
26 ታህሳስ 2024
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሓኖም ገብረ እየሱስ እስራኤል ጥቃት እየፈጸመች በነበረችበት በየመኑ ሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እንደነበሩ ገለጹ።በጥቃቱ አንድ የአውሮፕላኑ ሰራተኛ ተጎድተዋል።
“ከሁለት ሰዓታት በፊት፣ ከሰንዓ ለመብረር ወደ አውሮፕላኑ ልንሳፈር ስንል አየር ማረፊያው የአየር ጥቃት ተፈጸመበት” ብለዋል።
“ልንሳፈርበት የነበረው አውሮፕላን ሰራተኞች መካከል አንዱ ቆስሏል። ቢያንስ ሁለት ሰዎች በአውሮፕላን ማረፊያው መገደላቸው ሪፖርት ተደርጓል” ሲሉ ተናግረዋል።
“እኛ ካለንበት ጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ የነበረ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ እንዲሁም የማረፊያ ሳሎን እና ማኮብኮቢያው [በጥቃቱ] ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ነው ዶክተር ቴድሮስ የገለጹት
ቴዎድሮስ አድሐኖም ገብረእየሱስ እና ቡድናቸው አገሪቷን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት “በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ የደረሰው ጉዳት እስኪጠገን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ” ገልጸዋል።

- ፕሬዝደንት ኢሳያስ “የሶማሊያን ሰላም ማስጠበቅ ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ ነው” አሉ26 ታህሳስ 2024
- በእስራኤል ጥቃት አንድ የፍልስጤም ቴሌቪዥን ጣቢያ አምስት ጋዜጠኞች ተገደሉ26 ታህሳስ 2024
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስሥልጣን ታገደከ 4 ሰአት በፊት
አክለውም “እኔም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረቦቼ ደህና ነን” ሲሉ በጥቃቱ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው አረጋግጠዋል።
“በጥቃቱ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እንገልጻለን ” ሲሉ የኃዘን መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።
ዶክተር ቴድሮስ በእስር ላይ ያሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞች እንዲፈቱ የመደራደር እና በየመን ያለውን የጤና ሰብዓዊ ሁኔታ የገመገመው ተልዕኳቸው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ አውሮፕላኑ ሊሳፈሩ ሲል ይህ ጥቃት ማጋጠሙን ገልጸዋል።
በሰኔ ወር የመንግሥታቱ ድርጅት 13 ሰራተኞች በሁቲ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አረጋግጧል።
ሰራተኞቹ የተቀናጀ እርምጃ በሚመስል መልኩ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ነው የተወሰዱት።
በጥቃቱ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን በየመን ሁቲዎች የሚተዳደረው አልማሲራህ የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ከተገደሉት በተጨማሪ 11 ሰዎች ቆስለዋል። ሁለቱ የተገደሉት በሰንዓ አየር ማረፊያ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ኢሳ በተሰኘው ወደብ ነው።
እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት አለም አቀፉን የሰንዓ አየር ማረፊያ፣ ሁለት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን እና ወደቦችን መምታቷን አስታውቃለች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው የሁቲ መሰረተ ልማቶችን ታወድማለች ሲሉ ቅዳሜ ዕለት ተናግረው ነበር።
ሁቲዎች ቅዳሜ በቴልአቪቭ የፈጸሙት ጥቃትን ጨምሮ በርካታ ሚሳኤሎች ማስወንጨፋቸው ይታወሳል።
የሁቲ ቃል አቀባይ መሐመድ አብዱልሰላም ጥቃቱን “በየመን ህዝብ ላይ የተፈጸመ የጽዮናዊ የሰብዓዊነት ወንጀል” ሲሉ መግለጻቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።