
ከ 3 ሰአት በፊት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮን (አትሚስ) የሚተካው ሌላኛው ተልዕኮ ላይ ድምጽ ለመስጠት ሊሰበሰብ ነው።
በምክር ቤቱ ጊዜያዊ የአሰራር ደንብ መሰረት በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአትሚስ ተልዕኮ ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ እስከ ፈረንጆቹ ታህሳስ 31፣ 2024 ድረስ ተራዝሞ ነበር።
በዩናይትድ ኪንግደም የተዘጋጀው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ፤ የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የፀጥታው ምክር ቤት አትሚስን በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (AUSSOM) ለመተካት ያሳለፈውን ውሳኔ የሚደግፍ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት አባላት በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ለ12 ወራት እንዲወስዱ ስልጣን ይሰጣል።
ረቂቁ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት እስከ መጪው የአውሮፓውያኑ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 1,040 የፖሊስ አባላትን ጨምሮ እስከ 12 ሺህ ገደማ መለዮ ለባሽ የጸጥታ አካላት እንዲያሰማሩ ፈቅዷል።
በተጨማሪም እስከዚህ ቀን ድረስ ሁሉንም የአፍሪካ ህብረት ወታደሮች ከአትሚስ ወደ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ማቀናጀትን እንዲጠናቀቅ ያትታል።
የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት ከተለያዩ አገራት የተወጣጣ ሰላም አስከባሪ ኃይል ለስድስት ወራት በሶማሊያ እንዲቆይ ማሰማራቱ ይታወቃል።
- ሠራዊቷ ከሶማሊያው አዲሱ የሰላም ተልዕኮ ውጪ ነው የተባለችው ኢትዮጵያ አልሻባብን በማዳከም እንደምትቀጥልበት አስታወቀች14 ህዳር 2024
- ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ግዛቴ ጥሰው ገብተዋል ስትል ለፀጥታው ምክር ቤት ከሰሰች25 ሰኔ 2024
- ኢትዮጵያ ወታደሮቿ ወደ ሶማሊያ ግዛት ጥሰው ገብተዋል መባላቸውን “መሠረተ ቢስ” ስትል አጣጣለች27 ሰኔ 2024
ነገር ግን ለስድስት ወራት የተሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል ሁለት አስርት ኣመታት ለሚጠጋ ጊዜ በሶማሊያ ቆይቷል።
በሶማሊያ የተሰማራው ይህ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ መጠሪያውን ከአሚሶም ወደ አትሚስ የቀየረው ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር። ይህ ተልዕኮ ከቀናት በኋላ ቆይታው ያበቃል።
የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮቿን እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል አሰማርታ ኢትዮጵያ ሰራዊቷን አሰማርታ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር 3 ሺህ ያህል ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ስምምነት አዲሱ ተልዕኮ ከሚወሰንበት፣ ከሰኔ መጨረሻ በፊት ካልሰረዘች በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ስር እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት የሰፈሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንደሚወጡ የአገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሑሴን አሊ ከዚህ ቀደም ገልጸው ነበር።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ይህን ተከትሎ የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ሠራዊት ከአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ውጪ መሆኑን በይፋ አስታውቀው ነበር።
ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ሶማሊያ ውስጥ ሰላም ሲያስከብር የቆየው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከግዛቱ እንዲወጣ እንደሚፈልግ የሶማሊያ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።
ከዚህ ሁሉ መካረር በኋላ ግን የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መሪዎች አለመግባባታቸውን በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያውፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ፊርማቸውን ባኖሩበት የአንካራ ስምምነት መሰረት፤ “ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ስምምነቱ “የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ” ሲል ያትታል።