የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አርማ

ከ 1 ሰአት በፊት

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች “የፈጸሟቸውን ከባድ የሕግ ጥሰቶች በዝርዝር ባላስቀመጠ ደብዳቤ መታገዳቸው” አሳሳቢ ሆኖ እንዳገኘው አስታወቀ።

መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ይህን ያስታወቀው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የተጣለውን እገዳ በተመለከተ አርብ ታኅሳስ 19/2017 ባወጣው መግለጫ ነው።

ኢሰመኮ በመግለጫው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በሕዳር ወር ሶስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ እገዳ ማስተላለፉን ተከትሎ አቤቱታዎች እንደደረሱት ጠቁሟል።

ተቋሙ በደረሰው መረጃ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ “ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ መሥራት ሲገባቸው ከዓላማቸው ውጭ በመንቀሳቀስ የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ ተግባራት ላይ መሰማራታቸው” የሚል የእገዳ ደብዳቤ እንደደረሳቸው መረዳቱን በመግለጫው አስታውቋል።

ይህን ጉዳይ በመከታተል ላይ እያለ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሌሎች ሁለት የሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች መታገዳቸውን ያስታወሰው ኢሰመኮ፤ “ተቋሟቱ የፈጸሟቸውን ከባድ የሕግ ጥሰቶች በዝርዝር ባላስቀመጠ ደብዳቤ መታገዳቸው አሳሳቢ ሆኖ አግኝቶታል” ብሏል።

ኢሰመኮ በመግለጫው ተደጋጋሚ እገዳዎች፤ “የሲቪክ ምኅዳሩን በማጥበብ በማኅበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር” ባለስልጣኑ የድርጅቶቹን እንቅስቃሴዎች አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ የምርምራ ስራዎቹን “በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች” ጥሪ አቅርቧል።

ካለፈው ህዳር ወር ወዲህ አምስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በመንግሥት ታግደዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በቀናት ልዩነት ውስጥ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች እንዲሁም ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ በተባሉት ድርጅቶች ነበሩ።

በእነዚህ ድርጅቶች ላይ የተጣለው እገዳ በታኅሳስ ወር መጀመሪያ የተነሳ ሲሆን ከአምስት ቀናት በኋላ ግን፤ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች በድጋሜ ታግደዋል።

ሁለቱ ድርጅቶች በድጋሜ ከታገዱ አንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ታግደዋል።

ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሰረት በ2013 ዓ.ም. የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ትኩረቱን የሰብዓዊ መብቶች ላይ ያደረገ አገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ነው።

ሌላኛው በተመሳሳይ ጊዜ የታገደው ኢሰመጉ፤ ባለፉት 33 ዓመታት “በሃገሪቱ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን እና የህግ የበላይነት እንዲከበር ከፍተኛ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ አንጋፋ ድርጅት” መሆኑን ይገልጻል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፤ “የሰብዓዊ መብት የሚባል አዋጅ ተቋም አሠራርን መፈተሽ ያስፈልጋል። እኛ ደመወዝ የማንከፍለው ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለእናንተ መተው ነው” ብለው ነበር።

ዐቢይ አክለውም “ሰብዓዊ መብት ደስ የሚል ቋንቋ ነው። ግን ይሄ ቋንቋ ከዋናው የትርጉም ግንዱ ወጥቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ እየሆነ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትን ያስደነገጠ ነበር።

በኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚመሩ ግለሰቦች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር “አሳሳቢ” እና “አስደንጋጭ” መሆኑን ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።