በደም የተጨማለቀ እጅ የተቃውሞው ምልክት ሆኗል

ከ 5 ሰአት በፊት

በየዕለቱ ልክ ከረፋዱ 5 ሰዓት ከ52 ደቂቃ ላይ በሰርቢያ የሚገኙ መንገዶች ለ15 ደቂቃዎች ዝግ ይደረጋሉ። መኪኖች ይቆማሉ፤ ህዝቡ ጸጥ ይላል።

ይህም በህዳር ወር በሰርቢያ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ኖቪ ሳድ በባቡር ጣቢያ ላይ ጣሪያው ወድቆ ህይወት መቅጠፉን ለማሰብ የሚደረግ ነው።

ነዋሪዎች በየ ፍትህ እንዲሰጥ ይጠይቃሉ።

የ15 ደቂቃው ተቃውሞ ጣሪያው ወድቆ የተገደሉትን 15 ሰዎች ለማሰብ ነው።

የሰርቢያ የቀድሞ የግንባታ ሚኒስትርን ጨምሮ ከአደጋው በኋላ ወደ 12 የሚጠጉ ሰዎች ታስረዋል።

ሚኒስትሩ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ጠቅሰው ከአደጋው ማግስት ከኃላፊነት ለቀዋል።

አገሪቱ ከዚያን ወዲህ በአገር አቀፍ ደረጃ አልፎ አልፎ በሚደረጉ ቁጣን በቀላቀሉ ተቃውሞዎች እየተናጠች ትገኛለች።

የቤልግሬድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በህዳር ወር አጋማሽ ፋኩልቲያቸውን ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ተቃውሞው ቀስ በቀስ ከ50 በላይ ዩኒቨርስቲዎች እና በበርካታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዛምቷል።

እሑድ ዕለት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተማሪዎቹን ተቀላቅለው በዋና ከተማዋ ቤልግሬድ ጎዳናዎች ላይ በመውጣት ለአደጋው ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

“ሁላችንም በጣሪያው ስር ነን”

የቤልግሬዱ ተቃውሞ

የእሑዱ ተቃውሞ ባለፉት ዓመታት በሰርቢያ ከተደረጉት ትልቁ ነው።

የስልክ መብራቶች የቤልግሬድ አደባባይን ሸፍነውታል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባዩን ሞልተው ለ15 ደቂቃ ያህል በጸጥታ የአደጋውን ሰለባዎች አስበዋል።

“ተማሪዎች ለረጅም ጊዜ ዝም ብለዋል። እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ኃላፊነት የጎደላቸው ክስተቶች ድምሮች ነበሩ” ሲል የኖቪ ሳድ የህክምና ተማሪ የሆነው ማክሲም ኢሊች ተናግሯል።

እሑድ ዕለት አርሶ አደሮች፣ የጤና ሠራተኞች፣ ተዋናዮች፣ አርቲስቶች እና በቤልግሬድ እና በሰርቢያ ባሉ የሌሎች ከተማ ነዋሪዎችም ተማሪዎቹ ተቀላቅለዋል።

በጸጥታ ተቃውሞው በተሰማበት ወቅት ሰልፈኞች “ሁላችንም ከጣሪያው ስር ነን” የሚል ጽሑፍ አሳይተዋል።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተማሪዎችን ተቀላቅለዋል

የቻይና የመንግሥት ኩባንያዎችን ባካተተው ፕሮጀክት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብቻ ሁለት ጊዜ እድሳት ተደርጎለት በነበረው የባቡር ጣቢያ ግንባታ ላይ የተንሰራፋው ሙስና እና ደካማ የግንባታ አፈጻጸም ለባቡር ጣቢያው ጣሪያ መውደቅ ምክንያት ነው ብለዋል።

“የመጣሁት እየተቀጣጠሉ ያሉ ተቃውሞዎችን ለመደገፍ ነው፤ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብዬ አምናለሁ።”

“ሁላችንም ወደ አዲስ እና ጤናማ ሕይወት እንድንሄድ ሁሉንም ነገር ከመሠረቱ መለወጥ አስፈላጊ ነው” ስትል ከቤልግሬድ አቅራቢያ ከምትገኘው ከፓንሴቮ ከተማ የመጣችው ሊዲያ ለቢቢሲ ሰርቢያ ተናግራለች።

በተማሪዎች ተቃውሞ ላይ እምነት እንዳላት የገለጸችው ሊዲያ የወጣቶቹ ቁጥር መጨመር ለሁሉም ማስጠንቀቂያ ነው ብላለች።

“በቃላቸው ጸንተው በመቆየታቸው እና አቋማቸውን ስላልቀየሩ ሁሌም ከተማሪዎቹ ጎን ቆሜያለሁ” ስትል ተናግራለች።

‘ሙስና ይገድላል’ በሚል መፈክር ታጅቦ ‘በደም የጨቀዩ እጆች’ የተቃውሞው ምልክት ሆነዋል።

‘እጆቻችሁ በደም ተጨማልቀዋል’፣ ‘አገር የሕጻናት ነው” የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል።

ከ15 ደቂቃ ጸጥታ በኋላ ህዝቡ ከፍተኛ ጩኸት እና ባለስልጣናትን የሚቃወሙ መፈክሮችን አሰምተዋል።

ባለሥልጣኖቹ ምርመራ በመጀመር ጥያቄውን እንደሚመልሱ ቢገልጹም የኖቪ ሳድ ባቡር ጣቢያን መልሶ ግንባታ በተመለከተ የወጡት ሰነዶች ያልተሟላ ናቸው ይላሉ ተማሪዎቹ።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኖቪ ሳድ ከንቲባም ከስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል።

አሽከርካሪዎች መኪናዎችን በማቆም ድጋፋቸውን ገልጸዋል

ሁሉም የቤልግሬድ ዩኒቨርሲቲዎች እና ኖቪ ሳድ እና ኒስ የሚባሉት ሁለት የአገሪቱ ትላልቅ ከተሞች እንቅስቃሴ ታግዶባቸው ነበር።

አንዳንድ የመምህራን ማኅበራት የትምህርት ክፍለ ጊዜን በማሳጠር ተቃውሞውን ለመቀላቀል ወስነዋል። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ደግሞ ተጎጂዎችን ለማክበር ከትምህርት ቤታቸው በገፍ ወጥተዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያለው አለመረጋጋት እየጨመረ ባለበት ወቅት የሰርቢያ የትምህርት ሚኒስቴር የክረምቱ የእረፍት ጊዜ አስቀድሞ እንዲጀመር ወስኗል።

የሰርቢያ ባለስልጣናት የተማሪዎቹን ጥያቄዎች በሙሉ መልሰናል ቢሉም ተማሪዎቹ ግን በዚህ አይስማሙም። የትኛውም ጥያቄያቸው ሙሉ በሙሉ አልተሟላም ሲሉ ይከራከራሉ።

ተቃውሞ

ተማሪዎቹ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል በኖቪ ሳድ የባቡር ጣቢያ ከጣሪያው መደርመስ ጋር የተያያዙ ሰነዶች ይፋ እንዲደረጉ የጠየቁት ይገኝበታል።

ምንም እንኳን 195 ሰነዶች በመንግሥት ድረ-ገጽ ላይ ቢታተሙም፤ ተማሪዎቹ ከ800 በላይ መኖራቸውን ገልጸው የተለቀቁት የፋይናንስ ዝርዝር ጉዳዮችን አላካተትም ብለዋል።

በቤልግሬድ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና ፋኩልቲ የወጡትን ሰነዶች በመተንተን ወሳኝ መረጃዎች እንደሚጎድሉ ገልጿል።

ከእሁድ ምሽት ተቃውሞ በኋላ የሰርቢያው ፕሬዝዳንት አሌክሳንዳር ቩቺች በኢንስታግራም ላይ በቤልግሬድ የተቃዋሚ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች “በጣም ትልቅ ሰልፍ አካሂደዋል” ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለመስማት፣ ሃሳባቸውን ለማወቅ እና እምነታቸውን ለሰርቢያ እንዲጠቅም ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል ።