
ከ 27 ደቂቃዎች በፊት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮን (አትሚስ) ለሚተካው ሌላኛው ተልዕኮ ስምሪት ፈቃድ ሰጠ።
ምክር ቤቱ አርብ፣ ታህሳስ 18/ 2017 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ አዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) አትሚስን እንዲተካ ያሳለፈውን ውሳኔ አጽድቆ የሶማሊያን የደህንንት ኃላፊነት ለአገሪቷ ለማሸጋገር መሰረታዊ እርምጃ ነው ብሏል።
ረቂቅ የውሳኔ ኃሳቡ ምንም ተቃውሞ በሌለበት በአስራ አራት ድምጽ እና አሜሪካ ተአቅቦ ባደረገችበት በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ከመጪው ጥር ጀምሮ ለ12 ወራት ያህል የሶማሊያ መንግሥት የአልሻባብን እና እንደ የኢራቁ እስላማዊ መንግሥት፣ ሌቫንት (ዳኢሽ)ን ለማሽመድመድ በሚያደርገው ጥረት አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንዲወስዱ ፈቅዷል።
ምክር ቤቱ ሶማሊያ የአገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ይህም ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ የተሰማሩትን 7,000 የአትሚስ የሰላም አስካባሪዎችን በአገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ለመተካት የበለጠ ኃላፊነት በመውሰድ እየተጫወተችው ያለውን ሚና አወድሷል።
በውሳኔው መሰረት የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት እስከ መጪው የአውሮፓውያኑ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 1,040 የፖሊስ አባላትን ጨምሮ እስከ 12 ሺህ ገደማ መለዮ ለባሽ የጸጥታ አካላት በአዲሱ ተልዕኮ (አውሶም) እንዲያሰማሩ ፈቅዷል።በተጨማሪም እስከዚህ ቀን ድረስ ሁሉንም የአፍሪካ ህብረት ወታደሮች ከአትሚስ ወደ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ማቀናጀትን እንዲጠናቀቅ ያትታል።
የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) የገንዘብ ድጋፍን በተመለከተ ለአፍሪካ ህብረት የሰላም ድጋፍ ስራዎች ድጋፍ የሚያደርግ ማዕቀፍ የተዘጋጀ ሲሆን ይህም የተባበሩት መንግሥታት በሚያደርገው ግምገማ የሚወሰን ይሆናል።
የኢትዮጵያው ልዑክ ከአትሚስ ወደ የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) የሚደረገው ሽግግር ስኬታማ የሚሆነው የሶማሊያ የጸጥታ ኃይሎች ሙሉ ኃላፊነታቸውን መወጣት ከቻሉ ብቻ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ ያቀረበውን ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድን ልዑኩ በመደገፍ ተጨማሪ ሽግግሮች አቅም እየተገመገመ በሂደት መሆን አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሌሎችአገራት ጋር በመሆን የሶማሊያን መንግሥት መልሶ በመገንባት ረገድ ግንባር ቀደም መሆኗን ጠቁመዋል።
- ሶማሊያ በቀይ ባህር ዳርቻ የባህር በር ለኢትዮጵያ ሰጥታለች መባሉን አስተባበለች27 ታህሳስ 2024
- የጸጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ ተተኪን በተመለከተ ድምጽ ሊሰጥ ነው27 ታህሳስ 2024
- ዶክተር ቴድሮስ እስራኤል በየመን ከፈጸመችው የአየር ጥቃት “በሕይወት ለመትረፌ እርግጠኛ አልነበርኩም” አሉከ 4 ሰአት በፊት
ከቀናት በኋላ ጊዜው ለሚጠናቀቀው አትሚስ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ጂቡቲ ወታደሮቻቸውን አዋጥተዋል። ለቀጣዪ ተልዕኮ አውሶም የሚሰማሩ ወታደሮች ከየትኛው አገር እንደሚሆኑ የመምረጥ ኃላፊነቱ የሶማሊያ ሲሆን ኢትዮጵያ በዚህ ተልዕኮ ወታደሮቿን ታሳትፋለች የሚለው እስካሁን አልታወቀም።
የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮቿን እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል አሰማርታ ኢትዮጵያ ሰራዊቷን አሰማርታ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር 3 ሺህ ያህል ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ስምምነት አዲሱ ተልዕኮ ከሚወሰንበት፣ ከሰኔ መጨረሻ በፊት ካልሰረዘች በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ስር እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት የሰፈሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንደሚወጡ የአገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሑሴን አሊ ከዚህ ቀደም ገልጸው ነበር።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ይህን ተከትሎ የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ሠራዊት ከአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ውጪ መሆኑን በይፋ አስታውቀው ነበር።
ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ሶማሊያ ውስጥ ሰላም ሲያስከብር የቆየው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከግዛቱ እንዲወጣ እንደሚፈልግ የሶማሊያ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።
ከዚህ ሁሉ መካረር በኋላ ግን የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መሪዎች አለመግባባታቸውን በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያውፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ፊርማቸውን ባኖሩበት የአንካራ ስምምነት መሰረት፤ “ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ስምምነቱ “የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ” ሲል ያትታል።