ደህንንት ማረጋገጫውን የሰጠው።

ሰሜን ኮሪያ ሩሲያን ለማገዝ ከ10 ሺህ በላይ ወታደሮች ማሰማራቷን የዩክሬን እና የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ገልጸዋል። ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ወታደሮቹ መሰማራቸውን አላረጋገጡም እንዲሁም አልካዱም። ነገር ግን መንግሥታዊ የዜና ወኪል ኬሲኤንኤ በቅርቡ ባሰራጨው የሰሜን ኮሪያ መግለጫ አገሪቱ ከሩሲያ ጋር ያላት አጋርነት “የአሜሪካ እና የምዕራቡ ዓለም ያሰቡትን ተጽእኖ እያደናቀፈው ነው” ብሏል።

ከ3 ሺህ በላይ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በከርስክ ግዛት ሲዋጉ እንደሞቱ ወይም እንደቆሰሉ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሰኞ ዕለት ገልጸው ነበር።

በሩሲያ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል ያለው ትብብር በአጠቃላይ በኮሪያ ዙሪያ ያለውን “ያለመረጋጋት አደጋ” ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

በቅርቡ በዩክሬን ጦርነት ለሩሲያ ወግነው ከሚዋጉት መካከል ቢያንስ 100 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መገደላቸውን የደቡብ ኮሪያ የፓርላማ አባል ገልጸው ነበር።

ፓርላማው በአገሪቱ ብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ማብራሪያ ከተሰጠው በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ሊ ሱንግ ኳን ተጨማሪ 1 ሺህ ወታደሮች ቆስለዋል ብለዋል።

ከተገደሉት መካከል ከፍተኛ መኮንኖች እንደሚገኙበት ተናግረው የወታደሮቹ ግድያ ስለ አካባቢው በቂ ግንዛቤ አለመኖር እንዲሁም ከሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ጋር በተያያዘ ሊገለጽ ይችላል ብለዋል።

በጦርነቱ የተገደሉ ሰሜን ኮሪያውያን ወታደሮች ሪፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ በሆነበት በዚህ ወቅት ነው የተናገሩት።

ከሳምንት ገደማ በፊት የአሜሪካ የፔንታጎን ቃል አቀባይ ትክክለኛ ቁጥር ሳይገልጹ ሰሜን ኮሪያውያን ወታደሮች ተገድለዋል ብለው ነበር። ከአንድ ቀን በኋላ ስማቸው ያልተጠቀሰ አሜሪካዊ ባለስልጣን “በርካታ መቶዎች” ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል ብለዋል።

ቢቢሲ ተገድለዋል የተባሉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ሪፖርት በገለልተኛነት አላረጋገጠም።

አንዳቸውም ከዚህ በፊት የውጊያ ልምድ እንደሌላቸው የሚታሰብ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች የመጀመሪያዎቹን ሳምንታት በሩሲያ በስልጠና ላይ እንዲሁም በድጋፍ ሰጪነት ተሰማርተው እንደነበር ይታመናል።

ዩክሬን በሩሲያ የከርስክ ግዛት ድንገተኛ ወረራ በመፈጸም የተቆጣጠረቻቸውን ስፍራዎች ላይ ወታደሮቹ ተገድለው ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል።