ለታጋች ማስለቀቂያ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ድጋፍ እንዲሆን አንድ ወረዳ የፃፈው አነጋጋሪ ደብዳቤ
(መሠረት ሚድያ)- በበርካታ የሀገራችን ክፍሎች ንፁሀን ዜጎች የእገታ ወንጀል እየተፈፀመባቸው ይገኛል፣ የታጋች ቤተሰቦችም በእምነት ተቋማት እና መንገድ ላይ ጭምር ከህዝብ በመለመን ለአጋቾች ገንዘብ ሲከፍሉ እንደነበር ይታወቃል።
ዛሬ ለመሠረት ሚድያ የደረሰ አንድ ደብዳቤ እንደሚያሳየው ደግሞ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ፓዊ ወረዳ ነዋሪ የሆነች አንድ ግለሰብ ገርበ ጉራቻ ላይ ሰኔ 2016 ዓ/ም እገታ ተፈፅሞባት እሷን ለማስለቀቅ የተጠየቀውን 1 ሚልዮን ብር ለማሰባሰብ እንዲረዳ የወረዳው አስተዳዳሪ የድጋፍ ደብዳቤ ፅፈዋል።
“… ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ማንኛውም መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ግለሰቦች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላት እንጠይቃለን” የሚለው በፓዊ ወረዳ አስተዳዳሪ የተፃፈው ደብዳቤ የእገታ ድርጊቱ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ እንደሆነ ማሳያ ተደርጎ እየተወሰደ ነው።
መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለአጋቾች የሚከፈል ገንዘብ በማሰባሰባቸው ዙርያ ያለዎትን አስተያየት ያጋሩን።