ፖሊሶች እስረኛውን ይዘውት

ከ 5 ሰአት በፊት

በካቴና የታሰረ ጥቁር አሜሪካዊ እስረኛ ከመሞቱ በፊት የኒውዮርክ ማረሚያ ቤት ፖሊሶች ክፉኛ ሲደበድቡት የሚያሳይ ቪዲዮ ወጣ። የ43 ዓመቱ እስረኛ ሮበርት ብሩክስ በተደበደበ ማግስት በማረሚያ ቤቱ ህይወቱ አልፏል።

እስረኛው ህይወቱ ያለፈበት ማርሲ ማረሚያ ቤት የተደረገ የውስጥ ግምገማን ተከትሎ የኒውዮርክ ገዢ ካቺ ሆቺል በጥቃቱ የተሳተፉትን 13 መኮንኖች እና የማረሚያው ቤት ነርስ እንዲባረሩ አዘዋል።

የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሆኑት ሌቲሺያ ጄምስ ጽህፈት ቤት በሮበርት ሞት ላይ ምርመራ መክፈቱን አስታውቀዋል።

በጠቅላይ አቃቤ ህጓ አርብ ዕለት የተለቀቀው ቪዲዮ ሮበርት በህክምና የምርመራ አልጋ ላይ እጁ በካቴና ታስሮ በተቀመጠበት ወቅት ፖሊሶቹ ፊቱን እና ብልቱን ደጋግመው ሲመቱት ያሳያል።

አንደኛው የእስር ቤቱ መኮንን ሮበርትን ከመደብደቡ በፊት አፉ ውስጥ የሆነ ነገር ሲከትበት ያሳያል። ሌላኛው መኮንን ደግሞ በካቴና የታሰረውን ሮበርት ሆዱ ላይ በጫማ ሲመታው ያሳያል።

ቪዲዮው በተጨማሪም አንደኛው መኮንን አንገቱን ጨምድዶ አንቆ ካነሳው በኋላ በኃይል የምርመራው አልጋ ላይ ሲጥለው ያሳያል። ሮበርት ጥቃቱ በተፈጸመበት በማግስቱ ህይወቱ አልፏል። ሮበርት ለህልፈተ ህይወቱ መንስዔ አንገቱ ታንቆ መመሞቱን ወይም ‘አስፊክሲያ’ መሆኑን የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራዎች አረጋግጠዋል።

የእስር ቤቱ መኮንኖች ሮበርትን ወደ ማረሚያ ቤቱ ተቋም እንዲወስዱ ምክንያት የሆናቸው ጉዳይ ግልጽ አይደለም። ቪዲዮው ድምጽ የለውም።

አቃቤ ህጓ “ይህንን ቪዲዮ በተለይም በበዓል ሰሞን የለቀቁበት ምክንያት እንዳላቸው” ተናግረዋል።

“ቪዲዮዎቹን ይፋ ያደረግኩት ለሮበርት ቤተሰቦች ሃላፊነት እና ግዴታ ስላለብኝ ነው። በተጨማሪ ለኒውዮርክ ነዋሪዎች ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማሳየት ነው” ብለዋል።

ፖሊሶች እስረኛውን ሲደበድቡት

ሮበርት በጥቃት ክስ የ12 ዓመት እስር ተፈርዶበት እንደነበር አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። በእስር ከነበረበት ሞሃውክ ማረሚያ ቤት አቅራቢያው ወደሚገኘው ማርሲ ማረሚያ ቤት የተዛወረው ጥቃቱ በተፈጸመበት እለት ነው።

የሮበርት ቤተሰብን የወከሉት ጠበቃ ኤልዛቤት ማዙር በሰጡት መግለጫ ቪዲዮዎቹ “የጥቃቱን አሰቃቂነት እና አስከፊነት” የሚያሳይ ነው ብለዋል።

“መኖር ይገባው ነበር። በማርሲ ማረሚያ ውስጥ ያሉ ሁሉ በእስር ቤቱ ሰራተኞች ሊደርስባቸው የሚችል ጥቃትን በመፍራት በስጋት መኖር እንደሌለባቸው ማወቅ አለባቸው” ሲሉ ነው ጠበቃዋ የተናገሩት።

ቪዲዮው ከተለቀቀ በኋላ የኒውዮርክ ገዢ ሆቺል የተፈጠረው ክስተት “አስደንግጦኛል እንዲሁም አበሳጭቶኛል” ካሉ በኋላ በጥቃቱ የተሳተፉትን ተጠያቂ ለማድረግ እንደወሰኑ ተናግረዋል።

“የኒውዮርክ ግዛት ህግን ለሚጥሱ ግለሰቦች ምንም አይነት ትዕግስት የለውም። በዚህ ክስተት የተሳተፉትን በሙሉ ተጠያቂ ለማድረግ ቁርጠኛ ነኝ” ሲሉ አክለዋል።