
ከ 5 ሰአት በፊት
በአውሮፓውያኑ 2019 አንዲት የ13 ዓመት ታዳጊ ስኮትላንድ ውስጥ የደወለችው የስልክ ቁጥር የአንድ ወንጀለኛ መጨረሻ ሆኗል። ግለሰቡ በማኅበራዊ ሚድያ እያነፈነፈ ሕፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚያደርስ ነፍሰ ገዳይ ነው።
የሰሜን አየርላንዱ አሌክሳንደር ማካርትኒ ታዳጊ ሴት በመምሰል ነው ልጆችን የሚቀርበው። በዓለም ዙሪያ ያሉ ሕፃናት ሲያታልል እና ሲያጭበርበር ኖሯል። ያገኘውን ፎቶ ደግሞ ለሌሎች ወንጀለኞች ያጋራል።
አንዳንዶቹ ሕፃናት ገና አራት ዓመታቸው ነው። የተወሰኑ ሕፃናት ፖሊስ በራቸውን እስኪያንኳኳ ድረስ የደረሰባቸውን ጥቃት ለማንም አልተናገሩም።
ማካርትኒ የቀረቡበትን 185 ክሶች አምኗል። ብዝበዛ ያደረሰባት አንዲት የ12 ዓመት ታዳጊ ራሷን ማጥፋቷን ተከትሎ የግድያ ክስም ቀርቦበታል።
ወንጀለኛው የ20 ዓመታት እስር ተፈርዶበታል።
ፖሊስ ምን አደረገ?
ጥቆማ የደረሰው የሰሜን አየርላንድ ፖሊስ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2019 ነው ወዲያውኑ ወደ ምርመራ የገባው።
ፖሊስ የአሌክሳንደርን መኖሪያ አድራሻ ካጣራ በኋላ በቁጥጥር ሥር አውሎት ምርመራ ከፈተበት። ቤቱ ውስጥ የነበሩ 64 ስልኮች እና ሌሎች መሣሪያዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በእነዚህ ስልክ እና ላፕቶፖች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የሕፃናት ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ቪድዮዎች እና ፎቶዎች ተገኝተዋል። ሕፃናቱን በማስፈራራ ወሲባዊ ድርጊት እንዲፈፅሙ ሲያደርግ ይታያል።
ግለሰቡ በማኅበራዊ ሚድያ የተለያዩ ሐሰተኛ ገፆች አሉት። በተለይ ደግሞ ስናፕቻት በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ነው ሕፃናትን የሚያጠምደው።
የሰሜን አየርላንድ ፖሊስ እንደሚለው ሰውዬው “በጣም በሰፊው ነበር ወንጀል ሲፈፅም” የቆየው።
ሰለባዎቹን የሚቀርበው በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ ያለ ታዳጊ በመምሰል ነው። ቀጥሎ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ፎቶዎች እንዲልኩለት ያደርጋል፤ አሊያም ወሲባዊ እንቅስቃሴ እንዲፈፅሙ ያበረታታል። ይህን የሚያደርገው በሞባይል ስልክ እና ዌብካም በተባለ ካሜራ እየቀረጸ ነው።
መርማሪዎች እንደሚሉት ማካርትኒ ተመሳሳይ መንገድ በመጠቀም በርካቶችን አጭበርብሯል። “የያዛቸውን ፎቶዎች በይነ መረብ ላይ እንደሚለቅ በማስፈራራት ተጨማሪ ፎቶዎች እንዲልኩለት ያደርጋል። ፍርሃት ላይ ያሉ ሕፃናትን ይበዘብዛል።”
አንዲት የ12 ዓመት ታዳጊን በዘጠኝ ደቂቃዎች ውስጥ አጥምዶ፣ ወሲባዊ ጥቃት ከማድረሱም በላይ ፎቶዎቿን ሊበትን እንደሚችል ሲያስፈራራት ነበር።
- በነቀምቴ ከተማ ሁለት ታዳጊ ሴቶችን በቡድን የደፈሩ ወጣቶች እየተፈለጉ መሆኑን ፖሊስ ገለጸ29 ጥቅምት 2024
- ለዘጠኝ ዓመታት በሐሰተኛ ማንነት በኢንተርኔት የተታለለችው አፍቃሪ23 ጥቅምት 2024
- የታዳጊዎች አደገኛ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው – ጥናት26 መስከረም 2024

ግለሰቡ ከዩናይትድ ኪንግደም ባለፈ በሌሎች ክፍለ ዓለማት ያሉ ታዳጊዎችን ሲበዘብዝ ነው የከረመው።
የሰሜን አየርላንድ ፖሊስ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ከሌሎች ሀገራት ደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር በአሜሪካ፣ ኒው ዚላንድ እና በሌሎች 28 ሀገራት ያሉ ሰለባዎችን ማጣራት ችሏል።
ሰለባዎቹ ሊታወቁ የቻሉት በማካርትኒ ስልኮች እና ኮምፒውተሮች ውስጥ በተገኙ መረጃዎች መሠረት ነው።
ፖሊስ እንደሚለው ግለሰቡ “የሕፃናት ወሲባዊ ብዝበዛ አድራሾች መረብ ዘርግቷል” የሰለባዎቹን “የልጅነት ሕልም” ነጥቋል።
በሐሰተኛ ማንነት የሚያጭበረብረው
በእንግሊዝኛው ‘ካትፊሺንግ’ የሚባለው ድርጊት ሐሰተኛ ማንነት በመያዝ በበይነ መረብ ሰዎችን ማታለል ማለት ነው።
ፖሊስ ምርመራ አጠናቆ ግለሰቡን ፍርድ ቤት ሊቀርብ ሲሰናዳ አንድ አዲስ ዜና ተሰማ። የሰውዬው ሰለባ ከሆኑ ታዳጊዎች መካከል ዩናይትድ ስቴትስ ዌስት ቨርጂኒያ ነዋሪ የሆነች አንዲት ታዳጊ ራሷን ማጥፋቷ ተዘገበ።
የ12 ዓመቷ ታዳጊ ሲማሮን ቶማስ በአውሮፓውያኑ 2018 ማካርትኒ ብዝበዛ ሲያደርስባት ነው በሽጉጥ ራሷን ያጠፋችው።
ማካርትኒ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሰሰ።
ጥቃት አድራሽ እና ሰለባ በአካል ሳይገናኙ አንድ ግለሰብ ለነፍስ መጥፋት ኃላፊነት አለበት ተብሎ ሲከሰስ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ግለሰቡ 200 ያክል ክሶች ቀርበውበታል። የጥቃቱ ሰለባዎች 70 ገደማ ይሆናሉ። በሰሜን አየርላንድ ታሪክ ይህ ትልቁ የወንጀል መዝገብ ነው።

ሰውዬው ማነው?
ሰሜን አየርላንድ ኔውሪ የተባለች ከተማ አቅራቢያ ተወልዶ ያደገው አሌክሳንደር ማካርትኒ በአውሮፓውያኑ 2019 ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርብ የ21 ዓመት ወጣት ነበር።
ያለፉትን አምስት ዓመታት እስር ቤት ነው ያሳለፈው። ወንጀሉን ፈፅመሀል ተብሎ ሲፈርድበት በለሆሳስ ተቀብያለሁ ከማለት ውጪ የተናገረው ነገር የለም።
ኔውሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማረው ወጣቱ ጥቃት አድራሻ በበይነ መረብ ‘ጌም’ ከመጫወት ያለፈ ሕይወት የለውም።
አንድ ውስጥ አዋቂ “ከቤት የማይወጣ እና ሰዎች ሲበዙ ግራ የሚጋባ ነው። ከጓደኞቹ ውጭ ማንንም አያናግርም” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ለቤተሰቦቹ እና ለጓደኞቹ የተፈረደበት ወንጀል እጅግ አሰቃቂ ሆኖ ተገኝቷል።