
ከ 5 ሰአት በፊት
የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ በታህሳስ 16/ 2017 ዓ.ም. ለተከሰከሰው እና 38 ሰዎች ለሞቱበት የአዘርባጃን አየር መንገድ አውሮፕላን “አሜሪካ ያሏት ቅድመ መረጃዎች’ ሩሲያ ተጠያቂ ልትሆን እንደምትችል ያሳያል አሉ።
ሚስተር ኪርቢ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራርያ ባይሰጡም አሜሪካ በአደጋው ላይ ለሚደረገው ምርመራ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኝነቷን መግለጿን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ የካስፒያን ባህርን አቋርጦ ወደ ካዛኪስታን ከመብረሩ በፊት በቼችኒያ ለማረፍ ሲሞክር ከሩሲያ አየር መከላከያ ኃይል ተተኩሶ እንደተመታ ይታመናል።
በጉዳዩ ላይ ክሬምሊን አስተያየት ከመስጠት ብትቆጠብም፣ የሩሲያ የሲቪል አቪዬሽን ኤጀንሲ ግን የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች በአካባቢው ላይ በሚፈጽሙት ጥቃት በቼችኒያ ያለው ሁኔታ “በጣም የተወሳሰበ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ኪርቢ እንደተናገሩት አሜሪካ ያየቻቸው የአደጋው ቅድመ ምልክቶች በስፋት ከተሰራጩት የተከሰከሰው አውሮፕላን ምስሎች የዘለለ ነው ሲል ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።
በአዘርባጃን የሚገኙ የአቪዬሽን ባለሙያዎች እና ሌሎች የአውሮፕላኑ የጂፒኤስ ስርዓቶች በኤሌክትሮኒክ መሳርያ ግንኙታቸው እንዲቋረጥ መደረጉን እና በሩሲያ የአየር መከላከያ በተተኮሰ ሚሳኤል ጉዳት እንደደረሰባቸው ያምናሉ።
አዘርባጃን ሩሲያን በይፋ ባትከስም፣ የአገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር ግን አውሮፕላኑ ለማረፍ ሲሞክር “በውጭ ጣልቃ ገብነት” ከውስጥም ከውጪም ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።
ራሻድ ናቢዬቭ “ሁሉም [የተረፉት] ያለ ምንም ልዩነት አውሮፕላኑ በግሮዝኒ ሰማይ ላይ በነበረበት ጊዜ ሦስት የፍንዳታ ድምፅ እንደሰሙ ተናግረዋል።”
ናቢዬቭ እንዳሉት የምርመራ ባለሙያዎቹ አሁን “ምን አይነት መሳሪያ ወይም ምን ዓይነት ሮኬት ጥቅም ላይ እንደዋለ” ይመረምራሉ።
- ሶማሊያ በቀይ ባህር ዳርቻ የባህር በር ለኢትዮጵያ ሰጥታለች መባሉን አስተባበለች27 ታህሳስ 2024
- በዘውዲቱ ሆስፒታል አንዲት እናት 6 ኪሎግራም የሚመዝን ህጻን ተገላገለች27 ታህሳስ 2024
- ሰሞኑን በዩኒቨርስቲዎች የተፈጠረው “ተቃውሞ” መነሻው ምንድን ነው?27 ታህሳስ 2024
ይኹን እንጂ የመንግሥት ደጋፊ የሆኑት የፓርላማ አባል ራሲም ሙሳቤኮቭ “አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በሩሲያ ግዛት በግሮዝኒ ሰማይ ላይ ሳለ ነው፤ ይህንን መካድ የማይቻል ነው” ይላሉ።
ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት አውሮፕላኑ ጉዳት እንደደረሰበት እና አብራሪው በግሮዝኒ በድንገተኛ እንዲያርፍ ጠይቋል። በአቅራቢያው ወደሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች ከመመራት ይልቅ ጂፒኤስ ሳይኖረው በካስፒያን ባህር በኩል “ሩቅ እንደተላከ” ተናግረዋል።
ከአደጋው የተረፈችው የበረራ አስተናጋጇ ዙልፉካር አሳዶቭ አውሮፕላኑ በቼቺኒያ ሰማይ ላይ “በሆነ የውጭ ጥቃት” መመታቱን ገልጻለች።
“ያ በውስጥ መደናገጥ ፈጠረ። እነሱን ለማረጋጋት፣ እንዲቀመጡ ለማድረግ ሞክረን ነበር። በዚያን ጊዜ ሌላ ጥቃት ደረሰብን፣ እናም ክንዴ ተጎዳ።”
የኢምብራየር 190 አውሮፕላኑ አብራሪዎች በአደጋው ሕይወታቸው ቢያልፍም በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት መካከል 29ኙን በማዳናቸው ሙገሳ ተችሯቸዋል።
የአዘርባጃን አየር መንገድ አውሮፕላን በሩሲያ አየር መከላከያ መመታቱን የሚገልጹ ዘገባዎች እየበረከቱ ቢመጡም ክሬምሊን አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነችም።
ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “በዚህ የአቪዬሽን ክስተት ላይ ምርመራ በመካሄድ ላይ በመሆኑ ድምዳሜ ላይ እስኪደረስ ድረስ ምንም አይነት የራሳችንን ግምገማ ለመስጠት ኃላፊነት አለብን ብለን አናምንም” ብለዋል።
የካዛኪስታን ባለስልጣናት የተጎዱትን ሕክምና እንዲያገኙ እያደረጉ እና በተከሰከሰው አውሮፕላን ላይ የሚደረገውን ምርመራ ከአዘርባጃን ጋር በቅርበት እየሰሩ ነው።
ከባኩ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ሩሲያ እና ካዛኪስታን በሩሲያ የበላይነት ከተያዘው ቀጠናዊ ድርጅት ሲአይ ኤስ የተዋቀረ ኮሚቴ አደጋውን እንዲመረምር ሐሳብ አቅርበዋል። ነገርግን አዘርባጃን በምትኩ ዓለም አቀፍ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቃለች።